ሙሴም ሄደ፤ ወደ አማቱ ወደ ዮቶርም ተመለሰ፥ “እስከ ዛሬ በሕይወት እንደ አሉ አይ ዘንድ ተመልሼ ወደ ግብፅ ወደ ወንድሞች እሄዳለሁ” አለው። ዮቶርም ሙሴን፥ “በደኅና ሂድ” አለው። ከብዙ ዘመንም በኋላ የግብፅ ንጉሥ ሞተ። እግዚአብሔርም ሙሴን በምድያም፥ “ነፍስህን የሚሹአት ሰዎች ሁሉ ሞተዋልና ተመልሰህ ወደ ግብፅ ሂድ” አለው። ሙሴም ሚስቱንና ልጆቹን ወሰደ፤ በአህዮች ላይም አስቀመጣቸው፤ ወደ ግብፅም ሀገር ተመለሰ፤ ሙሴም ያችን የእግዚአብሔርን በትር በእጁ ይዞ ሄደ። እግዚአብሔርም ሙሴን አለው፥ “ወደ ግብፅ ተመልሰህ ስትሄድ በእጅህ ያደረግሁትን ተአምራቴን ሁሉ በፈርዖን ፊት ታደርገው ዘንድ ተመልከት፤ እኔ ግን ልቡን አጸናዋለሁ፤ ሕዝቡንም አይለቅቅም። አንተ ግን ፈርዖንን እንዲህ ትለዋለህ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስራኤል የበኵር ልጄ ነው፤ ያመልኩኝ ዘንድ ሕዝቤን ልቀቅ አልሁህ፤ አንተም ልትለቅቃቸው ባትፈቅድ፤ እኔ የበኵር ልጅህን እንደምገድል ዕወቅ።” እንዲህም ሆነ፤ በመንገድ ላይ በአደረበት ስፍራ የእግዚአብሔር መልአክ ተገናኘው፤ ሊገድለውም ፈለገ። ሚስቱ ሲፓራም ባልጩት ወሰደች፤ የልጅዋንም ሸለፈት ገረዘች፤ “ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላ ከእግሩ በታች ወደቀች። ከእርሱም ሄደ፤ የዚያ ጊዜ፥ “ይህ የልጄ የግርዛቱ ደም ስለ እርሱ ፈንታ ይሁን” ብላለችና። እግዚአብሔርም አሮንን አለው፥ “ሄደህ በምድረ በዳ ሙሴን ተገናኘው፤” ሄዶም በእግዚአብሔር ተራራ ተገናኘው፤ እርስ በርሳቸውም ተሳሳሙ። ሙሴም እግዚአብሔር የላከውን ቃል ሁሉ፥ የአዘዘውንም ተአምራት ሁሉ ለአሮን ነገረው። ሙሴና አሮንም ሄዱ፤ የእስራኤልንም ልጆች ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰቡ። አሮንም እግዚአብሔር ለሙሴ የነገረውን ቃል ሁሉ ተናገረ፤ ተአምራቱንም በሕዝቡ ፊት አደረገ። ሕዝቡም አመኑ፤ ደስም አላቸው፤ እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች ጐብኝቶአልና፤ ጭንቀታቸውንም አይቶአልና፤ ሕዝቡም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሰገዱ።
ኦሪት ዘፀአት 4 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 4:18-31
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos