በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ለብዙ ጊዜ ጦርነት ሆነ፤ የዳዊት ቤት እየበረታ፥ የሳኦል ቤት ግን እየደከመ የሚሄድ ሆነ። ለዳዊትም ወንዶች ልጆች በኬብሮን ተወለዱለት፤ በኵሩም ከኢይዝራኤላዊቱ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን ነበረ። ሁለተኛውም ከቀርሜሎሳዊቱ ከአቤግያ የተወለደው ዶሎሕያ ነበረ። ሦስተኛውም ከጌድሶር ንጉሥ ከቶልሜልም ልጅ ከመዓክ የተወለደው አቤሴሎም ነበረ። አራተኛውም የአጊት ልጅ አዶንያስ፥ አምስተኛውም የአቢጣል ልጅ ሰፋጥያ ነበረ። ስድስተኛውም የዳዊት ሚስት የዒገል ልጅ ይትረኃም ነበረ። ለዳዊት በኬብሮን የተወለዱለት እነዚህ ነበሩ። በሳኦል ቤትና በዳዊት ቤት መካከል ጦርነት ሆኖ ሳለ አበኔር የሳኦልን ቤት ያበረታ ነበር። ለሳኦልም የኢዮሄል ልጅ ሩጻፋ የተባለች ዕቅብት ነበረችው፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፥ “ወደ አባቴ ዕቅብት ለምን ገባህ?” አለው። አበኔርም ኢያቡስቴ እንዲህ ስላለው እጅግ ተቈጣ፤ አበኔርም እንዲህ አለው፥ “በውኑ እኔ የውሻ ራስ ነኝን? እኔ ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹም፥ ለዘመዶቹም ቸርነት አድርጌአለሁ፤ አንተንም ለዳዊት እጅ አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ አንተም ዛሬ ከዚህች ሴት ጋር ስለ ሠራሁት ኀጢአት ትከስሰኛለህ። እግዚአብሔር ለዳዊት እንደ ማለለት እንዲሁ ከእርሱ ጋር ዛሬ ባላደርግ እግዚአብሔር በአበኔር ይህን ያድርግበት፤ ይህንም ይጨምርበት። የዳዊትንም ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ከፍ ያደርግ ዘንድ መንግሥትን ከሳኦል ቤት ወሰዳት።” ኢያቡስቴም አበኔርን ይፈራው ነበርና ቃልን ይመልስለት ዘንድ አልቻለም። አበኔርም ለዳዊት፥ “ከእኔ ጋር ቃል ኪዳን አድርግ፤ እጄም ከአንተ ጋር ትሆናለች፤ እስራኤልንም ሁሉ ወደ አንተ እመልሰዋለሁ” ብለው በስሙ ይነግሩት ዘንድ መልእክተኞችን ወዲያውኑ ላከለት። ዳዊትም፥ “ይሁን፤ በመልካም ፈቃደኛነት ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር ከአንተ እሻለሁ፤ ፊቴን ለማየት በመጣህ ጊዜ፥ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ካላመጣህልኝ ፊቴን አታይም” አለው። ዳዊትም ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ፥ “በመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ያጨኋትን ሚስቴን ሜልኮልን መልስልኝ” ብሎ መልእክተኞችን ላከ። ኢያቡስቴም ልኮ ከሴሊስ ልጅ ከባልዋ ከፈላጥያል ወሰዳት። ባልዋም እያለቀሰ ከእርስዋ ጋር ሄደ፤ እስከ ብራቂም ድረስ ተከተላት። አበኔርም፥ “ሂድ፤ ተመለስ” አለው፤ እርሱም ተመለሰ። አበኔርም ለእስራኤል ሽማግሌዎች፥ “አስቀድሞ ዳዊት በእናንተ ላይ ንጉሥ ይሆን ዘንድ ፈልጋችሁ ነበር። እግዚአብሔርም ስለ ዳዊት፦ በባሪያዬ በዳዊት እጅ ሕዝቤን እስራኤልን ክፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው ሁሉ እጅ አድናለሁ ብሎ ተናግሮአልና እንግዲህ አሁን አድርጉ´ ብሎ ነገራቸው። አበኔርም ደግሞ በብንያም ልጆች ጆሮ ተናገረ፤ አበኔርም ደግሞ በእስራኤልና በብንያም ቤት ሁሉ መልካም የነበረውን ለዳዊት ሊነግረው ወደ ኬብሮን ሄደ። አበኔርም ከሃያ ሰዎች ጋር ወደ ዳዊት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። አበኔርም ዳዊትን፥ “ተነሥቼ ልሂድ፤ ካንተ ጋርም ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፥ ነፍስህም እንደ ወደደች ሁሉን እንድትገዛ እስራኤልን ሁሉ ለጌታዬ ለንጉሥ ልሰብስብ” አለው። ዳዊትም አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 3:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos