ትንቢተ ኤርምያስ 13
13
ከተልባ እግር የተሠራ መታጠቂያ
1እግዚአብሔር እንዲህ ይለኛል፦ ሂድ፥ ከተልባ እግር የተሠራችን መታጠቂያ ለአንተ ግዛ፤ ወገብህንም ታጠቅባት፤ በውኃውም ውስጥ አትንከራት። 2እግዚአብሔርም እንዳለኝ የተልባ እግር መታጠቂያን ገዛሁ፤ ወገቤንም ታጠቅሁባት። 3ዳግመኛም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 4“ለወገብህ የገዛሃትን ያቺን መታጠቂያ ወስደህ ተነሥ፤ ወደ ኤፍራጥስም ሂድ፤ በዚያም በተሰነጠቀ ዓለት ውስጥ ሸሽጋት።” 5እግዚአብሔርም እንዳዘዘኝ ሄድሁ፤ በኤፍራጥስም ወንዝ አጠገብ ሸሸግኋት። 6ከብዙ ቀንም በኋላ እግዚአብሔር፥ “ተነሥተህ ወደ ኤፍራጥስ ሂድ፥ በዚያም ትሸሽጋት ዘንድ ያዘዝሁህን መታጠቂያ ከዚያ ውስጥ ውሰድ” አለኝ። 7እኔም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ሄድሁ፤ ቈፈርሁም፤ ከቀበርሁበትም ስፍራ መታጠቂያዪቱን ወሰድሁ። እነሆም መታጠቂያዪቱ ተበላሽታ ነበር፤ ለምንም አልረባችም።
8የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤ 9እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እንዲሁ የይሁዳን ትዕቢት፥ ታላቁንም የኢየሩሳሌምን ትዕቢት አበላሻለሁ። 10ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ የሚሉ፥ በክፉ ልባቸውም እልከኝነት የሚሄዱ፥ ያገለግሏቸውና ይሰግዱላቸው ዘንድ ሌሎችን አማልክት ተከትለው የሚሄዱ እነዚህ ክፉ ሕዝብ አንዳች እንደማትረባ እንደዚች መታጠቂያ ይሆናሉ። 11መታጠቂያ በሰው ወገብ ላይ እንደምትጣበቅ፥ እንዲሁ ለስም፥ ለመመኪያና ለክብር ሕዝብ ይሆኑልኝ ዘንድ የእስራኤልን ቤት ሁሉ፥ የይሁዳንም ቤት ሁሉ ከእኔ ጋር አጣብቄአለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን አልሰሙም።”
የወይን ጠጅ ማድጋ
12ስለዚህ፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ ይሞላል” ብለህ ትነግራቸዋለህ፤ እነርሱም፥ “ማድጋ ሁሉ የወይን ጠጅ እንዲሞላ በውኑ እኛ አናውቅምን?” ቢሉህ፤ 13አንተም እንዲህ ትላቸዋለህ፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በዚህች ምድር የሚኖሩትን ሁሉ፥ በዳዊት ዙፋን የሚቀመጡትን ነገሥታት፥ ካህናቱንም፥ ነቢያቱንም፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም የተቀመጡትን ሁሉ በስካር እሞላቸዋለሁ። 14ሰውንና ወንድሙን፥ አባቶችንና ልጆችን በአንድ ላይ እበትናቸዋለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ አጠፋቸዋለሁ እንጂ አልራራላቸውም፤ አላዝንላቸውም፤ አልምራቸውምም።”
ኤርምያስ ስለ ትዕቢት የሰጠው ማስጠንቀቂያ
15ስሙ፤ አድምጡ፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና አትታበዩ። 16ሳይጨልምባችሁ፥ ጨለማም ባለባቸው ተራሮች እግሮቻችሁ ሳይሰነካከሉ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ክብርን ስጡ፤ በዚያም የሞት ጥላ አለና በጨለማውም ውስጥ ያኖራችኋልና ብርሃንን ተስፋ ታደርጋላችሁ። 17ይህን ባትሰሙ ነፍሴ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ነፍሳችሁ” ይላል። ስለ ትዕቢታችሁ በስውር ታለቅሳለች፤ የእግዚአብሔርም መንጋ ተሰብሮአልና ዐይኔ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ዐይኖቻችሁ” ይላል። ታነባለች፤ እንባንም ታፈስሳለች።
18ለነገሥታቱና ለመኳንንቱ፦#ዕብ. “ለንጉሡፍክ ና ለንግሥት እናት ለእቴጌዪቱ” ይላል። የክብራችሁ አክሊል ከራሳችሁ ወርዶአልና ራሳችሁን አዋርዳችሁ ተቀመጡ በላቸው። 19የደቡብ ከተሞች ተዘግተዋል፤ የሚከፍታቸውም የለም፤ ይሁዳ ሁሉ ተሰድዶአል፤ ፈጽሞም ተሰድዶአል።
20ኢየሩሳሌም ሆይ! ዐይንሽን አንሥተሽ እነዚህን ከሰሜን የሚመጡትን ተመልከቺ፤ ለአንቺ የሰጠሁሽ መንጋ፤ የክብር በጎችሽ ወዴት አሉ? 21አንቺ ትምህርት ያስተማርሻቸው አለቆችሽ ሆነው በጐበኙሽ ጊዜ ምን ትያለሽ? እንደ ወላድ ሴት ምጥ አይዝሽምን? 22በልብሽም፦ እንዲህ ያለ ነገር ስለ ምን ደረሰብኝ? ብትዪ፥ ከኀጢአትሽ ብዛት የተነሣ ልብስሽ በስተኋላሽ ተገፎአል፤ ተረከዝሽም ተገልጦአል።
23በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን? በዚያ ጊዜ ክፋትን የለመዳችሁ እናንተ ደግሞ በጎ ለማድረግ ትችላላችሁን? 24ነፋስ በምድረ በዳ እንደሚበትነው እብቅ እበትናችኋለሁ። 25ረስተሽኛልና፥ በሐሰትም ታምነሻልና ዕጣሽና እድል ፈንታሽ ይህ ነው፥ ይላል እግዚአብሔር። 26ስለዚህም የልብስሽን ዘርፍ በስተኋላሽ ወደ ፊትሽ እገልጣለሁ እፍረትሽም ይታያል። 27አስጸያፊ ሥራሽን፥ ምንዝርናሽን፥ ማሽካካትሽን፥ የዝሙትሽንም መዳራት በኮረብቶች ላይ፥ በሜዳም ላይ አይቻለሁ። ኢየሩሳሌም ሆይ! ወዮልሽ! ለመንጻት እንቢ ብለሻል፤ ይህስ እስከ መቼ ነው?
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 13: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ