2 ተሰሎንቄ 2:1-12

2 ተሰሎንቄ 2:1-12 NASV

ወንድሞች ሆይ፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱም ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደ ተላከ መልእክት የጌታ ቀን ደርሷል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሯችሁ አትናወጡ፤ አትደንግጡም። ማንም ሰው በምንም መንገድ አያታልላችሁ፤ አስቀድሞ ዐመፅ ሳይነሣ፣ ለጥፋት የተመደበውም የዐመፅ ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል። ከእናንተ ጋራ በነበርሁበት ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበር ትዝ አይላችሁምን? በራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን ምን እንደሚከለክለው ታውቃላችሁ። የዐመፅ ምስጢር አሁንም እንኳ እየሠራ ነውና፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የሚከለክለው ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው። ከዚያም በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያስወግደውና በምጽአቱም ክብር ፈጽሞ የሚያጠፋው ዐመፀኛ ይገለጣል። የእርሱም አመጣጥ እንደ ሰይጣን አሠራር ሲሆን፣ ይህም በኀይል ሁሉ፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቆችም ሁሉ ይሆናል፤ እንዲሁም ይድኑ ዘንድ እውነትን ባለመውደድ የሚጠፉትን ሰዎች በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በሐሰት እንዲያምኑ የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፤ ይህም የሚሆነው እውነትን ያላመኑት ነገር ግን በክፋት ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።