መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ካልእ 23

23
ንጉሡ ኢዮ​ስ​ያስ አም​ልኮ ጣዖ​ትን እንደ አስ​ወ​ገደ
(2ዜ.መ. 34፥3-729-33)
1ንጉ​ሡም ላከ፤ የይ​ሁ​ዳ​ንና የኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ም​ንም ሽማ​ግ​ሌ​ዎች ሁሉ ወደ እርሱ ሰበ​ሰ​ባ​ቸው። 2ንጉ​ሡም ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት ወጣ፤ ከእ​ር​ሱም ጋር የይ​ሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም የሚ​ኖሩ ሁሉ፥ ካህ​ና​ቱና ነቢ​ያ​ቱም፥ ሕዝ​ቡም ሁሉ ከታ​ና​ሾቹ ጀምሮ እስከ ታላ​ቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቤት የተ​ገ​ኘ​ውን የቃል ኪዳ​ኑን መጽ​ሐፍ ቃል ሁሉ በጆ​ሮ​አ​ቸው አነ​በበ። 3ንጉ​ሡም በዓ​ምደ ወርቁ አጠ​ገብ ቆሞ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ይከ​ተሉ ዘንድ፥ ትእ​ዛ​ዙ​ንና ምስ​ክ​ሩ​ንም ሥር​ዐ​ቱ​ንም በፍ​ጹም ልባ​ቸ​ውና በፍ​ጹም ነፍ​ሳ​ቸው ይጠ​ብቁ ዘንድ፥ በዚ​ህም መጽ​ሐፍ የተ​ጻ​ፈ​ውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸኑ ዘንድ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ቃል ኪዳን አደ​ረገ፤ ሕዝ​ቡም ሁሉ በቃል ኪዳን ጸኑ።
4ንጉ​ሡም የካ​ህ​ና​ቱን አለቃ ኬል​ቅ​ያ​ስን በሁ​ለ​ተ​ኛ​ውም መዓ​ርግ ያሉ​ትን ካህ​ናት በረ​ኞ​ቹ​ንም፥ ለበ​ዓ​ልና ለማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀድ ለሰ​ማ​ይም ሠራ​ዊት ሁሉ የተ​ሠ​ሩ​ትን ዕቃ​ዎች ሁሉ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መቅ​ደስ ያወጡ ዘንድ አዘ​ዛ​ቸው፤ ከኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ውጭ በቄ​ድ​ሮን ሜዳ አቃ​ጠ​ሉት፤ አመ​ዱ​ንም ወደ ቤቴል ወሰ​ዱት። 5የይ​ሁዳ ነገ​ሥ​ታ​ትም በይ​ሁዳ ከተ​ሞች በነ​በ​ሩት በኮ​ረ​ብ​ታው መስ​ገ​ጃ​ዎች፥ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ዙሪያ ባሉ መስ​ገ​ጃ​ዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖ​ሩ​አ​ቸ​ውን የጣ​ዖ​ቱን ካህ​ናት፥ ለበ​ዓ​ልና ለፀ​ሐይ፥ ለጨ​ረ​ቃና ለከ​ዋ​ክ​ብት ለሰ​ማ​ይም ሠራ​ዊት ሁሉ ያጥኑ የነ​በ​ሩ​ትን አቃ​ጠ​ላ​ቸው። 6የማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀ​ድ​ንም ጣዖት ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም ውጭ ወደ ቄድ​ሮን ፈፋ አወ​ጣው፤ በቄ​ድ​ሮ​ንም ፈፋ አጠ​ገብ አቃ​ጠ​ለው፤ አድ​ቅ​ቆም ትቢያ አደ​ረ​ገው፥ ትቢ​ያ​ው​ንም በሕ​ዝብ መቃ​ብር ላይ ጨመ​ረው። 7ሴቶ​ቹም ለማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀድ መጋ​ረጃ ይፈ​ት​ሉ​ባ​ቸው የነ​በ​ሩ​ትን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት ውስጥ ያሉ​ትን የሰ​ዶ​ማ​ው​ያ​ንን ቤቶች አፈ​ረሰ። 8ካህ​ና​ቱ​ንም ሁሉ ከይ​ሁዳ ከተ​ሞች አወ​ጣ​ቸው፤ ከጌ​ባ​ልም ጀምሮ እስከ ቤር​ሳ​ቤህ ድረስ ካህ​ናት ያጥ​ኑ​በት የነ​በ​ረ​ውን የኮ​ረ​ብታ መስ​ገጃ ሁሉ ርኩስ አደ​ረ​ገው። በከ​ተ​ማ​ዪ​ቱም በር በግራ በኩል በነ​በ​ረው በከ​ተ​ማ​ዪቱ ሹም በኢ​ያሱ በር መግ​ቢያ አጠ​ገብ የነ​በ​ሩ​ትን የበ​ሮ​ቹን መስ​ገ​ጃ​ዎች አፈ​ረሰ። 9የኮ​ረ​ብ​ታው መስ​ገ​ጃ​ዎች ካህ​ናት ግን በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ወዳ​ለው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሠ​ዊያ አይ​መ​ጡም ነበር፤ ብቻ በወ​ን​ድ​ሞ​ቻ​ቸው መካ​ከል ቂጣ እን​ጀራ ይበሉ ነበር። 10ሰው ሁሉ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞ​ሎክ በእ​ሳት እን​ዲ​ሠዋ በሄ​ኖም ልጅ ሸለቆ ቆሞ የነ​በ​ረ​ውን ጣፌ​ትን ርኩስ አደ​ረ​ገው። 11የይ​ሁ​ዳም ነገ​ሥ​ታት በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት መግ​ቢያ አጠ​ገብ በከ​ተ​ማው አቅ​ራ​ቢያ በነ​በ​ረው በን​ጉሡ ጃን​ደ​ረባ በና​ታን መኖ​ሪያ አጠ​ገብ ለፀ​ሐይ የሰ​ጡ​አ​ቸ​ውን ፈረ​ሶች አቃ​ጠለ፤ የፀ​ሐ​ይ​ንም ሰረ​ገ​ሎች በእ​ሳት አቃ​ጠለ። 12የይ​ሁ​ዳም ነገ​ሥ​ታት ያሠ​ሩ​ትን በአ​ካዝ ቤት ሰገ​ነት ላይ የነ​በ​ሩ​ትን መሠ​ዊ​ያ​ዎች፥ ምና​ሴም ያሠ​ራ​ውን በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት በሁ​ለቱ ወለ​ሎች ላይ የነ​በ​ሩ​ትን መሠ​ዊ​ያ​ዎች ንጉሡ አስ​ፈ​ረ​ሳ​ቸው፤ ከዚ​ያም አወ​ረ​ዳ​ቸው፤ አደ​ቀ​ቃ​ቸ​ውም፥ ትቢ​ያ​ቸ​ው​ንም በቄ​ድ​ሮን ፈፋ ጣለ። 13በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ፊት ለፊት በር​ኵ​ስት ተራራ ቀኝ የነ​በ​ሩ​ትን፥ የእ​ስ​ራ​ኤል ንጉሥ ሰሎ​ሞን ለሲ​ዶ​ና​ው​ያን ርኵ​ስት ለአ​ስ​ታ​ሮት፥ ለሞ​ዓ​ብም ርኵ​ሰት ለካ​ሞሽ፥ ለአ​ሞ​ንም ልጆች ርኵ​ሰት ለሞ​ሎክ ያሠ​ራ​ቸ​ውን መስ​ገ​ጃ​ዎች ንጉሡ ርኩስ አደ​ረገ። 14ሐው​ል​ቶ​ቹ​ንም ሁሉ አደ​ቀቀ፥ የማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀ​ዶ​ቹ​ንም ሁሉ ቈረጠ፤ በስ​ፍ​ራ​ቸ​ውም የሙ​ታ​ንን አጥ​ንት ሞላ​በት።
15ደግ​ሞም በቤ​ቴል ኮረ​ብታ የነ​በ​ረ​ውን መሠ​ዊያ፥ እስ​ራ​ኤ​ል​ንም ያሳተ የና​ባጥ ልጅ ኢዮ​ር​ብ​ዓም ያሠ​ራ​ውን የኮ​ረ​ብ​ታ​ውን መስ​ገጃ፥ ይህ​ንም መሠ​ዊ​ያና መስ​ገጃ አፈ​ረሰ፤ ድን​ጋ​ዮ​ቹ​ንም ሰባ​በረ፤ አድ​ቅ​ቆም ትቢያ አደ​ረ​ገው፤ የማ​ም​ለ​ኪያ ዐፀ​ዱ​ንም አቃ​ጠ​ለው። 16ኢዮ​ስ​ያ​ስም ዘወር ብሎ በከ​ተ​ማው የነ​በ​ሩ​ትን መቃ​ብ​ሮች አየ፤ ኢዮ​ር​ብ​ዓ​ምም በበ​ዓል ጊዜ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው እንደ ተና​ገ​ረው እንደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቃል፥ ልኮ ከመ​ቃ​ብ​ሮቹ አጥ​ን​ቶ​ቹን አስ​ወጣ፥ በመ​ሠ​ዊ​ያው ላይም አቃ​ጠ​ላ​ቸው፥ አረ​ከ​ሰ​ውም። ዘወ​ርም ብሎ ይህን ቃል ወደ ተና​ገ​ረው ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው መቃ​ብር ዐይ​ኖ​ቹን አቀና። እን​ዲ​ህም አለ፦ 17“ይህ የማ​የው የተ​ቀ​በረ ነገር ምን​ድን ነው?” አለ የዚ​ያ​ችም ከተማ ሰዎች፥ “ከይ​ሁዳ መጥቶ በቤ​ቴል መሠ​ዊያ ላይ ይህን ያደ​ረ​ግ​ኸ​ውን ነገር የተ​ና​ገ​ረው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ሰው መቃ​ብር ነው” ብለው ነገ​ሩት። 18እር​ሱም፥ “ተዉት፥ ማንም አጥ​ን​ቱን አያ​ን​ቀ​ሳ​ቅ​ሰው” አለ፤ አጥ​ን​ቶ​ቹም ከሰ​ማ​ርያ ከመ​ጣው ከነ​ቢዩ አጥ​ንት ጋር ዳኑ። 19በሰ​ማ​ር​ያም ከተ​ሞች የነ​በ​ሩ​ትን፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ያስ​ቈ​ጡት ዘንድ የእ​ስ​ራ​ኤል ነገ​ሥ​ታት የሠ​ሩ​ትን የኮ​ረ​ብ​ታ​ውን መስ​ገ​ጃ​ዎች ኢዮ​ስ​ያስ አስ​ወ​ገ​ዳ​ቸው፤ በቤ​ቴ​ልም እን​ዳ​ደ​ረ​ገው ነገር ሁሉ እን​ዲሁ አደ​ረ​ገ​ባ​ቸው። 20በዚ​ያም የነ​በ​ሩ​ትን የኮ​ረ​ብ​ታ​ውን መስ​ገ​ጃ​ዎች ካህ​ናት ሁሉ በመ​ሠ​ዊ​ያ​ዎቹ ላይ ገደ​ላ​ቸው፥ የሰ​ዎ​ቹ​ንም አጥ​ንት በመ​ሠ​ዊ​ያ​ዎቹ ላይ አቃ​ጠለ። ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ተመ​ለሰ።
ኢዮ​ስ​ያስ የፋ​ሲ​ካን በዓል እንደ አደ​ረገ
(2ዜ.መ. 35፥1-19)
21ንጉ​ሡም ሕዝ​ቡን ሁሉ፥ “በዚህ በቃል ኪዳኑ መጽ​ሐፍ እንደ ተጻ​ፈው ለአ​ም​ላ​ካ​ችሁ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፋሲ​ካን አድ​ርጉ” ብሎ አዘ​ዛ​ቸው። 22እን​ደ​ዚ​ህም ያለ ፋሲካ በእ​ስ​ራ​ኤል ላይ ይፈ​ርዱ ከነ​በሩ ከመ​ሳ​ፍ​ንት ዘመን ጀምሮ በእ​ስ​ራ​ኤ​ልና በይ​ሁዳ ነገ​ሥ​ታት ዘመን ሁሉ አል​ተ​ደ​ረ​ገም። 23ነገር ግን በይ​ሁዳ ንጉሥ በኢ​ዮ​ስ​ያስ በዐ​ሥራ ስም​ን​ተ​ኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ተደ​ረገ።
24ደግ​ሞም ካህኑ ኬል​ቅ​ያስ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ቤት ባገ​ኘው መጽ​ሐፍ የተ​ጻ​ፈ​ውን የሕ​ጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መና​ፍ​ስት ጠሪ​ዎ​ቹ​ንና ጠን​ቋ​ዮ​ቹን ተራ​ፊ​ም​ንና ጣዖ​ታ​ት​ንም በይ​ሁዳ ሀገ​ርና በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌም የተ​ገ​ኘ​ውን ርኵ​ሰት ሁሉ ኢዮ​ስ​ያስ አስ​ወ​ገደ። 25እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍ​ጹም ልቡ በፍ​ጹ​ምም ነፍሱ በፍ​ጹ​ምም ኀይሉ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የተ​መ​ለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእ​ርሱ አስ​ቀ​ድሞ አል​ነ​በ​ረም፤ እንደ እር​ሱም ያለ ንጉሥ ከእ​ርሱ በኋላ አል​ተ​ነ​ሣም።
26ነገር ግን ምናሴ ስላ​ስ​ቈ​ጣው ነገር ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር በይ​ሁዳ ላይ ከነ​ደ​ደው ከታ​ላቁ ቍጣው ትኵ​ሳት አል​ተ​መ​ለ​ሰም። 27እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም፥ “እስ​ራ​ኤ​ልን እን​ዳ​ራ​ቅ​ሁት ይሁ​ዳን ከፊቴ አር​ቀ​ዋ​ለሁ፤ ይህ​ች​ንም የመ​ረ​ጥ​ኋ​ትን ከተማ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ም​ንና፦ ስሜ በዚያ ይሆ​ናል ያል​ሁ​ት​ንም ቤት እጥ​ላ​ለሁ” አለ።
28የቀ​ረ​ውም የኢ​ዮ​ስ​ያስ ነገር፥ የሠ​ራ​ውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይ​ሁዳ ነገ​ሥ​ታት የታ​ሪክ መጽ​ሐፍ የተ​ጻፈ አይ​ደ​ለ​ምን? 29በእ​ር​ሱም ዘመን የግ​ብፅ ንጉሥ ፈር​ዖን ኒካዑ ከአ​ሦር ንጉሥ ጋር ሊጋ​ጠም ወደ ኤፍ​ራ​ጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉ​ሡም ኢዮ​ስ​ያስ ከእ​ርሱ ጋር ሊጋ​ጠም ወጣ፤ ፈር​ዖ​ንም በተ​ገ​ና​ኘው ጊዜ በመ​ጊዶ ገደ​ለው። 30አገ​ል​ጋ​ዮ​ቹም በድ​ኑን በሰ​ረ​ገ​ላው አድ​ር​ገው ከመ​ጊዶ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌም አመ​ጡት፤ በመ​ቃ​ብ​ሩም ቀበ​ሩት። የሀ​ገ​ሩም ሰዎች የኢ​ዮ​ስ​ያ​ስን ልጅ ዮአ​ክ​ስን ወሰ​ዱት። ቀብ​ተ​ውም በአ​ባቱ ፋንታ አነ​ገ​ሡት።
የዮ​አ​ክስ ዘመነ መን​ግ​ሥት
(2ዜ.መ. 36፥2-4)
31ዮአ​ክ​ስም በነ​ገሠ ጊዜ ሃያ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ሦስት ወር ነገሠ። እና​ቱም አሚ​ጣል ትባል ነበር፥ እር​ስ​ዋም የሎ​ብና ሰው የኤ​ር​ም​ያስ ልጅ ነበ​ረች። 32እር​ሱም አባ​ቶቹ እንደ አደ​ረጉ ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ክፉ አደ​ረገ። 33በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም እን​ዳ​ይ​ነ​ግሥ ፈር​ዖን ኒካዑ በኤ​ማት ምድር ባለ​ችው በዴ​ብ​ላታ አሰ​ረው፤ በም​ድ​ሩም ላይ መቶ መክ​ሊት ብርና አንድ መቶ መክ​ሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለ​በት። 34ፈር​ዖን ኒካ​ዑም የይ​ሁዳ ንጉሥ የኢ​ዮ​ስ​ያ​ስን ልጅ ኤል​ያ​ቄ​ምን በአ​ባቱ በኢ​ዮ​ስ​ያስ ፋንታ አነ​ገሠ፤ ስሙ​ንም ኢዮ​አ​ቄም ብሎ ለወ​ጠው። ዮአ​ክ​ስ​ንም ወስዶ ወደ ግብፅ አፈ​ለ​ሰው፤ በዚ​ያም ሞተ። 35ኢዮ​አ​ቄ​ምም ብሩ​ንና ወር​ቁን ለፈ​ር​ዖን ሰጠው፤ እንደ ፈር​ዖ​ንም ትእ​ዛዝ ገን​ዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድ​ሩን አስ​ገ​በረ፤ ለፈ​ር​ዖን ኒካ​ዑም ግብር ይሰጥ ዘንድ ከሀ​ገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግም​ጋ​ሜው ብርና ወርቅ አስ​ከ​ፈለ።
የኢ​ዮ​አ​ቄም ዘመነ መን​ግ​ሥት
(2ዜ.መ. 36፥5-8)
36ኢዮ​አ​ቄ​ምም በነ​ገሠ ጊዜ ሃያ አም​ስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢ​የ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እና​ቱም ሄል​ድፍ ትባል ነበር፤ እር​ስ​ዋም የሩማ ሰው የፈ​ዳያ ልጅ ነበ​ረች። 37አባ​ቶ​ቹም እን​ዳ​ደ​ረጉ ሁሉ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት ክፉ አደ​ረገ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ከ መጽ​ሐፈ ነገ​ሥት ካልእ 23ጋር የተዛመዱ ነፃ የንባብ እቅዶች እና ምንባቦች

YouVersion የእርስዎን ተሞክሮ ግላዊ ለማድረግ ኩኪዎችን ይጠቀማል። የእኛን ድረ ገጽ በመጠቀም፣ በግለሰብነት መመሪያችን ላይ እንደተገለጸው የእኛን የኩኪዎች አጠቃቀም ተቀብለዋል