ወደ ተሰ​ሎ​ንቄ ሰዎች 2 2:1-12

ወደ ተሰ​ሎ​ንቄ ሰዎች 2 2:1-12 አማ2000

ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት “የጌታ ቀን ደርሶአል፤” ብላችሁ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዐመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ አይደርስምና። “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤” ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው። ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን? በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። የዐመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ። በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዐመፀኛ ይገለጣል፤ ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዐመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዐመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።