የምርኮ ልጆች ሁሉም ወደ ኢየሩሳሌም ይሰበሰቡ ዘንድ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌም ዐዋጅ ነገረ “እስከ ሦስት ቀን ድረስ የማይመጣ ሁሉ እንደ ሽማግሎችና እንዳለቆች ምክር ከብቱ ሁሉ ይበዝበዝ፤ እርሱም ከምርኮው ጉባኤ ይለይ” ብሎ ዐዋጅ አስነገረ። ሦስት ቀንም ሳያልፍ በዘጠነኛው ወር ከወሩም በሃያኛው ቀን የይሁዳና የብንያም ሰዎች ሁሉ በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። ሕዝቡም ሁሉ ስለዚህ ነገርና ስለ ታላቁ ዝናብ እየተንቀጠቀጡ በእግዚአብሔር ቤት ፊት ባለው አደባባይ ተቀመጡ። ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ፥ “ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። አሁንም የአባቶቻችንን አምላክ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ” አላቸው። ጉባኤውም ሁሉ በታላቅ ድምፅ መልሰው እንዲህ አሉ፥ “እንደ ተናገርኸን እናደርግ ዘንድ ይገባናል። ነገር ግን የሕዝቡ ቍጥር ብዙ ነው፤ ጊዜውም የትልቅ ዝናብ ጊዜ ነው፤ በሜዳም ልንቆም አንችልም፤ በዚህም ነገር እጅግ በድለናልና ይህ ሥራ የአንድ ወይም የሁለት ቀን ሥራ አይደለም። አለቆቻችንም በጉባኤው ፋንታ ሁሉ ይቁሙ፤ ስለዚህም ነገር የአምላካችን ጽኑ ቍጣ ከእኛ ይመለስ ዘንድ እንግዶቹን ሴቶች ያገቡት በከተሞቻችን ያሉት ሁሉ በተቀጠረው ጊዜ ይምጡ፤ ከእነርሱም ጋር የከተማው ሁሉ ሽማግሌዎችና ፈራጆች ይምጡ።” ነገር ግን የአሣሄል ልጅ ዮናታንና የቴቁዋ ልጅ የሐዝያ ስለዚህ ነገር ከእኔ ጋር ናቸው፤ ሜሱላምና ሌዋዊው ሰባታይም ይረዱአቸው ነበር። የስደተኞቹም ልጆች እንዲህ አደረጉ፤ ካህኑ ዕዝራ፥ የአባቶችም ቤቶች አለቆች በየአባቶቻቸው ቤቶች ሁሉም በየስማቸው ተለዩ፤ በዐሥረኛውም ወር በመጀመሪያው ቀን ነገሩን ይመረምሩ ዘንድ ተቀመጡ። እስከ መጀመሪያውም ወር እስከ መጀመሪያው ቀን ድረስ ሠርተው እንግዶቹን ሴቶች ያገቡትን ሰዎች ሁሉ መርምረው ጨረሱ።
መጽሐፈ ዕዝራ 10 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዕዝራ 10:7-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos