ኤፌሶን 5:1-20
ኤፌሶን 5:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥ ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደ ሰጠ በፍቅር ተመላለሱ። ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፥ ይልቁን ምስጋና እንጂ። ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኵስ ወይም የሚመኝ እርሱም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ። እንግዲህ ከእነርሱ ጋር ተካፋዮች አትሁኑ፤ ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን እየመረመራችሁ፥ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳ ነውር ነውና፤ ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። ስለዚህ፦ አንተ የምትተኛ ንቃ ከሙታንም ተነሣ ክርስቶስም ያበራልሃል ይላል። እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።
ኤፌሶን 5:1-20 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ። ክርስቶስ እንደ ወደዳችሁ፥ ራሱንም ለእግዚአብሔር በጎ መዓዛ የሚሆን መሥዋዕትና ቍርባን አድርጎ እንደ ሰጠላችሁ በፍቅር ተመላለሱ። ነገር ግን ለቅዱሳን እንደሚገባቸው፥ ዝሙትና ርኵሰት ሁሉ ወይም ቅሚያ አይሰማባችሁ። የሚያሳፍር ነገርም፥ የስንፍና ነገርም፥ ወይም የማይገባ የዋዛ ነገር በእናንተ ዘንድ አይሁን፤ ማመስገን ይሁን እንጂ። ሴሰኛ፥ ወይም ኀጢአተኛ፥ ወይም ቀማኛ፥ ወይም ጣዖትን የሚያመልክ ሁሉ በእግዚአብሔር ልጅ በክርስቶስ መንግሥት ዕድል ፋንታ እንደሌለው ይህን ዕወቁ። በከንቱ ነገርም የሚያስታችሁ አይኑር፤ በእርሱ ምክንያት በከሓዲዎች ልጆች ላይ የእግዚአብሔር መዓት ይመጣልና። እንግዲህ አትምሰሉአቸው። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁና፥ ዛሬ ግን በጌታችን ብርሃን ሆናችኋል። እንግዲህስ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ። የብርሃን ፍሬው በጎ ሥራና እውነት፥ ቅንነትም ሁሉ ነውና። እግዚአብሔርንም ደስ የሚያሰኘውን መርምሩ። የሥራ ፍሬ ከሌላቸው፥ ሁለንተናቸውም ጨለማ ከሆነ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ገሥጹአቸው እንጂ። በስውር የሚሠሩት ሥራ ለመናገር የሚያሳፍር ነውና። ነገር ግን በብርሃን የተገለጠ ሁሉ ይታወቃል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። “የተኛህ ንቃ ከሙታንም ተለይተህ ተነሥ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ብሎአልና። እንግዲህ እንደ ዐዋቂዎች እንጂ እንደ አላዋቂዎች ሳይሆን እንዴት እንደምትመላለሱ በጥንቃቄ ዕወቁ። ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁት። ስለዚህም ሰነፎች አትሁኑ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ አስተውሉ እንጂ። መዳራት ነውና ወይን በመጠጣት አትስከሩ፤ መንፈስ ቅዱስን ተመሉ እንጂ። መዝሙርንና ምስጋናን፥ የተቀደሰ ማሕሌትንም አንብቡ፤ በልባችሁም ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ዘምሩም። ዘወትርም ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ለእግዚአብሔር አብ ምስጋና አቅርቡ።
ኤፌሶን 5:1-20 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ ክርስቶስ እንደ ወደደን ራሱንም ስለ እኛ መልካም መዐዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ተመላለሱ። ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኩሰት ወይም የሥሥት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና። የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰግኑ ሁኑ። ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ፣ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው። ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ። ፍሬ ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር ምንም ዐይነት ግንኙነት አይኑራችሁ፤ ይልቁን ግለጡት፤ በድብቅ የሚሠሩትን ነገር መናገር ራሱ አሳፋሪ ነውና። ብርሃን የበራበት ነገር ሁሉ ግልጽ ሆኖ ይታያል፤ ምክንያቱም ሁሉን ነገር እንዲታይ የሚያደርገው ብርሃን ነውና፤ ስለዚህም፣ “አንተ የተኛህ ንቃ፤ ከሙታን ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሏል። እንግዲህ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኞች እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ። ቀኖቹ ክፉ ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ ሞኞች አትሁኑ፤ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ። በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይህ ብክነት ነውና። በመዝሙርና በውዳሴ፣ በመንፈሳዊም ዝማሬ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በልባችሁ ለጌታ ተቀኙ፤ አዚሙም። በዚህም እግዚአብሔር አብን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር ሁልጊዜ አመስግኑ።
ኤፌሶን 5:1-20 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ እንደ ተወዳጅ ልጆች እናንተም የእግዚአብሔርን አርአያ ተከተሉ። ክርስቶስ እንደ ወደደንና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ መልካም መዓዛ ያለው መባና መሥዋዕት አድርጎ ሕይወቱን ስለ እኛ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም በፍቅር ኑሩ። እንዲህ ዐይነቱ ነገር ለክርስቲያኖች ስለማይስማማ ዝሙት ወይም ማናቸውንም ዐይነት ርኲሰት ወይም ንፍገት ማድረግ ይቅርና ወሬው እንኳ ሊሰማባችሁ አይገባም። ይልቅስ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቅርቡ እንጂ የሚያስቀይምና የሞኝነት አነጋገር፥ ወይም የፌዝን ነገር መናገር አይገባችሁም፤ እንዲህ ያለ ነገር ለእናንተ ተስማሚ አይደለም። አመንዝራም ቢሆን፥ ማናቸውንም የርኲሰት ሥራ የሚያደርግ ቢሆን፥ ወይም ጣዖት እንደ ማምለክ የሆነ ስግብግብነት ቢሆን፥ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት እንደማያገኝ ዕወቁ። በእነዚህ ነገሮች ምክንያት በማይታዘዙ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ስለሚመጣ ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ። ስለዚህ ከእነዚህ ከማይታዘዙ ሰዎች ጋር አትተባበሩ፤ ቀድሞ እናንተ በጨለማ ውስጥ ትኖሩ ነበር፤ አሁን ግን የጌታ ስለ ሆናችሁ ብርሃን ናችሁ ስለዚህ በብርሃን እንደሚኖሩ ሰዎች ተመላለሱ። የደግነት ሁሉ፥ የጽድቅና የእውነት ፍሬ የሚገኘው ከብርሃን ነውና። ስለዚህ ጌታን ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደ ሆነ መርምሩ። ወደ ብርሃን አውጥታችሁ አጋልጡት እንጂ ፍሬቢስ ከሆነ ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ። በጨለማ የሚኖሩ ሰዎች በስውር ስለሚያደርጉት ነገር መናገር እንኳ ያሳፍራል። ሁሉ ነገር ወደ ብርሃን ሲወጣ እውነተኛ መልኩ ግልጥ ሆኖ ይታያል። በግልጥ የሚታይ ሁሉ ብርሃን ነው፤ ስለዚህ፦ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ! ከሙታን ተለይተህ ተነሥ! ክርስቶስም ያበራልሃል” ተብሎአል። እንግዲህ እንዴት እንደምትኖሩ በጥንቃቄ አስተውሉ፤ እንደ ጥበበኞች እንጂ እንደ ሞኞች አትኑሩ። ይህ ዘመን ክፉ ስለ ሆነ በማናቸውም አጋጣሚ ጊዜ ተጠቀሙ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደ ሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። ወደ ጥፋት የሚመራችሁ ስለ ሆነ በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ ይልቅስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ። በመዝሙርና በውዳሴ፥ በመንፈሳዊም ዜማ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ በውዳሴና በመዝሙር በሙሉ ልባችሁ ጌታን አመስግኑ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር እግዚአብሔር አብን ዘወትር አመስግኑ።
ኤፌሶን 5:1-20 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ፤ ክርስቶስም እንዳፈቀራችሁ፥ ስለ እናንተም ለእግዚአብሔር መልካም መዓዛ ያለው መባንና መሥዋዕት አድርጎ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ፥ በፍቅር ተመላለሱ። ለቅዱሳን የማይገባው፥ ማንኛውም የዝሙትና የርኩሰት፥ ወይም የስስት ነገር ሁሉ በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያጸይፍ ነገር፥ ተራና የእንዝህላል ንግግርም ፈጽመው በመካከላችሁ አይኑሩ፤ ይልቁን አመስጋኞች ሁኑ። ይህን እወቁ፤ አመንዝራም ቢሆን ወይም ርኩስ ወይም ስስታም ማለትም ጣዖትን የሚያመልክ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ከዚህ የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና ማንም በከንቱ ንግግር አያታላችሁ። ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ፤ እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ፤ የብርሃን ፍሬ በበጎነትና በጽድቅ በእውነትም ሁሉ ነውና፤ ለጌታ ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ። ፍሬም ከሌለው ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፤ ይልቁን ግለጡት፤ እነርሱ በስውር ስለሚያደርጉት መናገር እንኳን ያስነውራል። ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና። ስለዚህ “አንተ የምታንቀላፋ ንቃ፤ ከሙታንም ተነሣ፤ ክርስቶስም ያበራልሃል፤” ተብሏል። እንግዲህ ስለ አኗኗሯችሁ በጥንቃቄ ተጠበቁ፥ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው አይሁን፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በሚገባ ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ። መንፈስ ይሙላባችሁ እንጂ ብክነት እንደ ሆነው በወይን ጠጅ አትስከሩ፤ በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊም ቅኔ እርስ በርሳችሁ ተነጋገሩ፤ ለጌታ በልባችሁ ተቀኙና ዘምሩ፤ ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ።