2 ተሰሎንቄ 2:1-12
2 ተሰሎንቄ 2:1-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት “የጌታ ቀን ደርሶአል፤” ብላችሁ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዐመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ አይደርስምና። “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤” ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው። ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን? በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። የዐመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ። በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዐመፀኛ ይገለጣል፤ ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዐመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዐመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።
2 ተሰሎንቄ 2:1-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱም ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደ ተላከ መልእክት የጌታ ቀን ደርሷል ብላችሁ ፈጥናችሁ ከአእምሯችሁ አትናወጡ፤ አትደንግጡም። ማንም ሰው በምንም መንገድ አያታልላችሁ፤ አስቀድሞ ዐመፅ ሳይነሣ፣ ለጥፋት የተመደበውም የዐመፅ ሰው ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። እርሱም አምላክ ከተባለና ከሚመለከው ነገር ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ተቃዋሚ ነው፤ እርሱም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ተቀምጦ፣ “እኔ አምላክ ነኝ” እያለ ዐዋጅ ያስነግራል። ከእናንተ ጋራ በነበርሁበት ጊዜ፣ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበር ትዝ አይላችሁምን? በራሱ ጊዜ ይገለጥ ዘንድ አሁን ምን እንደሚከለክለው ታውቃላችሁ። የዐመፅ ምስጢር አሁንም እንኳ እየሠራ ነውና፤ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የሚከለክለው ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ ብቻ ነው። ከዚያም በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያስወግደውና በምጽአቱም ክብር ፈጽሞ የሚያጠፋው ዐመፀኛ ይገለጣል። የእርሱም አመጣጥ እንደ ሰይጣን አሠራር ሲሆን፣ ይህም በኀይል ሁሉ፣ በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቆችም ሁሉ ይሆናል፤ እንዲሁም ይድኑ ዘንድ እውነትን ባለመውደድ የሚጠፉትን ሰዎች በሚያታልል በተለያየ የክፋት ሥራ ይመጣል። በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር በሐሰት እንዲያምኑ የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል፤ ይህም የሚሆነው እውነትን ያላመኑት ነገር ግን በክፋት ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።
2 ተሰሎንቄ 2:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን፥ በመንፈስ ወይም በቃል ወይም ከእኛ እንደሚመጣ በመልእክት፦ የጌታ ቀን ደርሶአል ብላችሁ፥ ከአእምሮአችሁ ቶሎ እንዳትናወጡ እንዳትደነግጡም እንለምናችኋለን። ማንም በማናቸውም መንገድ አያስታችሁ፤ ክህደቱ አስቀድሞ ሳይመጣና የዓመፅ ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ፥ አይደርስምና። እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥ ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ ነው። ገና ከእናንተ ጋር ሳለሁ፥ ይህን እንዳልኋችሁ ትዝ አይላችሁምን? በገዛ ራሱ ጊዜም ይገለጥ ዘንድ፥ የሚከለክለውን አሁን ታውቃላችሁ። የዓመፅ ምሥጢር አሁን ይሠራልና፤ ብቻ ከመንገድ እስኪወገድ ድረስ አሁን የሚከለክል አለ። በዚያም ጊዜ ጌታ ኢየሱስ በአፉ መንፈስ የሚያጠፋው፥ ሲመጣም በመገለጡ የሚሽረው ዓመፀኛ ይገለጣል፤ ይድኑ ዘንድ የእውነት ፍቅር ስላልተቀበሉ ለሚጠፉ፥ የእርሱ መምጣት በተአምራት ሁሉና በምልክቶች በሐሰተኞች ድንቆችም በዓመፅም መታለል ሁሉ እንደ ሰይጣን አሠራር ነው። ስለዚህም ምክንያት፥ በእውነት ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ ይላቸው የነበሩ ሁሉ ፍርድን እንዲቀበሉ፥ ሐሰትን ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር የስሕተትን አሠራር ይልክባቸዋል።
2 ተሰሎንቄ 2:1-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና እኛም ከእርሱ ጋር ለመሆን ስለ መሰብሰባችን ጉዳይ የምንለምናችሁ ይህን ነው፤ በትንቢት ወይም በቃል እንደ ተነገረ ወይም ከእኛ በመልእክት እንደ ተጻፈ አድርጋችሁ “የጌታ ቀን ደርሶአል” በማለት በቶሎ አእምሮአችሁ አይናወጥ፤ አትታወኩም፤ ማንም ሰው በምንም ዐይነት አያታላችሁ፤ አስቀድሞ ክሕደት ሳይመጣ፥ ገሃነም የሚገባው የዐመፅ ሰው የሆነውም ሳይገለጥ፥ ያ ቀን አይመጣም። ይህ የዐመፅ ሰው አማልክት ተብለው ከሚመለኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ያደርጋል፤ “እግዚአብሔር ነኝ” እያለም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንኳ ለመቀመጥ ይደፍራል። ከእናንተ ጋር በነበርኩ ጊዜ ይህን ነገር ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን? በተወሰነለት ጊዜ እስኪገለጥ ድረስ አሁን እንዳይገለጥ የሚከለክለው ምን እንደ ሆነ ታውቃላችሁ። ምሥጢራዊው የዐመፅ ኀይል አሁንም በመሥራት ላይ ነው፤ ሆኖም አሁን የሚከለከለው አለ፤ ይህም የሚሆነው ያ የሚከለክለው እስኪወገድ ድረስ ነው። ከዚህ በኋላ ጌታ ኢየሱስ በአፉ እስትንፋስ የሚያጠፋውና በግርማ መምጣቱ የሚደመስሰው የዐመፅ ሰው ይገለጣል። የዐመፅ ሰው የሚመጣው በሰይጣን ኀይል አሳሳች ተአምራትንና ምልክቶችን አስደናቂ ነገሮችንም በማድረግ ነው፤ እንዲሁም የሚጠፉትን ሰዎች የሚያታልሉት ማናቸውንም ክፉ ነገሮችን በማድረግ ነው። እነዚህ ሰዎች የሚጠፉትም ለመዳን የሚያበቃቸውን እውነት ወደው ስላልተቀበሉ ነው። በዚህ ምክንያት በሐሰት እንዲያምኑ እግዚአብሔር የሚያሳስት ኀይልን ይልክባቸዋል። ይህም የሚሆነው እውነትን አናምንም ብለው በኃጢአት የሚደሰቱ ሁሉ እንዲፈረድባቸው ነው።
2 ተሰሎንቄ 2:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ነገር ግን ወንድሞች ሆይ! ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መምጣትና ወደ እርሱ ስለ መሰብሰባችን ይህን እንለምናችኋለን፤ ከእኛ በሚመስል መልእክት ወይም በቃል ወይም በመንፈስ፦ “የጌታ ቀን መጥቷል፤” ብላችሁ አእምሮአችሁ በቀላሉ አይናወጥ አይደንግጥም። ማንም ሰው በማናቸውም መንገድ አያታልላችሁ፤ ከሐዲው አስቀድሞ ሳይመጣ የዓመፅም ሰው እርሱም የጥፋት ልጅ ሳይገለጥ ያ ቀን አይመጣምና። እርሱም ሰው የሚያመልከውን ነገር ወይም አማልክት ነን ከሚሉት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ በማድረግና በመቃወም፦ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ” ብሎ ያውጃል፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ይቀመጣል። ከእናንተ ጋር በነበርሁ ጊዜ እነዚህን ነገሮች ነግሬአችሁ እንደ ነበረ አታስታውሱምን? አሁን ምን እንደከለከለው አውቃችኋልና በራሱ ጊዜ የተገለጠ ይሆናል። አስቀድሞም የዓመፅ ሚስጢር በሥራ ላይ ነው፤ አሁን ግን እርሱ ብቻ ይከለክለዋል፤ እርሱም እንዲህ የሚያደርገው ከመንገድ እስከሚወገድ ድረስ ነው። በዚያም ጊዜ ዓመፀኛው ይገለጣል፤ ጌታ ኢየሱስም በአፉ እስትንፋስ ይገድለዋል፤ በመምጣቱም መገለጥ ያጠፋዋል፤ ዓመፀኛው ከሙሉ ኃይልና ምልክቶች፥ ከሐሰትም ተአምራቶች ጋር ሆኖ በሰይጣን አሠራር ይመጣል። እንዲሁም ለመዳን እውነቱን ወድደው ባለ መቀበላቸው ለሚጠፉት በማታለል ክፋት ሁሉ ይመጣባቸዋል። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ የሐሰትን ኑፋቄ በመላክ በስሕተት እንዲያምኑ ያደርጋቸዋል። በዚህም እውነቱን ያላመኑ ነገር ግን በዓመፅ ደስ የሚሰኙ ሁሉ ይፈረድባቸዋል።