ትንቢተ ኤርምያስ 42
42
ኤርምያስ እንዲጸልይላቸው ሕዝቡ እንደ ጠየቁ
1የጭፍራ አለቆችም ሁሉ፥ የቃርሔም ልጅ ዮሐናን፥ የሐናንያ#ዕብ. “ሆሻያ” ሲል ግሪክ ሰባ. ሊ. “ማሲያ” ይላል። ልጅ ኢዛንያስ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ዓዛርያስ” ይላል። ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ ነቢዩ ወደ ኤርምያስ መጡ። 2እንዲህም አሉት፥ “እባክህ ልመናችን በፊትህ ትድረስ፤ ስለ እኛ፥ ስለ እነዚህም ቅሬታዎች ሁሉ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን፤ ዐይኖችህ እንደ አዩን ከብዙ ጥቂት ቀርተናልና። 3አምላክህ እግዚአብሔርም የምንሄድበትን መንገድና የምናደርገውን ነገር ይንገረን።”
4ነቢዩ ኤርምያስም አላቸው፥ “ሰምታችኋል፤ እነሆ እንደ ቃላችሁ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር እጸልያለሁ፤ እግዚአብሔርም የሚመልስልኝን ሁሉ እነግራችኋለሁ፤ ከእናንተም አንድም ቃል አልሸሽግም።” 5ኤርምያስንም፥ “አምላክህ እግዚአብሔር ወደ እኛ የላከህን ነገር ሁሉ ባናደርግ፥ እግዚአብሔር በመካከላችን እውነተኛና ታማኝ ምስክር ይሁን። 6የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል ስለምንሰማ መልካም እንዲሆንልን፥ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን፥ አንተን ወደ እርሱ የምንልክህ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ቃል እንሰማለን” አሉት።
ለኤርምያስ ጸሎት እግዚአብሔር የሰጠው መልስ
7እንዲህም ሆነ፤ ከዐሥር ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ መጣ። 8የቃርሔምንም ልጅ ዮሐናንን፥ ከእርሱም ጋር የነበሩትን የጭፍራ አለቆች ሁሉ፥ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ሕዝቡንም ሁሉ ጠራ፤ 9እንዲህም አላቸው፥ “ልመናችሁን በፊቱ አቀርብ ዘንድ ወደ እርሱ የላካችሁኝ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 10አደርግባችሁ ዘንድ ከአሰብሁት ክፉ ነገር ተመልሻለሁና በዚች ምድር ብትቀመጡ እሠራችኋለሁ እንጂ አላፈርሳችሁም፥ እተክላችኋለሁ እንጂ አልነቅላችሁም። 11ከምትፈሩት ከባቢሎን ንጉሥ ፊት አትፍሩ፤ አድናችሁ ዘንድ፥ ከእጁም አስጥላችሁ ዘንድ እኔ ከእናንተ ጋር ነኝና አትፍሩ፥ ይላል እግዚአብሔር። 12ይቅርታን እሰጣችኋለሁ፤ ይቅርም እላችኋለሁ፤ ወደ ሀገራችሁም እመልሳችኋለሁ።
13“እናንተ ግን በዚች ምድር አንቀመጥም ብትሉ፥ የአምላካችሁንም የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ 14እናንተም፦ አይደለም፤ ሰልፍ ወደማናይባት፥ የመለከትም ድምፅ ወደማንሰማባት፥ እንጀራንም ወደማንራብባት ወደ ግብፅ ምድር እንሄዳለን፤ በዚያም እንቀመጣለን ብትሉ፥ 15ስለዚህ እናንተ#“ስለዚህ እናንተ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የይሁዳ ቅሬታ ሆይ! አሁን እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ግብፅም ትገቡ ዘንድ በዚያም ትቀመጡ ዘንድ ፊታችሁን ብታቀኑ፤ 16እናንተ የምትፈሩት ሰይፍ በዚያ በግብፅ ምድር ያገኛችኋል፤ ስለ እርሱም የምትደነግጡበት ራብ በዚያ በግብፅ ይደርስባችኋል፤ በዚያም ትሞታላችሁ። 17ወደ ግብፅም ይገቡ ዘንድ፥ በዚያም ይቀመጡ ዘንድ ፊታቸውን በሚያቀኑ ሰዎች ሁሉ እንዲህ ይሆንባቸዋል፤ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም ያልቃሉ፤ እኔም ከማመጣባቸው ክፉ ነገር ማንም አይቀርም፤ ማንም አያመልጥም።
18“የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ ቍጣዬና መቅሠፍቴ በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ላይ እንደ ፈሰሰ፥ እንዲሁ ወደ ግብፅ በገባችሁ ጊዜ መዓቴ ይፈስስባችኋል፤ እናንተም ለጥላቻና ለጥፋት ለስድብና ለርግማን ትሆናላችሁ፤ ይችንም ስፍራ ከእንግዲህ ወዲህ አታዩአትም። 19እናንተ የይሁዳ ቅሬታ ሆይ! እግዚአብሔር፦ ወደ ግብፅ አትግቡ ብሎ ተናግሮባችኋልና ዛሬ እንዳስጠነቀቅኋችሁ በእርግጥ ዕወቁ። 20እናንተ፦ ሰለ እኛ ወደ አምላካችን ወደ እግዚአብሔር ጸልይ፤ አምላካችንም እግዚአብሔር የሚናገርህን ሁሉ ንገረን፤ እኛም እናደርገዋለን ብላችሁ ወደ እግዚአብሔር ወደ አምላካችሁ ልካችሁኝ ነበርና ራሳችሁን አታልላችኋል። 21እኔም ዛሬ ነግሬአችኋለሁ፤ ወደ እናንተም በላከኝ ነገር ሁሉ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማችሁም። 22አሁንም ሄዳችሁ እንድትቀመጡ በወደዳችሁበት ስፍራ በሰይፍና በራብ፥ በቸነፈርም እንድትሞቱ በእርግጥ ዕወቁ።”#ምዕ. 42 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 49 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 42: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ