በዚህ ዐይነት በሳኦል ቤተሰብና በዳዊት ቤተሰብ መካከል የሚካሄደው ጦርነት ለረጅም ጊዜ ቈየ፤ ሆኖም ዳዊት እየበረታ ሲሄድ የሳኦል ቤተሰብ እየተዳከመ ሄደ። ዳዊት በኬብሮን ሳለ ስድስት ወንዶች ልጆች ተወለዱለት፤ እነርሱም በኲሩ የኢይዝራኤል ተወላጅ ከሆነችው ከአሒኖዓም የተወለደው አምኖን፥ ሁለተኛው የቀርሜሎስ ተወላጅ የናባል ሚስት ከነበረችው ከአቢጌል የተወለደው ኪልአብ፥ ሦስተኛው ታልማይ ተብሎ የሚጠራው የገሹር ንጉሥ ልጅ ከሆነችው ከማዕካ የተወለደው አቤሴሎም፥ አራተኛው ከሐጊት የተወለደው አዶኒያ፥ አምስተኛው ከአቢጣል የተወለደው ሸፋጥያ፥ ስድስተኛው ከሚስቱ ከዔግላ የተወለደው ዩትረዓም፥ እነዚህ ሁሉ በኬብሮን የተወለዱ ናቸው። በሳኦል ቤተሰብና በዳዊት ቤተሰብ መካከል ጦርነቱ እየቀጠለ በሄደ መጠን አበኔር በሳኦል ቤተሰብ እየበረታ ሄደ። ሳኦል የአያ ልጅ የሆነች ሪጽፋ የምትባል ቁባት ነበረችው፤ ኢያቡስቴ አበኔርን “ለምን ከአባቴ ቁባት ጋር ተገናኘህ” አለው። የኢያቡስቴ ቃል አበኔርን በጣም አስቈጣው፤ እንዲህም አለ፦ “እኔ ወደ ይሁዳ ነገድ የዞርኩ የማልጠቅም ውሻ ነኝን? እኔ ለአባትህ ቤት፥ ለወንድሞቹና ለወዳጆቹ ታማኝነትን አሳይቼአለሁ፤ አንተንም ለዳዊት አሳልፌ አልሰጠሁህም፤ ታዲያ፥ አንተ ስለዚህች ሴት ትወቅሰኛለህን? እግዚአብሔር መንግሥትን ከሳኦል ቤት ወሰደ የዳዊትን ዙፋን በእስራኤልና በይሁዳ ላይ ከሰሜን ከዳን ጀምሮ እስከ ደቡብ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ለመዘርጋት በመሐላ ቃል በገባለት መሠረት ባላስፈጽም በእኔ ላይ እግዚአብሔር ይፍረድ!” ኢያቡስቴም እጅግ ፈርቶ ስለ ነበር፥ ለአበኔር አንድ ቃል እንኳ ሊመልስለት አልቻለም። አበኔር በዚያን ጊዜ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት መልእክተኞች ልኮ “የዚህች ምድር ገዢ የሚሆን ማነው? እንግዲህ ከእኔ ጋር ስምምነት አድርግ፤ እኔም መላው እስራኤል በአንተ ቊጥጥር ሥር እንዲሆን ለማድረግ እረዳሃለሁ” አለው። ዳዊትም “መልካም ነው! ከአንተ ጋር ስምምነት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን አንተ በቅድሚያ የምትፈጽምልኝ ነገር አለ፤ ይኸውም ወደ እኔ በምትመጣበት ጊዜ የሳኦልን ልጅ ሜልኮልን ይዘህ ካልመጣህ መገናኘት አንችልም” አለው። እንዲሁም ዳዊት ወደ ኢያቡስቴ መልእክተኞች ልኮ እንዲህ አለው፤ “ሚስቴን ሜልኮልን መልስልኝ፤ እኔ እርስዋን ለማግባት የአንድ መቶ ፍልስጥኤማውያን ሸለፈት ማጫ ጥያለሁ” አለው። ስለዚህም ኢያቡስቴ መልእክተኛ በመላክ ሜልኮል የላዊሽ ልጅ ከሆነው ከባልዋ ከፓልጢኤል ልጅ አስወሰዳት፤ ባልዋ ፓልጢኤልም እያለቀሰ እስከ ባሑሪም ከተማ ድረስ ተከተላት፤ ነገር ግን አበኔር “ወደ ቤትህ ተመለስ” ባለው ጊዜ ተመለሰ። አበኔር ወደ እስራኤል መሪዎች ሄዶ እንዲህ አላቸው፤ “ዳዊት የእናንተ ንጉሥ እንዲሆን ለብዙ ጊዜ ተመኝታችሁ ነበር፤ እነሆ፥ አሁን አድርጉ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ‘በአገልጋዬ በዳዊት አማካይነት ሕዝቤን እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያንና ከሌሎቹም ጠላቶቻቸው እጅ በመታደግ አድናለሁ’ ሲል ተናግሮ እንደ ነበር አስታውሱ።” አበኔር ለብንያም ነገድ ሕዝብም ይህንኑ ተናገረ፤ ከዚያም በኋላ የብንያምና የእስራኤል ሕዝብ ለማድረግ የተስማሙበትን ጉዳይ ለዳዊት ለመንገር ወደ ኬብሮን ሄደ። አበኔር ኻያ ሰዎችን አስከትሎ ዳዊት ወዳለበት ወደ ኬብሮን በመጣ ጊዜ ዳዊት ግብዣ አደረገላቸው፤ አበኔርም ዳዊትን “ከአንተ ጋር እንዲነጋገሩና እንዲዋዋሉ አንተም ልብህ በተመኘው ሁሉ ላይ እንድትነግሥ ለማድረግ ወደ እስራኤላውያን ልሂድ” አለው። በዚህም ዐይነት ዳዊት አበኔርን በሰላም አሰናበተው።
ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሁለተኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 3:1-21
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos