ትንቢተ ኤርምያስ 36
36
ባሮክ የተጠቀለለውን ብራና በቤተ መቅደስ እንዳነበበውና ንጉሡ እንዳቃጠለው
1እንዲህም ሆነ፤ በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ ልጅ በኢዮአቄም በአራተኛው ዓመተ መንግሥት ይህ ቃል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ። 2“አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከይሁዳ ንጉሥ ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በኢየሩሳሌም” የሚል ይጨምራል። በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 3ምናልባት የይሁዳ ቤት ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ፥ እኔም በደላቸውንና ኀጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ፥ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል።”
4ኤርምያስም የኔርዩን ልጅ ባሮክን ጠራ፤ ባሮክም እግዚአብሔር ለእርሱ የተናገረውን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ በመጽሐፉ ክርታስ ጻፈ። 5ኤርምያስም ባሮክን እንዲህ ሲል አዘዘው፥ “እኔ እስረኛ ነኝ፤ ወደ እግዚአብሔር ቤትም እገባ ዘንድ አልችልም። 6አንተ ግን ገብተህ ከአፌ የጻፍኸውን የእግዚአብሔርን ቃል በጾም ቀን በእግዚአብሔር ቤት በሕዝቡ ጆሮ በክርታሱ አንብብ፤ ደግሞም ከከተሞቻቸው በሚወጡ በይሁዳ ሰዎች ሁሉ ጆሮ አንብበው። 7እግዚአብሔር በዚህ ሕዝብ ላይ የተናገረው ቍጣውና መዓቱ ታላቅ ነውና ምናልባት ልመናቸው በእግዚአብሔር ፊት ትደርስ ይሆናል፤ ሁሉም ከክፉ መንገዳቸው ይመለሱ ይሆናል።” 8የኔርዩም ልጅ ባሮክ ነቢዩ ኤርምያስ ያዘዘውን ሁሉ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ቤት የእግዚአብሔርን ቃል በመጽሐፉ አነበበ።
9እንዲህም ሆነ፤ የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስ ልጅ ኢዮአቄም በነገሠ በአምስተኛው#“ስምንት” የሚልም ይገኛል። ዓመት በዘጠነኛው ወር በኢየሩሳሌም የተቀመጡ ሕዝብ ሁሉ፥ ከይሁዳም ከተሞች ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ለመጾም ዐዋጅ ነገሩ። 10ባሮክም የኤርምያስን ቃል በእግዚአብሔር ቤት በላይኛው አደባባይ በእግዚአብሔር ቤት በአዲሱ በር መግቢያ ባለው በጸሓፊው በሳፋን ልጅ በገማርያ ክፍል በሕዝቡ ሁሉ ጆሮ በመጽሐፉ አንበበ።
11የሳፋንም ልጅ የገማርያ ልጅ ሚክያስ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ከመጽሐፉ ሰማ። 12ወደ ንጉሡም ቤት ወደ ጸሓፊው ክፍል ወረደ፤ እነሆም አለቆቹ ሁሉ፥ ጸሓፊው ኤሊሳማ፥ የሸማያ ልጅ ድላያ፥ የዓክቦር ልጅ ኤልናታን፥ የሳፋን ልጅ ገማርያ፥ የሐናንያ ልጅ ሴዴቅያስ፥ አለቆቹም ሁሉ በዚያ ተቀምጠው ነበር። 13ሚክያስም ባሮክ በሕዝቡ ጆሮ በመጽሐፉ በአነበበ ጊዜ የሰማውን ቃል ሁሉ ነገራቸው። 14አለቆቹም ሁሉ፥ “በሕዝቡ ጆሮ ያነበብኸውን ክርታስ በእጅህ ይዘህ ና” ብለው የኩሲ ልጅ የሰሌምያ ልጅ የናታንያ ልጅ ይሁዳን ወደ ኔርዩ ልጅ ወደ ባሮክ ላኩ። የኔርዩም ልጅ ባሮክ ክርታሱን በእጁ ይዞ ወደ እነርሱ ወረደ። 15እነርሱም፥ “እስኪ ተቀመጥ፤ በጆሮአችንም አንብብ” አሉት። ባሮክም በጆሮአቸው አነበበው። 16እንዲህም ሆነ፦ ቃሉን ሁሉ በሰሙ ጊዜ ፈርተው እርስ በርሳቸው ተመካከሩ፤ ባሮክንም፥ “ይህን ቃል ሁሉ በርግጥ ለንጉሡ እንናገራለን” አሉት። 17ባሮክንም፥ “ይህን ቃል ሁሉ እንዴት እንደ ጻፍኸው ንገረን” ብለው ጠየቁት። 18ባሮክም፥ “ኤርምያስ ይህን ቃል ከአፉ ይነግረኝ ነበር፤ እኔም በመጽሐፉ ላይ እጽፍ ነበር” ብሎ መለሰላቸው። 19አለቆቹም ባሮክን፥ “አንተና ኤርምያስ ሂዱ፤ ተሸሸጉ፤ ወዴትም እንደ ሆናችሁ ማንም አይወቅ” አሉት።
20ወደ ንጉሡም ወደ አደባባይ ገቡ፥ ክርታሱንም በጸሓፊው በኤሊሳማ ክፍል አኑረውት ነበር፤ ቃሉንም ሁሉ ለንጉሡ ተናገሩ። 21ንጉሡም ክርታሱን ያመጣ ዘንድ ይሁዳን ላከ፤ እርሱም ከጸሓፊው ከኤሊሳማ ክፍል ወሰደው፤ ይሁዳም በንጉሡና በንጉሡ አጠገብ በቆሙት አለቆች ሁሉ ጆሮ አነበበው። 22ንጉሡም በዘጠነኛው ወር#“በዘጠነኛው ወር” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በክረምት በሚቀመጥበት ቤት ተቀምጦ ነበር፤ በፊቱም እሳት ይነድድ ነበር። 23ይሁዳም ሦስትና አራት ዐምድ ያህል በአነበበ ቍጥር፥ ንጉሡ በብርዕ መቍረጫ ቀደደው፤ ክርታሱንም በምድጃ ውስጥ በአለው እሳት ፈጽሞ እስኪቃጠል ድረስ በምድጃ ውስጥ ወደ አለው እሳት ጣለው። 24ንጉሡም፥ ይህንም ቃል ሁሉ የሰሙ አገልጋዮቹ ሁሉ አልደነገጡም፤ ልብሳቸውንም አልቀደዱም። 25ነገር ግን ኤልናታንና ጎዶልያ፥ ገማርያም#“ገማልያል” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ክርታሱን እንዳያቃጥል ንጉሡን ለመኑት፤ እርሱ ግን አልሰማቸውም። 26ንጉሡም ጸሓፊውን ባሮክንና ነቢዩን ኤርምያስን ይይዙ ዘንድ የንጉሡን ልጅ ይረሕምኤልንና የዓዝርኤልን ልጅ ሠራያን የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን#“የዓብድኤልንም ልጅ ሰሌምያን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። አዘዘ፤ እግዚአብሔር ግን ሰወራቸው።
የተቃጠለው መጽሐፍ እንደ ገና እንደ ተጻፈ
27ንጉሡም፥ ባሮክ ከኤርምያስ አፍ የጻፈው ቃል ያለበትን ክርታስ ካቃጠለ በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ ኤርምያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 28“ዳግመኛም ሌላ ክርታስ ውሰድ፤ የይሁዳም ንጉሥ ኢዮአቄም በአቃጠለው ክርታስ ላይ የነበረውን የቀድሞውን ቃል ሁሉ ጻፍበት። 29የይሁዳንም ንጉሥ ኢዮአቄምን እንዲህ በለው፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ አንተ፦ የባቢሎን ንጉሥ በርግጥ ይመጣል፤ ይችንም ሀገር ያፈርሳታል፤ ሰውና እንስሳም ያልቃሉ ብለህ ለምን ጻፍህበት? ብለህ ይህን ክርታስ አቃጥለሃል። 30ስለዚህም ስለ ይሁዳ ንጉሥ ስለ ኢዮአቄም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ በዳዊት ዙፋን ላይ የሚቀመጥ ልጅ አይኖርለትም፥ ሬሳውም በቀን ለትኩሳት፥ በሌሊትም ለውርጭ ይጣላል። 31ስለ ኀጢአታቸውም እርሱንና ዘሩን አገልጋዮቹንም በመዓት እጐበኛለሁ፤ እነርሱም አልሰሙምና የተናገርሁባቸውን ክፉ ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይና በኢየሩሳሌም በሚቀመጡ በይሁዳም ሰዎች ላይ አመጣለሁ።”
32ኤርምያስም ሌላ ክርታስ ወሰደ፤ ለኔርዩም ልጅ ለጸሓፊው ለባሮክ ሰጠው፤ እርሱም የይሁዳ ንጉሥ ኢዮአቄም በእሳት ያቃጠለውን የመጽሐፉን ቃል ሁሉ ከኤርምያስ አፍ ጻፈበት፤ ደግሞም እንደ ቀድሞው ያለ ቃል ብዙ ቃል ተጨመረበት።#ምዕ. 36 በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 43 ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 36: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ