መጽሐፈ ኢዮብ 12
12
የኢዮብ መልስ
1ኢዮብም መለሰ፥ እንዲህም አለ፦
2“በእርግጥ እናንተ ዓይነተኞች ሰዎች ናችሁ፤
ጥበብም በእናንተ ዘንድ ትፈጸማለች።#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ይሞታል” ይላል።
3ነገር ግን እኔ ደግሞ እንደ እናንተ ልብ አለኝ።
እኔ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም፥
እንደዚህ ያለውን ነገር የሚያውቅ ማነው?#“እኔ ከእናንተ የማንስ አይደለሁም እንደዚህ ያለውን ነገር የሚያውቅ ማን ነው” የሚለው በዕብ. ብቻ።
4እግዚአብሔርን የጠራሁ እርሱም የመለሰልኝ እኔ፥
ለባልንጀራው መሣለቂያ እንደሚሆን ሰው ሆኛለሁ፤
ጻድቁና ንጹሑ ሰው መሣለቂያ ሆኖአል።#የምዕ. 12 ቍ. 4 የመጀመሪያዎቹ ሁለት መስመሮች በግሪክ ሰባ. ሊ. የሉም።
5እርሱ በተወሰነው ዕድሜ በሌሎች እንዲወድቅ፥
ቤቱም በኃጥኣን እንዲፈርስ ተዘጋጅቶአል።
ነገር ግን ማንም ክፉ ሆኖ ንጹሕ እንደሚሆን አይመን።
6እግዚአብሔርን የሚያስቈጡትን ሰዎች፥
እርሱ የሚመረምራቸው አይደለምን?
7“አሁን ግን እንስሶችን ጠይቅ፥ ያስተምሩህማል፤
የሰማይንም ወፎች ጠይቅ፥ ይነግሩህማል።
8ለምድር ንገራት፥
እርስዋም ትተረጕምልሃለች፤
የባሕርም ዓሣዎች ያስረዱሃል።
9የእግዚአብሔር እጅ ይህን ሁሉ እንዳደረገ
ከእነዚህ ሁሉ የማያውቅ ማን ነው?
10የሕያዋን ሁሉ ነፍስ፥
የሰውም ሁሉ መንፈስ በእጁ ናትና።
11ዦሮ ነገርን የሚለይ አይደለምን?
ጕረሮስ#ዕብ. “ምላስ” ይላል። መብልን የሚቀምስ አይደለምን?
12በረዥም ዘመን ጥበብ፥
በመኖር ብዛትም ዕውቀት ይገኛል።
13በእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ኀይል አለ፤
ለእርሱ ምክርና ማስተዋል አለው።
14እነሆ፥ እርሱ ቢያፈርስ፥ ማን ይሠራል?
በሰውም ላይ ቢዘጋበት ማን ይከፍታል?
15እነሆ፥ ዝናብን ከሰማይ ቢከለክል ምድርን ያደርቃታል፤
እንደገና ቢተዋትም ትጠፋለች፤ ትገለበጣለችም።
16ኀይልና ብርታት በእርሱ ዘንድ ናቸው፤
ዕውቀትና ማስተዋልም ለእርሱ ናቸው።
17መካሮችንም እንዲማረኩ ያደርጋቸዋል፤
የምድር ፈራጆችንም አላዋቆች ያደርጋቸዋል።
18ነገሥታትንም በዙፋን ያስቀምጣቸዋል፤
ወገባቸውንም በኀይል መታጠቂያ ያስታጥቃቸዋል።
19ካህናተ ጣዖትን እንዲማረኩ ያደርጋቸዋል፤
የምድር ኀያላንንም ይገለብጣቸዋል።
20ከታመኑ ሰዎችም ቋንቋን ይለውጣል፤
የሽማግሌዎችንም ምክር ያውቃል።
21በአለቆች ላይ ውርደትን ያመጣል፥
ትሑታንንም ያድናቸዋል።
22ጥልቅ ነገርን ከጨለማ ይገልጣል፤
የሞትንም ጥላ ወደ ብርሃን ያወጣል።
23አሕዛብን ያቅበዘብዛቸዋል፤ ያጠፋቸዋልም፤
አሕዛብንም ይገለብጣቸዋል፤ ያፈልሳቸዋልም።
24የምድር አለቆች ማስተዋልን ይለውጣል።
በማያውቁት መንገድም ያቅበዘብዛቸዋል።
25ብርሃንም ሳይኖር በጨለማ ይርመሰመሳሉ፤
እንደ ሰካራምም ይፍገመገማሉ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ኢዮብ 12: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ