መጽሐፈ ዕዝራ 9
9
1ይህም ከተፈጸመ በኋላ የሕዝቡ አለቆች ወደ እኔ ቀርበው፥ “የእስራኤል ሕዝብ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ እንደ ከነዓናውያን፥ እንደ ኬጤዎናውያን፥ እንደ ፌርዜዎናውያን፦ እንደ ኢያቡሴዎናውያን፥ እንደ አሞናውያን፥ እንደ ሞዓባውያን፥ እንደ ግብፃውያንና እንደ አሞራውያን ርኵሰት ያደርጋሉ እንጂ ከምድር አሕዛብ አልተለዩም፤ 2ለራሳቸውና ለልጆቻቸውም ሴቶች ልጆቻቸውን ወስደዋል፤ የተቀደሰውንም ዘር ከምድር አሕዛብ ጋር ደባልቀዋል፤ አስቀድሞም አለቆቹና ሹሞቹ በዚህ መተላለፍ መጀመሪያ ሆነዋል” አሉኝ። 3ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጐናጸፊያዬን ቀደድሁ፤ አዘንሁም፤ የራሴንና የጢሜንም ጠጕር ነጨሁ፤ ደንግጬም ተቀመጥሁ። 4ስለ ምርኮኞቹም መተላለፍ የእስራኤልን አምላክ ቃል የሚፈሩ ሁሉ ወደ እኔ ተሰበሰቡ፤ እኔም እስከ ሠርክ መሥዋዕት ድረስ ዐዝኜ ተቀመጥሁ።
5በሠርክም መሥዋዕት ጊዜ ልብሴና መጐናጸፊያዬ እንደ ተቀደደ ሆኖ ከመዋረዴ ተነሣሁ፤ በጕልበቴም ተንበርክኬ ወደ አምላኬ ወደ እግዚአብሔር እጄን ዘረጋሁ። 6እንዲህም አልሁ፥ “አምላኬ ሆይ፥ ኀጢአታችን በራሳችን ላይ በዝቶአልና፥ በደላችንም ወደ ሰማይ ከፍ ብሎአልና አምላኬ ሆይ፥ ፊቴን ወደ አንተ አነሣ ዘንድ አፍራለሁ፤ እፈራማለሁ። 7ከአባቶቻችን ዘመን ጀምረን እስከ ዛሬ ድረስ እጅግ በድለናል፤ ስለ ኀጢአታችን እኛና ልጆቻችን#“ልጆቻችን” የሚለው በዕብ. የለም። ንጉሦቻችን፥ ካህናቶቻችንም ለሰይፍና ለምርኮ፥ ለብዝበዛና ለዕፍረት በአሕዛብ ነገሥታት እጅ ተጣልን፤ እስከ ዛሬም ድረስ በፊታችን እፍረት እንኖራለን። 8አሁንም ቅሬታ ይተዉልን ዘንድ፥ በተቀደሰውም ስፍራው ኀይልን#ዕብ. “ችንካር” ይላል። ይሰጠን ዘንድ፥ አምላካችንም ዐይናችንን ያበራ ዘንድ፥ በባርነትም ሳለን ጥቂት የሕይወት መታደስን ይሰጠን ዘንድ ለጥቂት ጊዜ ከአምላካችን ከእግዚአብሔር ጥቂት ዕረፍትን አገኘን። 9ባሪያዎቹ ነንና፥ አምላካችን ግን በባርነታችን አልተወንም፤ ቀለባችንን ይሰጡን ዘንድ፥ የአምላካችንንም ቤት ከፍ ከፍ ያደርጉ ዘንድ፥ የተፈታውንም ይጠግኑ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌምም ቅጥር ያደርጉልን ዘንድ በፋርስ ነገሥታት ፊት ሞገስን ሰጠን። 10አሁንስ ከዚህ በኋላ ምን እንላለን? አምላካችን ሆይ፥ ትእዛዝህን ትተናልና። 11በባሮችህ በነቢያት እጅ ያዘዝሃትን እንዲህ ስትል፦ ትወርሱአት ዘንድ የምትገቡባት ምድር በምድር አሕዛብ ርኵሰት የረከሰች ናት፤ በርኵሰታቸውም ከዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ መልተዋታል። 12አሁንም ትበረቱ ዘንድ፥ የምድሩንም ፍሬ ትበሉ ዘንድ፥ ልጆቻችሁም ለዘለዓለም ይወርሱአት ዘንድ፥ ሴቶችን ልጆቻችሁን ለወንዶች ልጆቻቸው አትስጡ፤ ሴቶች ልጆቻቸውንም ለወንዶች ልጆቻችሁ አትውሰዱ፤ ሰላማቸውንና ደኅንነታቸውንም ለዘለዓለም አትሹ። 13ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኀጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም፤ ነገር ግን ድኅነትን ሰጠኸን። 14ትእዛዝህን እናፈርስ ዘንድ ተመልሰናልና፥ ርኵስ ሥራ ከሚሠሩ ከእነዚህ አሕዛብ ጋርም ተጋብተናልና ከእኛ ከሞት የሚያመልጥ እስከማይኖር ድረስ ፈጽመህ አትቈጣን። 15አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፥ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል የለም።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ 9: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ