ዳዊትም እግዚአብሔር ከሳኦል እጅና ከጠላቶቹ ሁሉ እጅ ባዳነው ቀን የዚህን መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር ተናገረ። እንዲህም አለ፥ “እግዚአብሔር ዓለቴ፥ አምባዬም፥ መድኀኒቴም ነው፤ እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፤ በእርሱም እታመናለሁ፤ ጋሻዬና የመድኀኒቴ ቀንድ፥ ረዳቴ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኀኒቴ ሆይ፥ ከግፈኛ ታድነኛለህ። ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ጭንቅ ያዘኝ፤ የዐመፅ ጎርፍም አስፈራኝ፤ የሞት ጣር ከበበኝ፤ የሞት ወጥመድም ደረሰብኝ። በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ እንዲረዳኝም ወደ አምላኬ ጮኽሁ፤ ከመቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፤ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮዎቹ ገባ። ምድርም ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤ የሰማይ መሠረቶችም ተነቃነቁ፤ ተንቀጠቀጡም፤ እግዚአብሔር ተቈጥቶአልና። ከቍጣው ጢስ ወጣ፤ ከአፉም የሚበላ እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ ተቃጠለ። ሰማዮችን አዘነበለ፤ ወረደም፤ ጭጋግም ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፎች ሆኖ ታየ፤ መሰወርያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም የነበረውን ድንኳን የውኃ ጨለማ አደረገ፤ በደመናም አገዘፈው። በፊቱም ካለው ብርሃን የተነሣ ፍም ተቃጠለ። እግዚአብሔርም ከሰማይ አንጐደጐደ፤ ልዑልም ቃሉን ሰጠ። ፍላጻውን ላከ፤ በተናቸውም፤ መብረቅንም አሰምቶ አስደነገጣቸው። ከእግዚአብሔር ተግሣፅ የተነሣ፥ ከመዓቱም መንፈስ እስትንፋስ የተነሣ፥ የባሕር ፈሳሾች ታዩ፤ የዓለም መሠረቶችም ተገለጡ። ከላይ ላከ፤ ወሰደኝም፤ ከብዙ ውኆችም አወጣኝ። ከብርቱዎች ጠላቶቼ፥ ከሚጠሉኝም አዳነኝ፤ በርትተውብኝ ነበርና።
መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 22 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ካልእ 22:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች