የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2 ሳሙኤል 3:1-21

2 ሳሙኤል 3:1-21 NASV

በዳዊት ቤትና በሳኦል ቤት መካከል የነበረው ጦርነት ብዙ ጊዜ ቈየ፤ ዳዊት እየበረታ ሲሄድ፣ የሳኦል ቤት ግን እየተዳከመ መጣ። ዳዊት በኬብሮን ሳለ፣ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ የበኵር ልጁ ከኢይዝራኤላዊቷ ከአኪናሆም የተወለደው አምኖን፣ ሁለተኛው፣ የቀርሜሎሳዊው የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢግያ የተወለደው ኪልአብ፣ ሦስተኛው፣ ከጌሹር ንጉሥ ከተልማይ ልጅ ከመዓካ የተወለደው አቤሴሎም፣ አራተኛው፣ ከአጊት የተወለደው አዶንያስ፤ ዐምስተኛው፣ ከአቢጣል የተወለደው ሰፋጥያ፣ ስድስተኛው፣ ከዳዊት ሚስት ከዔግላ የተወለደው ይትረኃም ነበር። እነዚህ ዳዊት በኬብሮን ሳለ የተወለዱለት ናቸው። የሳኦል ቤትና የዳዊት ቤት በጦርነት ላይ በነበሩበት ጊዜ፣ አበኔር በሳኦል ቤት ላይ ኀይሉን ያጠናክር ነበር። ሳኦልም የኢዮሄልን ልጅ ሪጽፋን በቁባትነት አስቀምጧት ነበር፤ ኢያቡስቴም አበኔርን፣ “ለምንድን ነው ከአባቴ ቁባት ጋራ የተኛኸው?” አለው። አበኔርም በኢያቡስቴ ንግግር እጅግ ስለ ተቈጣ እንዲህ አለ፤ “እኔ ለይሁዳ የምወግን የውሻ ጭንቅላት ነኝን? ለአባትህ ለሳኦል ቤት ለወንድሞቹና ለዘመዶቹ ታማኝነቴን እስከ ዛሬ ድረስ አላጓደልሁም፤ አንተንም አሳልፌ ለዳዊት አልሰጠሁም፤ አሁን ግን አንተ ከዚህች ሴት ጋራ በፈጸምሁት ነገር ትከሰኛለህን? እግዚአብሔር ለዳዊት በመሐላ የሰጠውን ተስፋ እዳር እንዲደርስ ሳላደርግ ብቀር እግዚአብሔር በአበኔር ላይ ክፉ ያድርግበት፤ ከዚያ የባሰም ያምጣበት፤ የማለለትም መንግሥትን ከሳኦል ቤት አውጥቶ፣ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ባለው በእስራኤልና በይሁዳ ምድር ላይ የዳዊትን ዙፋን ለመመሥረት የሰጠው ተስፋ ነው።” ኢያቡስቴም አበኔርን አጥብቆ ፈርቶት ስለ ነበር፣ እንደ ገና አንዲት ቃል እንኳ ሊመልስለት አልደፈረም። ከዚያም አበኔር ለዳዊት፣ “ምድሪቱ የማን ናት? ከእኔ ጋራ ተስማማ፤ እነሆ እስራኤል ሁሉ ወደ አንተ እንዲመለስ እኔ እረዳሃለሁ” ብለው ለዳዊት እንዲነግሩለት መልክተኞች ላከ። ዳዊትም፣ “ይሁን ዕሺ፣ ከአንተ ጋራ ስምምነቱን አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ከአንተ አንዲት ነገር እሻለሁ፤ ይኸውም ወደ እኔ ስትመጣ በመጀመሪያ የሳኦልን ሴት ልጅ ሜልኮልን ይዘህልኝ እንድትመጣ ነው፤ አለዚያ ግን ወደ እኔ እንዳትመጣ” አለ። ከዚያም ዳዊት፣ “የመቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ የከፈልሁባትን ሚስቴን ሜልኮልን ስጠኝ” ብሎ ወደ ሳኦል ልጅ ወደ ኢያቡስቴ መልክተኞች ላከበት። ስለዚህም ኢያቡስቴ መልክተኛ ልኮ፣ ሜልኮልን ከባሏ ከሌሳ ልጅ ከፈልጢኤል ወሰዳት። ባሏም እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ እያለቀሰ ተከትሏት ሄደ፤ ከዚያም አበኔር፣ “በል ይበቃል! ወደ ቤትህ ተመለስ” አለው። ስለዚህም ተመለሰ። አበኔር ከእስራኤል ሽማግሌዎች ጋራ ተመካከረ፤ እንዲህም አለ፤ “ባለፈው ጊዜ ዳዊት በላያችሁ እንዲነግሥ ፈልጋችሁ ነበር፤ እግዚአብሔር ለዳዊት፣ ‘በባሪያዬ በዳዊት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን እጅና ከጠላቶቻቸው እጅ እታደጋቸዋለሁ’ ብሎ ተስፋ ስለ ሰጠው፣ ይህን አሁኑኑ አድርጉት።” እንዲሁም አበኔር ለብንያማውያን ራሱ ሄዶ ይህንኑ ነገራቸው፤ ከዚያም እስራኤልና መላው የብንያም ቤት ለማድረግ የፈለጉትን ሁሉ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ። አበኔር ከሃያ ሰዎች ጋራ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን መጣ፤ ዳዊትም ለአበኔርና ዐብረውት ለነበሩት ሰዎች ግብዣ አደረገላቸው። ከዚያም አበኔር ዳዊትን፤ “ከአንተ ጋራ ቃል ኪዳን እንዲያደርጉ፣ ልብህ እንደተመኘውም ሁሉን እንድትገዛ ፈጥኜ ሄጄ፣ ለጌታዬ ለንጉሡ መላውን እስራኤልን ልሰብስብ” አለው። ስለዚህ ዳዊት አበኔርን አሰናበተው፤ በሰላምም ሄደ።