ትንቢተ ኤርምያስ 11
11
እስራኤልና ይሁዳ ቃል ኪዳንን እንዳፈረሱ
1ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣው ቃል ይህ ነው። 2የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ፤ ለይሁዳም ሰዎች በኢየሩሳሌምም ለሚኖሩ ተናገሩ፤ 3እንደዚህም በሏቸው፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የዚህን ቃል ኪዳን ቃል የማይሰማ ሰው ርጉም ይሁን፤ 4ከግብፅ ሀገር ከብረት ምድጃ ባወጣኋቸው ቀን ለአባቶቻችሁ ያዘዝሁትን፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ አድርጉ፤ እንዲሁም እናንተ ሕዝብ ትሆኑኛላችሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ” ያልሁትን ቃሌን ስሙ። 5ይህም ዛሬ እንደ ሆነ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣቸው ዘንድ ለአባቶቻችሁ የማልሁትን መሐላ አጸና ዘንድ ነው። እኔም፥ “አቤቱ! ጌታ ሆይ! ይሁን” ብዬ መለስሁለት።
6እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፥ “ይህችን ቃል ሁሉ በይሁዳ ከተሞችና በኢየሩሳሌም አደባባይ ተናገር፤ እንዲህም በል፦ የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ስሙ፤ አድርጉትም። 7አባቶቻችሁን ከግብፅ ምድር ከአወጣሁበት ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ፥ በማለዳ ተነሥቼ እያስጠነቀቅሁ፦ ቃሌን ስሙ በማለት አስጠንቅቄአቸው ነበር።#ምዕ. 11 ቍ. 7 በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 8እነርሱ ሁሉ ግን በክፉ ልባቸው እልከኝነት ሄዱ እንጂ አልሰሙም፤ ጆሮአቸውንም አላዘነበሉም፤ ስለዚህ ያዘዝኋቸውን እነርሱም ያላደረጉትን የዚህን ቃል ኪዳን ቃል ሁሉ አመጣሁባቸው።”
9እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ በይሁዳ ሰዎችና በኢየሩሳሌም በሚኖሩ ዘንድ አድማ ተገኝቶአል። 10ቃሌን ይሰሙ ዘንድ እንቢ ወደ አሉ ወደ አባቶቻቸው ኀጢአት ተመለሱ፥ ያመልኩአቸውም ዘንድ እንግዶችን አማልክት ተከተሉ፤ የእስራኤል ቤትና የይሁዳ ቤት ከአባቶቻቸው ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን አፈረሱ።
11ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ ሊያመልጡት የማይችሉትን ክፉ ነገር በዚህ ሕዝብ ላይ አመጣለሁ፤ ወደ እኔም ይጮኻሉ፤ እኔ ግን አልሰማቸውም። 12በይሁዳም ከተሞችና በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሄደው ወደሚያጥኑላቸው፥ በመከራቸው ጊዜ ከቶ ወደማያድኗቸው አማልክት ይጮኻሉ። 13ይሁዳ ሆይ! አማልክትህ እንደ ከተሞችህ ቍጥር እንዲሁ ናቸው፤ እንደ ኢየሩሳሌምም መንገዶች ቍጥር ለነውረኛ ነገር ለበዓል ታጥኑባቸው ዘንድ መሠዊያዎችን አድርጋችኋል። 14አንተም ስለዚህ ሕዝብ አትጸልይ፤ በመከራቸው ቀን ወደ እኔ በጮኹ ጊዜ አልሰማቸውምና ስለ እነርሱ አትጸልይ፤ በምልጃና በጸሎት አትማልድ።
15ወዳጄ በቤቴ ውስጥ ለምን ርኵሰትን አደረገች? ስእለት ወይም የተቀደሰ ሥጋ ክፋትሽን ከአንቺ ያስወግዳልን? ወይስ በእነዚህ ታመልጫለሽን? 16እግዚአብሔር ስምሽን፦ በመልካም ፍሬ የተዋበችና የለመለመች የወይራ ዛፍ ብሎ ጠራው፤ ከመቈረጥዋም ድምፅ የተነሣ በላይዋ እሳት ነደደባት፤ ቅርንጫፎችዋም ተሰብረዋል። 17ለበዓልም በማጠናቸው ያስቈጡኝ ዘንድ ለራሳቸው ስለ ሠሩአት ስለ እስራኤልና ስለ ይሁዳ ቤት ክፋት የተከለሽ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ክፉን ነገር ተናግሮብሻል።
ኤርምያስን ለመግደል የተደረገ ሤራ
18ጌታ ሆይ! አስታውቀኝ፤ እኔም አውቃለሁ፤ ያንጊዜም ሥራቸውን ገለጥህልኝ። 19እኔም ለመታረድ እንደሚነዳ እንደ የዋህ ጠቦት በግ ሆንሁ፤ እነርሱም በእንጀራው ዕንጨት እንጨምር#ዕብ. “ዛፉን ከፍሬው ጋር እንቍረጥ” ይላል። ስሙም ከእንግዲህ ወዲህ እንዳይታሰብ ከሕያዋን ምድር እናጥፋው ብለው ክፉ ምክርን እንዳሰቡብኝ አላወቅሁም ነበር። 20ኵላሊትንና ልብን የምትፈትን፥ በቅንም የምትፈርድ እግዚአብሔር ሆይ! ክርክሬን ገልጬልሃለሁና ከእነርሱ ፍረድልኝ። 21ስለዚህም፥ “በእጃችን እንዳትሞት በእግዚአብሔር ስም ትንቢት አትናገር” ብለው ነፍሴን ስለሚሹ ስለ አናቶት ሰዎች እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ 22ስለዚህ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ በመዓት እጐበኛቸዋለሁ፤ ጐበዛዝቶቻቸው በሰይፍ ይሞታሉ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውም በራብ ይሞታሉ፤ 23በምጐበኛቸውም ዓመት በዓናቶት ሰዎች ላይ ክፉ ነገር አመጣባቸዋለሁና ማንም ከእነርሱ የሚተርፍ የለም።
Currently Selected:
ትንቢተ ኤርምያስ 11: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ