ትንቢተ ኤርምያስ 12
12
ኤርምያስ ወደ እግዚእብሔር ያቀረበው እሮሮ
1አቤቱ! ከአንተ ጋር በተምዋገትሁ ጊዜ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ነገር ግን ከአንተ ጋር ስለ ፍርድ ልናገር። የኀጢአተኞች መንገድ ስለ ምን ይቀናል? በደልንስ የሚያደርጉ ሁሉ ስለ ምን ደስ ይላቸዋል? 2አንተ ተክለሃቸዋል፤ ሥር ሰድደዋል፤ ወልደዋል#ዕብ. “አድገዋል” ይላል። አፍርተውማል፤ በአፋቸውም አንተ ቅርብ ነህ፤ ከልባቸው ግን ሩቅ ነህ። 3አንተ ግን አቤቱ! ዐውቀኸኛል፤ አይተኸኛል፤ ልቤንም በፊትህ ፈትነሃል፤ እንደ በጎች ለመታረድ ጐትተህ ለያቸው፤ ለመታረድም ቀን አዘጋጃቸው። 4በሚኖሩባት ሰዎች ክፋት ምድሪቱ የምታለቅሰውና የዱሩ ሣርስ ሁሉ የሚደርቀው እስከ መቼ ነው? እግዚአብሔር ፍጻሜያችንን አያይም ብለዋልና እንስሶችና ወፎችም ጠፍተዋል።
5እግሮችህ ሮጠው ይደክማሉ፤ ፈረሶችን ለምን ታስጌጣለህ? በሰላምም ምድር ላይ ለምን ትታመናለህ? በዮርዳኖስስ ጩኸት ለምን እንዲህ ታደርጋለህ? 6ወንድሞችህና የአባትህ ቤት እነርሱ ጭምር ክደውሃልና፥ ጮኸውም በስተኋላህ ተሰበሰቡ፤ በመልካምም ቢናገሩህ አትመናቸው።
7ቤቴን ትችአለሁ፤ ርስቴንም ጥያለሁ፤ ነፍሴ የምትወድዳትንም በጠላቶችዋ እጅ አሳልፌ ሰጥቻለሁ። 8ርስቴ በዱር እንደ አለ አንበሳ ሆናብኛለች፤ ድምፅዋንም አንሥታብኛለች፤ ስለዚህ ጠልቻታለሁ። 9ርስቴ እንደ ጅብ ጕድጓድ ናትን? ወይስ በዙሪያዋ የሚከቡአት የሽፍቶች ዋሻ ናትን? የምድር አራዊት ሁሉ ይበሉአት ዘንድ ተሰብስበው ይመጣሉ። 10ብዙ እረኞች የወይኑን ቦታዬን አጥፍተዋል፤ እድል ፈንታዬንም አርክሰዋል፤ የምወድዳትንም እድል ፈንታ ምድረ በዳ አድርገዋታል። 11እርስዋም ለፍጹም ጥፋት ሆናለች፤ ስለ እኔም ምድር ሁሉ ባድማ ሆናለች፤ በልቡም የሚያኖራት የለም። 12ወራዶች ወደ ዱር ሁሉ#ዕብ. “በዝባዦች” ይላል። መጥተዋል፤ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከምድር ዳር ጀምሮ እስከ ምድር ዳር ድረስ ይበላልና፤ ለሥጋ ለባሽ ሁሉ ሰላም የለም። 13ስንዴን ትዘራላችሁ፤ እሾህንም ታጭዳላችሁ፤ ዕጣችሁም ምንም አይጠቅማችሁም፤ ከእግዚአብሔር ጽኑ ቍጣ የተነሣ በአዝመራችሁ ታፍራላችሁ።
14እግዚአብሔር ለሕዝቤ ለእስራኤል ያወረስሁትን ርስት ለሚነኩት ክፉዎች ጎረቤቶች ሁሉ እንዲህ ይላልና፥ “እነሆ ከምድራቸው እነቅላቸዋለሁ፤ የይሁዳንም ቤት ከመካከላቸው እነቅለዋለሁ። 15ከነቀልኋቸውም በኋላ መልሼ ይቅር እላቸዋለሁ፥ ሁላቸውንም በርስታቸው፥ እያንዳንዳቸውንም በምድራቸው አኖራቸዋለሁ። 16በበዓል ይምሉ ዘንድ ሕዝቤን እንዳስተማሩ በስሜ፦ ሕያው እግዚአብሔርን! ብለው ይምሉ ዘንድ የሕዝቤን መንገድ ፈጽመው ቢማሩ፥ በዚያ ጊዜ በሕዝቤ መካከል ይመሠረታሉ። 17ባይመለሱ ግን ያን ሕዝብ እነቅለዋለሁ፤ አስወግደዋለሁ፤ አጠፋውማለሁ፤” ይላል እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 12: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ