እንደ ባሳን ቅልብ ላሞች ሰውነታችሁን ያወፈራችሁ የሰማርያ ሴቶች ሆይ! ይህን ቃል አድምጡ! እናንተ ደካሞችን ታዋርዳላችሁ፤ ድኾችን ትጨቊናላችሁ፤ ባሎቻችሁ ሁልጊዜ የሚያሰክር መጠጥ እንዲያቀርቡላችሁ ትጠይቃላችሁ። ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር በቅድስናው እንዲህ ሲል ምሎአል፦ “እናንተ በመንጠቆ ተይዞ እንደሚወሰድ ነገር የምትወሰዱበት ጊዜ ይመጣል፤ ከእናንተ እስከ መጨረሻ የቈዩት እንኳ በመንጠቆ ተይዘው እንደሚወሰዱ ዐሣዎች ይወሰዳሉ። እያንዳንዳችሁ በአቅራቢያችሁ በሚገኘው መሹለኪያ ቀዳዳ ተጐትታችሁ በመውጣት ወደ ሃርሞን ትጣላላችሁ።” ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ወደ ቤትኤል ሄዳችሁ ኃጢአት ሥሩ! ወደ ጌልጌላም ሂዱና የበለጠ በደል ፈጽሙ! በየዕለቱ መሥዋዕታችሁን አቅርቡ! በየሦስተኛውም ቀን ዐሥራታችሁን ስጡ። እናንተም ማድረግ የምትፈልጉት ይህንኑ ስለ ሆነ፥ የምስጋና ቊርባን የሆነውን የኅብስት መባችሁን አቅርቡ፤ በፈቃዳችሁም ስለምታቀርቡት መሥዋዕት ዐዋጅ ንገሩ።” “በአፋችሁ የምትቀምሱት እህል አሳጥቼ በከተሞቻችሁ ሁሉ ችጋር ለቅቄባችኋለሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። አዝመራችሁ ከመድረሱ ከሦስት ወር በፊት ዝናብ እንዲቋረጥ አደረግሁ፤ በአንድ ከተማ ሲዘንብ በሌላው ከተማ እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ ለአንዱ እርሻ ሲዘንብለት ሌላው እርሻ ዝናብ አጥቶ ደረቀ። ሰዎች ውሃ መጠጣት ፈልገው ከከተማ ወደ ከተማ ሄዱ፤ ነገር ግን በቂ ውሃ ባለማግኘታቸው ጠጥተው ሊረኩ አልቻሉም፤ እናንተም ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። “ሰብላችሁን የሚያደርቅ ብርቱ ነፋስ ላክሁባችሁ፤ አትክልታችሁንና የወይን ተክላችሁን የበለስና የወይራ ዛፋችሁን ሁሉ አንበጣ በላው፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። “በግብጽ ምድር የላክሁትን ዐይነት መቅሠፍት ላክሁባችሁ፤ ጐልማሶቻችሁ በሰይፍ እንዲሞቱ፥ ፈረሶቻችሁም እንዲማረኩ አደረግሁ፤ በሰፈራችሁ በሞቱ ሰዎች የበድን ግማት አፍንጫችሁን ሞላሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። “ሰዶምንና ገሞራን እንደ ደመሰስኩ ከእናንተም ብዙዎችን ደመሰስኩ፤ እናንተም የተረፋችሁት በእሳት ከተቀጣጠለ በኋላ ተነጥቆ እንደ ወጣ እንጨት ነው፤ ይህም ሁሉ ሆኖ ወደ እኔ አልተመለሳችሁም። የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እነሆ እኔም እንደዚሁ አደርግባችኋለሁ፤ ስለዚህ ይህን ስለማደርግባችሁ ከእኔ ከአምላካችሁ ጋር በፍርድ ለመገናኘት ተዘጋጁ!” ተራራዎችን የሠራ፥ ነፋሶችን የፈጠረ፥ ያሰበውን ነገር ለሰው የሚገልጥ፥ የቀኑን ብርሃን ወደ ጨለማ የሚለውጥ፥ በምድር ከፍታዎች ላይ የሚራመድ፥ ስሙ የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው።
ትንቢተ አሞጽ 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ትንቢተ አሞጽ 4:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች