ትንቢተ ሆሴዕ 8
8
የእስራኤል ሕዝብ ጣዖት በማምለካቸው መገሠጻቸው
1በብብታቸው እንደ መሬት፤#ዕብ. “መለከትን ወደ አፍህ አቅርብ” ይላል። በእግዚአብሔርም ቤት እንደ ንስር ይመጣል። ቃል ኪዳኔን ተላልፈዋልና፥ በሕጌም ላይ ዐምፀዋልና። 2አምላክ ሆይ! እኛ እስራኤል#“እስራኤል” የሚለው በዕብ. ብቻ። ዐወቅንህ ብለው ወደ እኔ ይጮኻሉ። 3እስራኤል ደግነቱን ጥሎአልና፤ ጠላትም ያሳድደዋልና። 4ራሳቸውን አነገሡ፤ ከእኔም ዘንድ አይደለም፤ አለቆችንም አደረጉ፤ እኔም አላወቅሁም፤ ለጥፋታቸውም ከብራቸውና ከወርቃቸው ጣዖታትን ለራሳቸው አደረጉ። 5ሰማርያ ሆይ! እምቦሳሽን መልሺ፤ ቍጣዬም በላያቸው ነድዶአል፤ እስከ መቼም ድረስ ንጹሕ ሊሆኑ አይችሉም። 6ይህ ደግሞ በእስራኤል ዘንድ ነው፤ ሠራተኛ ሠራው፤ እርሱም አምላክ አይደለም፤ ሰማርያ ሆይ! እንቦሳሽ ተቅበዝብዞአልና። 7ነፋስን ዘርተዋልና ዐውሎ ነፋስን አጨዱ፤ ለነዶአቸውም ኀይል የለውም፤ ከፍሬውም ዱቄት አይገኝም፤ ቢገኝም ጠላት ይበላዋል።#ዕብ. “እንግዶች ይበሉታል” ይላል።
8እስራኤል ተውጦአል፤ በአሕዛብም መካከል ዛሬ እንደ ግትቻ ዕቃ ሆኖአል። 9ለብቻውም እንደሚቀመጥ እንደ ምድረ በዳ አህያ ወደ አሦር ወጥተዋል፤ ኤፍሬምም እንደ ገና ለመለመ፤ እጅ መንሻንም ወደደ። 10ስለዚህ ለአሕዛብ አልፈው ይሰጣሉ፤ እኔም አሁን እቀበላቸዋለሁ፤ ንጉሥንና አለቆችንም ይቀቡ ዘንድ ፈጽመው ያንሣሉ።
11ኤፍሬም መሠዊያን አብዝቶአልና የወደደው መሠዊያ ለኀጢአት ሆነበት። 12ብዙ ሕጎችን እጽፍለታለሁ፤ ነገር ግን ሥርዐቱና የተወደደው መሠዊያው እንደ እንግዳ ነገር ተቈጠሩ። 13መሥዋዕትንም ቢሠዉ፥ ሥጋንም ቢበሉ፤ እግዚአብሔር አይቀበላቸውም፤ አሁንም በደላቸውን ያስባል፤ በኀጢአታቸውም ይበቀላቸዋል፤ እነርሱም ወደ ግብፅ ይመለሳሉ፤ በአሦርም ርኩስ ነገርን ይበላሉ። 14እስራኤል ፈጣሪውን ረስቶአል፤ መስገጃዎችንም ሠርቶአል፤ ይሁዳም የተመሸጉትን ከተሞች አብዝቶአል፤ እኔ ግን በከተሞች ላይ እሳትን እሰድዳለሁ፤ መሠረቶቻቸውንም ትበላለች።
Currently Selected:
ትንቢተ ሆሴዕ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ