2 ሳሙኤል 22:1-18

2 ሳሙኤል 22:1-18 NASV

እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ሁሉና ከሳኦል እጅ በታደገው ጊዜ፣ ዳዊት የዚህን መዝሙር ቃል ለእግዚአብሔር ዘመረ፤ እንዲህም አለ፤ “እግዚአብሔር ዐለቴ፣ መጠጊያዬና ታዳጊዬ ነው፤ አምላኬ፣ የምሸሸግበት ዐለቴ፣ ጋሻዬና የድነቴ ቀንድ ነው፤ እርሱም ጠንካራ ምሽጌ፣ መጠጊያና አዳኜ ነው፤ ከዐመፀኛ ሰዎችም ታድነኛለህ። “ምስጋና የሚገባውን እግዚአብሔርን እጠራለሁ፤ ከጠላቶቼም እድናለሁ። የሞት ማዕበል ከበበኝ፤ ምናምንቴ ነገርም አጥለቀለቀኝ። የሲኦል ገመድ ተጠመጠመብኝ፤ የሞት ወጥመድም ተጋረጠብኝ። “በተጨነቅሁ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፤ ወደ አምላኬም ጮኽሁ። እርሱም ከመቅደሱ ድምፄን ሰማ፤ ጩኸቴም ከጆሮው ደረሰ። ምድር ተንቀጠቀጠች፤ ተናወጠችም፤ የሰማያትም መሠረቶች ተናጉ፤ እርሱ ተቈጥቷልና ተንቀጠቀጡ። ከአፍንጫው ጢስ ወጣ፤ ከአፉ የሚባላ እሳት ነደደ፤ ከውስጡም ፍሙ ጋለ። ሰማያትን ሰንጥቆ ወረደ፤ ከእግሩም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበረ። በኪሩቤል ላይ ተቀምጦ በረረ፤ በነፋስም ክንፍ መጠቀ። ጨለማው በዙሪያው እንዲከብበው፣ ጥቅጥቅ ያለውም የሰማይ ዝናም ደመና እንዲሰውረው አደረገ። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ፣ የመብረቅ ብልጭታ ወጣ። እግዚአብሔር ከሰማያት አንጐደጐደ፤ የልዑልም ድምፅ አስተጋባ። ፍላጻውን ሰድዶ በተናቸው፤ ታላቅ መብረቆቹንም ልኮ አወካቸው። ከእግዚአብሔር ተግሣጽ፣ ከአፍንጫው ከሚወጣው፣ ከእስትንፋሱ ቍጣ የተነሣ፣ የባሕር ወለል ታየ፤ የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። “ከላይ እጁን ዘርግቶ ያዘኝ፤ ከጥልቅ ውሆችም ውስጥ አወጣኝ። ከብርቱ ጠላቶቼ አዳነኝ፤ ከሚበረቱብኝ ባላጋሮቼም ታደገኝ።