መጽሐፈ ባሮክ 4
4
1የዘላለም ሕግ የሆነ የእግዚአብሔር የትእዛዙ መጽሐፍ ይህ ነው፤ የሚጠብቋትም ሁሉ ይኖራሉ፤ የሚተዉኣት ግን ይሞታሉ። 2ያዕቆብ! ተመልሰህ ያዛት፤ በብርሃንዋም ሂድ። 3ክብርህን ለባዕድ አትስጥ፤ የሚሻልህንም ለሌላ ወገን አትስጥ። 4የአምላካችን የእግዚአብሔር ምሕረት በእኛ ታውቋልና እኛ እስራኤል ብፁዓን ነን።
መጽናናት ለእስራኤል
5ወገኖች ተጽናኑ፤ እስራኤልም አስቡ። 6ለጥፋት ያይደለ ለሌላ ወገን ተሽጣችሁ ነበር፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን ስላስቈጣችሁት ለጠላቶቻችሁ ተላልፋችሁ ተሰጥታችሁ ነበር። 7ለእግዚአብሔር ያይደለ ለአጋንንት በመሠዋታችሁ ፈጣሪያችሁን ለመዓት አነሳሳችሁት። 8ያሳደጋችሁን የዘለዓለም አምላካችሁንም ረስታችሁታልና፥ ሞግዚታችሁን ኢየሩሳሌምንም አሳዝናችኋታልና። 9የመጣባችሁን የእግዚአብሔርን መቅሠፍት ባየች ጊዜ እንዲህ አለች፦ የጽዮን ስደተኞች ስሙ፤ እግዚአብሔር ጽኑፅ ልቅሶን አምጥቶብኛልና። 10ዘለዓለማዊ አምላክ ያመጣባቸውን የወንዶች ልጆችንና የሴቶች ልጆችን መማረክ አይቻለሁና 11በደስታ አሳድጊያቸው ነበር፤ ነገር ግን በልቅሶና በኀዘን ሸኘኋቸው። 12በብዙዎች ዘንድ የተጣልሁ በሆንሁ በእኔ በመበለቲቱ ደስ የሚለው አይኑር፤ ከእግዚአብሔር ሕግ ርቀዋልና። 13ትእዛዙንም አላወቋትም፤ በእግዚአብሔርም በትእዛዙ መንገድ አልተመላለሱም፤ በምክሩም ፍለጋ ወደ ጽድቁ አልገቡም።
14የጽዮን ስደተኞች ይምጡ፤ ዘለዓለማዊው አምላክ ያመጣባቸውን የወንዶች ልጆችንና የሴቶች ልጆችንም ምርኮ ያስቡ። 15የማያፍርና ቋንቋው ልዩ የሆነ ሕዝብን ከሩቅ አምጥቶባቸዋልና፤ ሽማግሌውን አላከበሩምና፥ ለሕፃናቱም አልራሩምና። 16የመበለትነቷንም የተወደዱ ልጆች ነጠቁ፤ ከሴቶች ልጆችዋም ለይተው ብቻዋን አስቀሩአት። 17ነገር ግን እኔ ምን ረዳችኋለሁ? 18ክፉ ነገርን ያመጣባችሁ እርሱ ከጠላቶቻችሁ እጆች ያወጣችኋልና። 19ልጆች! መንገዳችሁን ሂዱ፤ መንገዳችሁን ሂዱ፤ እኔ የተፈታች ምድረ በዳ ሁኛለሁና። 20የሰላም ልብሴን አወለቅሁ፤ የመከራዬንም ማቅ ለበስሁ፤ በዘመኔም ወደ ዘለዓለማዊው አምላክ እጮሃለሁ፤
21ልጆች ተጽናኑ፤ ወደ አምላክም ጩኹ፤ ከጠላቶቻችሁ እጅና አገዛዝ ያወጣችኋል። 22ከዘለዓለማዊው አምላክ ዘንድ ድኅነታችሁን ተስፋ አድርጌአለሁና። ከዘለዓለማዊው መድኀኒታችን ዘንድ ፈጥኖ ስለሚመጣላችሁ ምሕረትም ደስታ ከቅዱሱ መጣልኝ፤ 23ከኀዘንና ከልቅሶ ጋር ሸኝቻችኋለሁና፤ ነገር ግን እግዚአብሔር እናንተን በደስታና በሐሤት ለዘለዓለም ይመልስልኛል። 24የጽዮን ጎረቤቶች መማረካችሁን እንዳዩ፥ እንዲሁም በታላቅ ክብርና በዘለዓለማዊው አምላክ ብርሃን ከእግዚአብሔር ዘንድ የምትመጣላችሁን ድኅነታችሁን ፈጥነው ያያሉ።
25ልጆች! ከእግዚአብሔር ዘንድ የመጣባችሁን ቍጣ በትዕግሥት ተቀበሉ፤ ጠላቶቻችሁ አሳድደዋችኋልና ውድቀታቸውን ፈጥናችሁ ታያላችሁ፤ በራሳቸውም ላይ ትወጣላችሁ። 26ቅምጥሎች በሻካረው መንገድ ሄዱ፤ ጠላቶችም እንደ ተዘረፉ በጎች ነጠቋቸው። 27ልጆች! ተጽናኑ፤ ወደ አምላክም ጩኹ፤ የወሰዳችሁ እርሱ ያስባችኋል። 28ከእግዚአብሔር ትርቁ ዘንድ ፈቃዳችሁ እንደ ሆነ እንዲሁ ዐሥር ጊዜ ወደኋላ ተመልሳችሁ ትፈልጉታላችሁ፤ 29ይህን መቅሠፍት ያመጣባችሁ እርሱ ዘለዓለማዊ ደስታን ከድኅነታችሁ ጋር ዳግመኛ ያመጣላችኋል።
የኢየሩሳሌም ረድኤት እንደ ተረጋገጠ
30ኢየሩሳሌም ተጽናኚ፤ ስም ያወጣልሽ እርሱ ያጽናናሻል። 31መከራ ያጸኑብሽና በውድቀትሽም ደስ ያላቸው ይጐሰቍላሉ። 32ልጆችሽን የገዙ፥ ልጆችሽንም ማርከው የወሰዱ ከተሞች ይጐሰቍላሉ። 33በጥፋትሽ ደስ እንደ አላት፥ በውድቀትሽም ሐሤት እንደ አደረገች እንዲሁ በራስዋ ጥፋት ታዝናለች። 34ብዙ ደስታዋንም ከእርስዋ አስወግዳለሁ፤ ደስታዋም ወደ ኀዘን ይመለሳል። 35እሳት ከዘለዓለማዊው አምላክ ለረዥም ዘመን ይመጣባታልና ለብዙ ዘመንም የአጋንንት ማደሪያ ትሆናለችና። 36ኢየሩሳሌም ወደ ምሥራቅ ተመልከች ከአምላክሽ ከእግዚአብሔር የመጣልሽ ደስታንም እዪ። 37እነሆ የላክሻቸው ልጆችሽ መጡ፤ በቅዱሱም ቃል ከምሥራቅና ምዕራብ ተሰበሰቡ፤ በእግዚአብሔርም ክብር ደስ ይላቸዋል።
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ