መጽሐፈ ባሮክ 2
2
1“አምላካችን በእኛና እስራኤልን በገዙ መሳፍንቶቻችን ላይ፥ በነገሥታቶቻችን ላይና በመኳንንቶቻችን ላይ፥ በይሁዳና በእስራኤልም ሁሉ ላይ የተናገረውን ቃሉን አጸና። 2በሙሴ ኦሪት እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም እንደ አደረገው ከሰማይ በታች ያልሆነ ክፉ ነገርን በእኛ ላይ ያመጣ ዘንድ፥ ቃሉን አጸና። 3በዚያ ወራት ሰው የወንዶች ልጆቹንና የሴቶች ልጆቹን ሥጋ በላ። 4እግዚአብሔር እነርሱን በበተነበት በዙሪአችን በአሉ አሕዛብ ዘንድ ለውርደትና ለመከራ ይሆኑ ዘንድ በዙሪያችን በአሉ ነገሥት ሁሉ እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 5ወራዶች ሆንን፤ የከበርንም አልሆንም፤ ለቃሉ ሳንታዘዝ አምላካችንን እግዚአብሔርን በድለናልና። 6ጽድቅ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ ለእኛና ለአባቶቻችን ግን እንደ ዛሬው ዕለት የፊት ኀፍረት ነው። 7በእኛ ላይ የደረሰውን ክፉ ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ተናግሮ ነበርና። 8እያንዳንዳችንም ከክፉ ልባችን መንገድ እንመለስ ዘንድ በአምላካችን በእግዚአብሔር ፊት አልጸለይንም። 9እግዚአብሔርም ለመከራ ተጋ፤ በእኛም ላይ አመጣው፤ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ባዘዘው ሥራው ሁሉ ጻድቅ ነውና። 10በፊታችን በሰጠን በእግዚአብሔርም ትእዛዝ እንሄድ ዘንድ ቃሉን አልሰማንም።
11“አሁንም በጸናች እጅ፥ በተአምርና በድንቅ ሥራ፤ በታላቅ ኀይልና በተዘጋጀች ክንድ ሕዝብህን ከግብፅ ምድር ያወጣህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው ለራስህ ታላቅ ስምን ያደረግህ የእስራኤል አምላክ ሆይ! 12በደልን፤ ክፉም አደረግን፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ! በሥርዐትህ ሁሉ ላይ የማይገባ ሥራን ሠራን። 13ቍጣህን ከእኛ አብርድ፤ እኛን በዚያ በበተንህበት በአሕዛብ ዘንድ ጥቂት ቀርተናልና። 14ጌታ ሆይ! ልመናችንንና ጸሎታችንን ስማ፤ ስለ ስምህም ስትል አድነን፤ በማረኩንም ሰዎች ፊት ሞገስን እናገኝ ዘንድ ስጠን፤ 15ምድር ሁሉ አንተ እግዚአብሔር አምላካችን እንደ ሆንህ ታውቅ ዘንድ፥ ስምህ በእስራኤል ላይና በወገኑ ላይ ተጠርቶአልና ። 16አቤቱ ከቤተ መቅደስህ ሁነህ ተመልከት፤ አቤቱ ጆሮህን ወደ እኛ አዘንብለህ ስማን።
17“ዐይኖችህን ገልጠህ ተመልከት፤ አቤቱ ነፍሳቸው ከሥጋቸው የተለየች በመቃብር የሚኖሩ ሙታን የሚያከብሩህና የሚያመሰግኑህ አይደሉምና። 18ነገር ግን አዝናና ተጨንቃ የምትኖር፥ በብዙ መከራም ያዘነች ሰውነትና የፈዘዙ ዐይኖች፥ የተራበችም ነፍስ ያመሰግኑሃል፤ አቤቱ ለጽድቅህም ይገዛሉ። 19አቤቱ አምላካችን በፊትህ ምሕረትን የለመንንህ እንደ አባቶቻችንና ነገሥታቶቻችን ጽድቅ አይደለምና። 20በባሪያዎችህ በነቢያት እጅ እንደ ተናገርህ መዓትህንና መቅሠፍትህን በእኛ ላይ ሰድደሃልና።
21“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ትከሻችሁን ዝቅ አድርጉ ለባቢሎንም ንጉሥ ተገዙ፤ ለአባቶቻችሁ በሰጠኋት ምድርም ትኖራላችሁ፤ 22የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙ፥ ለባቢሎንም ንጉሥ ባትገዙ፥ 23የደስታና የሐሤት ድምፅ፥ የወንድ ሙሽራና የሴት ሙሽራ ድምፅ ከይሁዳ ከተሞችና ከኢየሩሳሌም ውጭ ይጠፋል፤ ምድርም ሁሉ ከነዋሪዎች ምድረ በዳ ይሆናል። 24ቃልህን አልሰማንም፤ ለባቢሎንም ንጉሥ አልተገዛንም፤ የንጉሦቻችን ዐፅሞችና የአባቶቻችን ዐፅሞች ከቦታቸው እንደሚወጡ በባሮችህ ነቢያት እጅ የተናገርኸውም ደረሰብን።
25“እነሆ በቀን ሐሩርና በሌሊት ቍር ጣሏቸው፤ ተማረክን፤#“ተማረክን” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በቀጠናና በጦር፥ በቸነፈርም ክፉ ሞትን ሞትን። 26በእስራኤል ወገንና በይሁዳ ወገን ኀጢአት ምክንያት ስምህ የተጠራበትን መቅደስ እንደ ዛሬው ዕለት ጣልህ። 27ነገር ግን አቤቱ አምላካችን! እንደ ቸርነትህ ሁሉና እንደ ታላቁ ይቅርታህ ሁሉ አደረግህልን፤ 28በእስራኤል ልጆች ፊት ሕግህን ይጽፍ ዘንድ ባዘዝህባት ዕለት በአገልጋይህ በሙሴ እጅ እንዲህ ስትል እንደ ተናገርህ፥ 29ቃሌን በእውነት ባትሰሙ ይህች ብዛታችሁ እናንተን በበተንሁባቸው በአሕዛብ መካከል ወደ ጥቂትነት ትመለሳለች።
30“እንደማይሰሙኝም ዐወቅኋቸው፤ አንገተ ደንዳና ሕዝብ ናቸውና፤ በተሰደዱበትም ሀገር ወደ ፈቃዳቸው ይመለሳሉ። 31እኔም አምላካቸው እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ። ልብን፥ ለመስማትም ጆሮን እሰጣቸዋለሁ። 32ባስማረክኋቸውም ሀገር ያመሰግኑኛል፤ ስሜንም ያስባሉ። 33ከደንዳና ልባቸውና ከክፉ ሥራቸው ይመለሳሉ፤ በእግዚአብሔር ፊት የበደሉ የአባቶቻቸውንም መንገድ ያስባሉ። 34ለአባቶቻቸው ለአብርሃም፥ ለይስሐቅና ለያዕቆብም ወደ ማልሁላቸው ሀገር እመልሳቸዋለሁ፤ ይገዙአታልም፤ እኔም አበዛቸዋለሁ፤ እነርሱም አያንሱም። 35አምላካቸው እሆናቸው ዘንድ የዘለዓለም ቃል ኪዳንን እሠራላቸዋለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ ይሆኑኛል፤ ከእንግዲህም ወዲህ ሕዝቤ እስራኤልን ከሰጠኋቸው ሀገራቸው አላወጣቸውም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ባሮክ 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ