መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 24
24
1በእርሱም ዘመን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወጣ፤ ኢዮአቄምም ሦስት ዓመት ተገዛለት፤ ከዚያም በኋላ ዘወር አለና ዐመፀበት። 2እግዚአብሔርም የከለዳውያንን አደጋ ጣዮች፥ የሶርያውያንንም አደጋ ጣዮች፥ የሞዓባውያንንም አደጋ ጣዮች፥ የአሞንንም ልጆች አደጋ ጣዮች ሰደደበት፤ በባሪያዎቹ በነቢያት ቃል እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ያጠፉት ዘንድ በይሁዳ ላይ ሰደዳቸው። 3ምናሴም ስላደረገው ኀጢአት ሁሉ ከፊቱ ያርቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳ ላይ ሆነ፤ 4ጻድቁንም ስለ ገደለ ኢየሩሳሌምንም በንጹሕ ደም ስለ ሞላ እግዚአብሔር ይራራ ዘንድ አልወደደም።
5የቀረውም የኢዮአቄም ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 6ኢዮአቄምም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በኦዛም የአትክልት ቦታ ተቀበረ#“በኦዛም የአትክልት ቦታ ተቀበረ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. የለም። ልጁም ዮአኪን በእርሱ ፋንታ ነገሠ። 7የባቢሎንም ንጉሥ ለግብፅ ንጉሥ የነበረውን ሁሉ ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ ወስዶ ነበርና የግብፅ ንጉሥ ከዚያ ወዲህ ከሀገሩ አልወጣም።
የይሁዳ ንጉሥ የዮአኪን ዘመነ መንግሥት
(2ዜ.መ. 36፥9-10)
8ዮአኪንም በነገሠ ጊዜ ዐሥራ ስምንት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ፤ እናቱም ኒስታ ትባል ነበር፤ እርስዋም የኢየሩሳሌም ሰው የኤልናታን ልጅ ነበረች። 9አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
10በዚያም ወራት የባቢሎን ንጉሥ የናቡከደነፆር ሠራዊት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ ከተማዪቱም ተከበበች። 11የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርም ወደ ከተማዪቱ መጣ። ሠራዊቱም ከበቡአት። 12የይሁዳም ንጉሥ ዮአኪን ከእናቱ፥ ከብላቴኖቹም፥ ከአለቆቹም፥ ከጃንደረቦቹም ጋር ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወጣ፤ የባቢሎንም ንጉሥ በነገሠ በስምንተኛው ዓመት ያዘው። 13የእግዚአብሔርን ቤተ መዛግብት ሁሉ የንጉሡንም ቤተ መዛግብት ከዚያ አወጣ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር መቅደስ የሠራውን የወርቁን ዕቃ ሁሉ ሰባበረ። 14ኢየሩሳሌምንም አጠፋት፥ አለቆቹንም ሁሉ፥ ጽኑዓኑንና ኀያላኑን ሁሉ፥ ጠራቢዎቹንም ሁሉ፥ ብረት ሠራተኞቹንም ሁሉ ዐሥር ሺህ ምርኮኞችን ሁሉ አፈለሰ፤ ከሀገሩ ድሆች በቀር ማንም አልቀረም። 15ዮአኪንንም ወደ ባቢሎን አፈለሰ፤ የንጉሡንም እናት፥ የንጉሡንም ሚስቶች፥ ጃንደረቦቹንም፥ የሀገሩንም ታላላቆች ከኢየሩሳሌም ወደ ባቢሎን ማረከ። 16የባቢሎንም ንጉሥ ሰባት ሺህ ያህል፥ ብርቱዎችንና ሰልፍ የሚችሉትን ሁሉ፥ ኀያላኑን ሁሉ አንድ ሺህ የሚሆኑ ጠራቢዎችንና ብረት ሠራተኞችንም ወደ ባቢሎን ማረከ። 17የባቢሎንም ንጉሥ የዮአኪንን አጎት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ልጁን” ይላል። ማታንያን በእርሱ ፋንታ አነገሠ፤ ስሙንም ሴዴቅያስ ብሎ ለወጠው።
የይሁዳ ንጉሥ የሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት
(2ዜ.መ. 36፥11-12፤ ኤር. 52፥1-3)
18ሴዴቅያስም በነገሠ ጊዜ ሃያ አንድ ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም አሚጣል የተባለች የሎብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 19ኢዮአቄምም እንዳደረገው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 20ከፊቱ አውጥቶ እስኪጥላቸው ድረስ ይህ ነገር በእግዚአብሔር ቍጣ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ ሆኖአልና፤ ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ላይ ዐመፀ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 24: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ