ትንቢተ ኤርምያስ 41
41
1እንዲህም ሆነ፤ በሰባተኛው ወር ከመንግሥት ወገንና ከንጉሡ ዋና ዋና አለቆች አንዱ የኤሊሳማ ልጅ የናታንያ ልጅ እስማኤል ከዐሥር ሰዎች ጋር ወደ መሴፋ ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ መጣ፤ በዚያም በመሴፋ በአንድ ላይ እንጀራ በሉ። 2የናታንያም ልጅ እስማኤል ከእርሱም ጋር የነበሩት ዐሥሩ ሰዎች ተነሥተው የሳፋንን ልጅ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በሰይፍ መቱ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በሀገሩ ላይ የሾመውን ገደሉ። 3እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር በመሴፋ የነበሩትን አይሁድ ሁሉ፥ በዚያም የተገኙትን ከለዳውያንን ሁሉ፤ ሰልፈኞች ሰዎችንም#“ሰልፈኞች ሰዎችንም” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሁሉ ገደላቸው።
4እስማኤል ማንም ሳያውቅ ጎዶልያስን ከገደለ በኋላ በሁለተኛው ቀን እንዲህ ሆነ፤ 5ጢማቸውን ላጭተው፥ ልብሳቸውንም ቀድደው እያለቀሱ#ዕብ. “ገላቸውን ነጭተው” ሲል ግሪክ ሰባ. ሊ. ደግሞ “ደረታቸውን እየደቁ” የሚል ይጨምራል። ወደ እግዚአብሔር ቤት ያቀርቡ ዘንድ የእህል ቍርባንና ዕጣን በእጃቸው የያዙ፥ ሰማንያ ሰዎች ከሴኬምና ከሴሎ፥ ከሰማርያም መጡ። 6የናታንያም ልጅ እስማኤል ከመሴፋ ወጥቶ እያለቀሰ ሊገናኛቸው ሄደ፤ በተገናኛቸውም ጊዜ፥ “ወደ አኪቃም ልጅ ወደ ጎዶልያስ ኑ” አላቸው። 7ወደ ከተማም መካከል በመጡ ጊዜ የናታንያ ልጅ እስማኤል፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሰዎች ገደሉአቸው፤ በጕድጓድም መካከል ጣሉአቸው። 8በዚያም የተገኙ ዐሥር ሰዎች ቀርበው እስማኤልን እንዲህ አሉት፥ “በሜዳው ድልብ አለንና፥ ገብስና ስንዴ፥ ዘይትና ማርም አለንና አትግደለን፤” እርሱም በወንድሞቻቸው መካከል እነርሱን መግደል ተወ።
9እስማኤልም ከጎዶልያስ ጋር የገደላቸውን ሰዎች ሬሳ ሁሉ የጣለበት ጕድጓድ ንጉሡ አሳ የእስራኤልን ንጉሥ ባኦስን ስለ ፈራ የሠራው ጕድጓድ ነበረ፤ የናታንያም ልጅ እስማኤል የገደላቸውን ሞላበት። 10እስማኤልም በመሴፋ የነበረውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ የንጉሡን ሴቶች ልጆች፥ የአዛዦች አለቃ ናቡዛርዳን ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ የሰጠውን በመሴፋ የቀሩትን ሕዝብ ሁሉ መለሰ፤#ዕብ. “ማረካቸው” ይላል። የናታንያም ልጅ እስማኤል ወደ አሞን ልጆች ይሄድ ዘንድ ተነሣ።
11የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ የጭፍራ አለቆች ሁሉ የናታንያ ልጅ እስማኤል ያደረገውን ክፋት ሁሉ ሰሙ። 12ሠራዊቱንም ሁሉ ይዘው ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ጋር ሊዋጉ ሄዱ። በገባዖንም ባለው በብዙ ውኃ አጠገብ አገኙት። 13እንዲህም ሆነ፤ ከእስማኤል ጋር የነበሩት ሕዝብ ሁሉ የቃርሔን ልጅ ዮሐናንን ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆችን ሁሉ ባዩ ጊዜ ደስ አላቸው። 14እስማኤልም ከመሴፋ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ተመልሰው ወደ ቃርሔም ልጅ#“እስማኤልም ከመሴፋ የማረካቸው ሕዝብ ሁሉ ተመልሰው ወደ ቃርሔም ልጅ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ወደ ዮሐናን ሔዱ። 15የናታንያ ልጅ እስማኤል ግን ከስምንት ሰዎች ጋር ከዮሐናን አመለጠ፥ ወደ አሞንም ልጆች ሄደ።
16የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩት የጭፍራ አለቆች ሁሉ የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን በመሴፋ ከገደለው በኋላ ከናታንያ ልጅ ከእስማኤል ያስመለሱአቸውን የሕዝቡን ቅሬታ ሁሉ፥ ከገባዖን ያስመለሱአቸውን ኀያላን ሰልፈኞችን፥ ሴቶችንም፥ ልጆችንም፥ ጃንደረቦችንም ወሰዱ፤ 17ተነሥተውም ወደ ግብፅ ይሄዱ ዘንድ በቤተልሔም አጠገብ በአለው በጌሮት-ከመዓም ተቀመጡ፤ 18እስማኤል የባቢሎን ንጉሥ በሀገሩ ላይ የሾመውን የአኪቃምን ልጅ ጎዶልያስን ስለ ገደለው ከለዳውያንን ፈርተዋልና።#ምዕ. 41 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 48 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 41: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ