በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ፥ ድሆችንም የምትበድሉ፥ ችግረኞችንም የምታስጨንቁ፥ ጌቶቻቸውንም፦ አምጡ እንጠጣ የምትሉ እናንተ የባሳን ላሞች ሆይ! ይህን ቃል ስሙ። ጌታ አግዚአብሔር፥ “እናንተን በሰልፍ ዕቃ፥ ቅሬታችሁንም በመቃጥን የሚወስዱበት ቀን እነሆ በላያችሁ ይመጣል” ብሎ በቅዱስነቱ ምሎአል። “ዕራቁታችሁን ያወጡአችኋል፤ እርስ በርሳችሁም ትተያያላችሁ፤ በሬማንም ተራራ ትጣላላችሁ፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “ወደ ቤቴል ገብታችሁ ኀጢአትን ሠራችሁ፤ በጌልገላም ኀጢአትን አበዛችሁ፤ በየማለዳውም መሥዋዕታችሁን፥ በየሦስተኛውም ቀን ዐሥራታችሁን አቀረባችሁ፤ ሕጉን በውጭ አነበባችሁ፤ የታመነም አላችሁት፤ በፈቃዳችሁም የምታቀርቡትን አውጁና አውሩ፥” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “በከተማችሁ ሁሉ ጥርስን ማጥረስን፥ በስፍራችሁም ሁሉ እንጀራን ማጣትን ሰጠኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም ይላል እግዚአብሔር። መከር ሳይደርስ ገና ከሦስት ወር በፊት ዝናብን ከለከልኋችሁ፤ በአንድም ከተማ ላይ አዘነብሁ፤ በሌላውም ከተማ ላይ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ በአንድ ወገን ዘነበ፤ ያልዘነበበትም ወገን ደረቀ። የሁለት ወይም የሦስት ከተሞች ሰዎች ወደ አንዲት ከተማ ውኃ ይጠጡ ዘንድ ሄዱ፤ ነገር ግን አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። በአባርና በቸነፈር መታኋችሁ፤ አትክልታችሁ፥ ወይናችሁና በለሳችሁ፥ ወይራችሁም ከበጀ በኋላ ተምች በላው፤ ይህም ሆኖ እናንተ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። “በግብፅ እንደ ሆነው ሞትን ሰደድሁባችሁ፤ ጐበዛዝቶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፤ ፈረሶቻችሁንም አስማረክሁ፤ በሰፈራችሁም እሳትን ሰድጄ አጠፋኋችሁ፤ በዚህም ሁሉ እናንተ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፥ ይላል እግዚአብሔር። ሰዶምንና ገሞራን አስቀድሜ እንደ ገለበጥኋቸው፥ እንዲሁ ገለበጥኋችሁ፤ እናንተም ከእሳት ውስጥ እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ በዚህም ወደ እኔ አልተመለሳችሁም” ይላል እግዚአብሔር። “ስለዚህ እስራኤል ሆይ! እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እስራኤልም ሆይ! እንደዚህ ስለማደርግብህ የአምላክህን ስም ለመጥራት ተዘጋጅ። እነሆ ነጐድጓድን የሚያጸና፥ ነፋስንም የፈጠረ፥ የመሢሕን ነገር ለሰው የሚነግር፥ ንጋትን ጭጋግ የሚያደርግ፥ በምድርም ከፍታዎች ላይ የሚረግጥ፥ ስሙ ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።”
ትንቢተ አሞጽ 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 4:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች