እናንተ በሰማርያ ተራራ የምትኖሩ የባሳን ላሞች፤ ድኾችን የምትጨቍኑና ችግረኞችን የምታስጨንቁ፣ ባሎቻችሁንም፣ “መጠጥ አቅርቡልን” የምትሉ ሴቶች ይህን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር በቅድስናው እንዲህ ሲል ምሏል፤ “እነሆ፤ በመንጠቆ ተይዛችሁ የምትወሰዱበት ትሩፋናችሁ እንኳ፣ በዓሣ መንጠቆ የሚወሰድበት ጊዜ ይመጣል። እያንዳንዳችሁ በቅጥሩ በተነደለው መሽሎኪያ ወደ ሬማንም ትጣላላችሁ፤” ይላል እግዚአብሔር። “ወደ ቤቴል ሂዱና ኀጢአትን ሥሩ፤ ወደ ጌልገላም ሂዱና ኀጢአትን አብዙ፤ በየማለዳው መሥዋዕቶቻችሁን፣ በየሦስቱ ዓመት ዐሥራታችሁን አቅርቡ። እርሾ ያለበትን እንጀራ የምስጋና መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ፤ የበጎ ፈቃድ ስጦታችሁን አሳውቁ፤ እናንተ የእስራኤል ልጆች የምትወድዱት ይህን ነውና፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር። “በየከተማው ጥርሳችሁን አጠራለሁ፤ በየመንደሩም የምትበሉትን አሳጣኋችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም” ይላል እግዚአብሔር። “መከር ሊደርስ ሦስት ወር ሲቀረውም፣ ዝናብ ከለከልኋችሁ፤ በአንዱ ከተማ ላይ አዘነብሁ፤ በሌላው ላይ ግን እንዳይዘንብ አደረግሁ፤ አንዱ ዕርሻ ሲዘንብለት፣ ሌላው ዝናብ ዐጥቶ ደረቀ። ሰዎች ውሃ ፍለጋ ከከተማ ወደ ከተማ ባዘኑ፣ ይሁን እንጂ ጠጥተው አልረኩም፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፤” ይላል እግዚአብሔር። “የአትክልትና የወይን ቦታዎቻችሁን ብዙ ጊዜ መታሁ፤ በዋግና በአረማሞም አጠፋኋቸው፤ አንበጦችም የበለስና የወይራ ዛፎቻችሁን በሉ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፤” ይላል እግዚአብሔር። “በግብጽ ላይ እንዳደረግሁት፣ መቅሠፍትን ላክሁባችሁ፤ ከተማረኩት ፈረሶቻችሁ ጋራ፣ ጕልማሶቻችሁን በሰይፍ ገደልሁ፤ የሰፈራችሁ ግማት አፍንጫችሁ እንዲገባ አደረግሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም” ይላል እግዚአብሔር። “ሰዶምንና ገሞራን እንደ ገለበጥኋቸው፣ አንዳንዶቻችሁን ገለበጥሁ፤ ከእሳት እንደ ተነጠቀ ትንታግ ሆናችሁ፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም፤” ይላል እግዚአብሔር። “ስለዚህ እስራኤል ሆይ፤ እንደዚህ አደርግብሃለሁ፤ እንደዚህም ስለማደርግብህ፣ እስራኤል ሆይ፤ አምላክህን ለመገናኘት ተዘጋጅ።” ተራሮችን የሚሠራ፣ ነፋስን የሚፈጥር፣ ሐሳቡንም ለሰው የሚገልጥ፣ ንጋትን ጨለማ የሚያደርግ፣ የምድርንም ከፍታዎች የሚረግጥ፣ ስሙ የሰራዊት አምላክ እግዚአብሔር ነው።
አሞጽ 4 ያንብቡ
ያዳምጡ አሞጽ 4
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አሞጽ 4:1-13
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች