መጽሐፈ ባሮክ 3
3
1“አቤቱ! ነግሠህ የምትኖር የእስራኤል አምላክ ሆይ! የተራበች ነፍስ፥ ያዘነችም ነፍስ ወደ አንተ ጮኸች። 2አቤቱ! ሰምተህ ይቅር በላት፤ በፊትህ በድለናልና። 3አንተ ለዘለዓለሙ የምትኖር ነህና፥ እኛ ግን ለዘለዓለሙ እንጠፋለንና።
4በሁሉ ላይ የምትነግሥ#“በሁሉ ላይ የምትነግሥ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የእስራኤል አምላክ አቤቱ! የሙታን የእስራኤልን፥ በፊትህም የበደሉ፥ የአምላካቸውንም ቃል ያልሰሙ የልጆቻቸውን ጸሎት ስማ። 5ክፉ ነገርም ተከተለን፤ የአባቶቻችንንም ኀጢአት አላሰብንም፤ በዚህም ወራት እጅህንና ስምህን ዐስብ። 6አንተ እግዚአብሔር አምላካችን ነህና አቤቱ! እናመሰግንሃለን። 7ስለዚህም ስምህን እንጠራ ዘንድ፥ ባስማረክኸንም ቦታ እናመሰግንህ ዘንድ መፈራትህን በልቡናችን አሳደርህ። በፊትህ የበደሉ የአባቶቻችንን ክፋት ሁሉ ከልባችን አርቀናልና። 8አቤቱ አምላካችን! እነሆ ዛሬ፦ ከአንተ እንደ ራቁ አባቶቻችን ክፋት ሁሉ ለውርደት፥ ለርግማንና ለፍዳ በበተንኸን ምርኮ ውስጥ ነን።” 9እስራኤል ሆይ፥ የሕይወትን ትእዛዝ ስማ፥ የጥበብንም ምክር አድምጥ። 10እስራኤል ምንድን ነው? በጠላትስ ሀገር ለምን ይኖራል? 11በባዕድ ሀገርስ ለምን ጠፋ? ከሬሳዎችስ ጋር ለምን ረከሰ? ወደ መቃብር ከወረዱት ጋርስ ለምን ተቈጠረ? 12የሕይወትን ምንጭ ተውህ? 13በእግዚአብሔርስ መንገድ ብትሄድ ለዘለዓለም በሰላም በኖርህ ነበር! 14ተማር፥ ጥበብ ከየት ነው? ኀይልስ ከየት ነው? ምክርና ዕውቀትስ ከየት ናቸው? ለብዙ ዘመናት መኖርስ ከየት ነው? የዐይኖች ብርሃንና ሰላም ከየት ናቸው? 15የጥበብ ሀገሯን ማን አገኘ? ወደ መዛግብትዋስ ማን ገባ? 16የምድረ በዳ አውሬዎችን የገዙ የአሕዛብ አለቆች ወዴት ናቸው? 17በሰማይ አዕዋፍም የሚጫወቱ ሰዎች የሚታመኑበት ብርና ወርቅን የሚሰበስቡ፤ ለመሰብሰባቸውም ወሰን የሌላቸው የአሕዛብ አለቆች ወዴት ናቸው? 18ብርን የሚያነጥሩ ይተጋሉና፥ ለሥራቸውም ምርመራ የለውም። 19አለቁ፤ ወደ መቃብርም ወረዱ፤ ስለ እነርሱም ሌሎች ተተኩ።
20ታናናሾች ብርሃንን አዩ፤ በምድራቸውም ኖሩ፤ የጥበብን መንገድ ግን አላወቁም። 21ፍለጋውንም አላገኙም፤ አልተቀበሉአትም፤ ልጆቻቸውም ከመንገዳቸው ራቁ። 22የከነዓን ሰዎች አልሰሙም፤ የቴምናም ሰዎች አላዩም። 23በምድር ጥበብን የሚፈልጓት የአጋር ልጆችም የሚጫወቱባት፥ ዕውቀትንም የሚፈልጓት፥ የመርያንና የቴምና ነጋዴዎችም የጥበብን ጐዳና አላወቁም፤ ፍለጋዋንም አላስተዋሉም። 24እስራኤል ሆይ! የእግዚአብሔር ቤት እንዴት ታላቅ ነው! ቦታውም እንዴት ሰፊ ነው! ፍጻሜ የለውም፤ መለኪያም የለውም። 25ታላቅ ነው፤ ፍጻሜም የለውም፤ ላይኛውም መለኪያ የለውም። 26ከጥንት ጀምሮ ቁመታቸው ረዥም የሆነ፥ ጦርነትንም የሚያውቁ ረዐይት የሚባሉ በዚያ ነበሩ። 27እነዚህን እግዚአብሔር አልመረጣቸውም፤ የዕውቀት መንገድንም አልሰጣቸውም። 28ጥበብ አልነበራቸውምና ጠፉ፤ በድፍረታቸውም ጠፉ። 29ወደ ሰማይ የወጣና የያዛት፤ ከደመናትም ያወረዳት ማነው? 30ባሕሩን ተሻግሮ ያገኛት፥ በቀይ ወርቅስ ያመጣት ማነው? 31መንገድዋን የሚያውቅ፥ ፍለጋዋንም የሚያስብ የለም። 32ሁሉን የሚያውቅ ያውቃታል፤ በጥበቡም አገኛት። ምድርን የፈጠረ ለዘለዓለም በእንስሳት ሞላት። 33ብርሃኑን ይልካል፤ እርሱም ይሄዳል፤ እንደ ገናም ይጠራዋል፤ በፍርሃትም ይታዘዘዋል። 34ከዋክብትም በየጊዜያቸው ያበራሉ፤ ደስም ይላቸዋል። 35ይጠራቸዋል፤ እነርሱም፦ መጣን ይላሉ። ለፈጠራቸውም በደስታ ያበራሉ። 36እርሱን የሚመስል ሌላ የለምና አምላካችን ነው ይላሉ። 37የጥበብን መንገድ ሁሉ እርሱ አገኛት፤ ለባለሟሉ ለያዕቆብ፥ ለወዳጁም ለእስራኤል ሰጠው። 38ከዚህ በኋላ በምድር ተገለጠ፤ እንደ ሰውም ሆነ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ