2 ተሰሎንቄ ሰዎች 2:1-12

2 ተሰሎንቄ ሰዎች 2:1-12 አማ05

ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና እኛም ከእርሱ ጋር ለመሆን ስለ መሰብሰባችን ጉዳይ የምንለምናችሁ ይህን ነው፤ በትንቢት ወይም በቃል እንደ ተነገረ ወይም ከእኛ በመልእክት እንደ ተጻፈ አድርጋችሁ “የጌታ ቀን ደርሶአል” በማለት በቶሎ አእምሮአችሁ አይናወጥ፤ አትታወኩም፤ ማንም ሰው በምንም ዐይነት አያታላችሁ፤ አስቀድሞ ክሕደት ሳይመጣ፥ ገሃነም የሚገባው የዐመፅ ሰው የሆነውም ሳይገለጥ፥ ያ ቀን አይመጣም። ይህ የዐመፅ ሰው አማልክት ተብለው ከሚመለኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ያደርጋል፤ “እግዚአብሔር ነኝ” እያለም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንኳ ለመቀመጥ ይደፍራል። ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ይህን ነገር ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን? በተወሰነለት ጊዜ እስኪገለጥ ድረስ አሁን እንዳይገለጥ የሚከለክለው ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ምሥጢራዊው የዐመፅ ኀይል አሁንም በመሥራት ላይ ነው፤ ሆኖም አሁን የሚከለከለው አለ፤ ይህም የሚሆነው ያ የሚከለክለው እስኪወገድ ድረስ ነው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያጠፋውና በግርማ መምጣቱ የሚደመስሰው የዐመፅ ሰው ይገለጣል። የዐመፅ ሰው የሚመጣው በሰይጣን ኀይል አሳሳች ተአምራትንና ምልክቶችን አስደናቂ ነገሮችንም በማድረግ ነው፤ እንዲሁም የሚጠፉትን ሰዎች የሚያታልሉት ማናቸውንም ክፉ ነገሮችን በማድረግ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠፉትም ለመዳን የሚያበቃቸውን እውነት ወደው ስላልተቀበሉ ነው። በዚህ ምክንያት በሐሰት እንዲያምኑ እግዚአብሔር የሚያሳስት ኀይልን ይልክባቸዋል። ይህም የሚሆነው እውነትን አናምንም ብለው በኃጢአት የሚደሰቱ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።