እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ። ክርስቶስ እንደ ወደዳችሁ፥ ራሱንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ የሚሆን መሥዋዕትና ቍርባን አድርጎ እንደ ሰጠላችሁ በፍቅር ተመላለሱ። ነገር ግን ለቅዱሳን እንደሚገባቸው፥ ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም ቅሚያ አይሰማባችሁ። የሚያሳፍር ነገርም፥ የስንፍና ነገርም፥ ወይም የማይገባ የዋዛ ነገር በእናንተ ዘንድ አይሁን፤ ማመስገን ይሁን እንጂ። ሴሰኛ፥ ወይም ኀጢአተኛ፥ ወይም ቀማኛ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ሁሉ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ መንግሥት ዕድል ፋንታ እንደሌለው ይህን ዕወቁ። በከንቱ ነገርም የሚያስታችሁ አይኑር፤ በእርሱ ምክንያት በከሓዲዎች ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መዓት ይመጣልና። እንግዲህ አትምሰሉአቸው። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ ዛሬ ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችኋል። እንግዲህስ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ። የብርሃን ፍሬው በጎ ሥራና እውነት፥ ቅንነትም ሁሉ ነውና። እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ። የሥራ ፍሬ ከሌላቸው፥ ሁለንተናቸውም ጨለማ ከሆነ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ገሥጹአቸው እንጂ። በስውር የሚሠሩት ሥራ ለመናገር የሚያሳፍር ነውና። ነገር ግን በብርሃን የተገለጠ ሁሉ ይታወቃል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። “የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሎአልና። እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ። ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት። ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ። መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ። መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም። ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ።
ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:1-20
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos