መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 23
23
ንጉሡ ኢዮስያስ አምልኮ ጣዖትን እንደ አስወገደ
(2ዜ.መ. 34፥3-7፤29-33)
1ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምንም ሽማግሌዎች ሁሉ ወደ እርሱ ሰበሰባቸው። 2ንጉሡም ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጣ፤ ከእርሱም ጋር የይሁዳ ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ ሁሉ፥ ካህናቱና ነቢያቱም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሾቹ ጀምሮ እስከ ታላቆቹ ድረስ ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 3ንጉሡም በዓምደ ወርቁ አጠገብ ቆሞ እግዚአብሔርን ይከተሉ ዘንድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩንም ሥርዐቱንም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ይጠብቁ ዘንድ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸኑ ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ፤ ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳን ጸኑ።
4ንጉሡም የካህናቱን አለቃ ኬልቅያስን በሁለተኛውም መዓርግ ያሉትን ካህናት በረኞቹንም፥ ለበዓልና ለማምለኪያ ዐፀድ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ የተሠሩትን ዕቃዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር መቅደስ ያወጡ ዘንድ አዘዛቸው፤ ከኢየሩሳሌምም ውጭ በቄድሮን ሜዳ አቃጠሉት፤ አመዱንም ወደ ቤቴል ወሰዱት። 5የይሁዳ ነገሥታትም በይሁዳ ከተሞች በነበሩት በኮረብታው መስገጃዎች፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ባሉ መስገጃዎች ያጥኑ ዘንድ ያኖሩአቸውን የጣዖቱን ካህናት፥ ለበዓልና ለፀሐይ፥ ለጨረቃና ለከዋክብት ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ያጥኑ የነበሩትን አቃጠላቸው። 6የማምለኪያ ዐፀድንም ጣዖት ከእግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ቄድሮን ፈፋ አወጣው፤ በቄድሮንም ፈፋ አጠገብ አቃጠለው፤ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፥ ትቢያውንም በሕዝብ መቃብር ላይ ጨመረው። 7ሴቶቹም ለማምለኪያ ዐፀድ መጋረጃ ይፈትሉባቸው የነበሩትን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ያሉትን የሰዶማውያንን ቤቶች አፈረሰ። 8ካህናቱንም ሁሉ ከይሁዳ ከተሞች አወጣቸው፤ ከጌባልም ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ ካህናት ያጥኑበት የነበረውን የኮረብታ መስገጃ ሁሉ ርኩስ አደረገው። በከተማዪቱም በር በግራ በኩል በነበረው በከተማዪቱ ሹም በኢያሱ በር መግቢያ አጠገብ የነበሩትን የበሮቹን መስገጃዎች አፈረሰ። 9የኮረብታው መስገጃዎች ካህናት ግን በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ አይመጡም ነበር፤ ብቻ በወንድሞቻቸው መካከል ቂጣ እንጀራ ይበሉ ነበር። 10ሰው ሁሉ ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን ለሞሎክ በእሳት እንዲሠዋ በሄኖም ልጅ ሸለቆ ቆሞ የነበረውን ጣፌትን ርኩስ አደረገው። 11የይሁዳም ነገሥታት በእግዚአብሔር ቤት መግቢያ አጠገብ በከተማው አቅራቢያ በነበረው በንጉሡ ጃንደረባ በናታን መኖሪያ አጠገብ ለፀሐይ የሰጡአቸውን ፈረሶች አቃጠለ፤ የፀሐይንም ሰረገሎች በእሳት አቃጠለ። 12የይሁዳም ነገሥታት ያሠሩትን በአካዝ ቤት ሰገነት ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች፥ ምናሴም ያሠራውን በእግዚአብሔር ቤት በሁለቱ ወለሎች ላይ የነበሩትን መሠዊያዎች ንጉሡ አስፈረሳቸው፤ ከዚያም አወረዳቸው፤ አደቀቃቸውም፥ ትቢያቸውንም በቄድሮን ፈፋ ጣለ። 13በኢየሩሳሌምም ፊት ለፊት በርኵስት ተራራ ቀኝ የነበሩትን፥ የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ለሲዶናውያን ርኵስት ለአስታሮት፥ ለሞዓብም ርኵሰት ለካሞሽ፥ ለአሞንም ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ ያሠራቸውን መስገጃዎች ንጉሡ ርኩስ አደረገ። 14ሐውልቶቹንም ሁሉ አደቀቀ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ሁሉ ቈረጠ፤ በስፍራቸውም የሙታንን አጥንት ሞላበት።
15ደግሞም በቤቴል ኮረብታ የነበረውን መሠዊያ፥ እስራኤልንም ያሳተ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓም ያሠራውን የኮረብታውን መስገጃ፥ ይህንም መሠዊያና መስገጃ አፈረሰ፤ ድንጋዮቹንም ሰባበረ፤ አድቅቆም ትቢያ አደረገው፤ የማምለኪያ ዐፀዱንም አቃጠለው። 16ኢዮስያስም ዘወር ብሎ በከተማው የነበሩትን መቃብሮች አየ፤ ኢዮርብዓምም በበዓል ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል፥ ልኮ ከመቃብሮቹ አጥንቶቹን አስወጣ፥ በመሠዊያው ላይም አቃጠላቸው፥ አረከሰውም። ዘወርም ብሎ ይህን ቃል ወደ ተናገረው ወደ እግዚአብሔር ሰው መቃብር ዐይኖቹን አቀና። እንዲህም አለ፦ 17“ይህ የማየው የተቀበረ ነገር ምንድን ነው?” አለ የዚያችም ከተማ ሰዎች፥ “ከይሁዳ መጥቶ በቤቴል መሠዊያ ላይ ይህን ያደረግኸውን ነገር የተናገረው የእግዚአብሔር ሰው መቃብር ነው” ብለው ነገሩት። 18እርሱም፥ “ተዉት፥ ማንም አጥንቱን አያንቀሳቅሰው” አለ፤ አጥንቶቹም ከሰማርያ ከመጣው ከነቢዩ አጥንት ጋር ዳኑ። 19በሰማርያም ከተሞች የነበሩትን፥ እግዚአብሔርን ያስቈጡት ዘንድ የእስራኤል ነገሥታት የሠሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ኢዮስያስ አስወገዳቸው፤ በቤቴልም እንዳደረገው ነገር ሁሉ እንዲሁ አደረገባቸው። 20በዚያም የነበሩትን የኮረብታውን መስገጃዎች ካህናት ሁሉ በመሠዊያዎቹ ላይ ገደላቸው፥ የሰዎቹንም አጥንት በመሠዊያዎቹ ላይ አቃጠለ። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
ኢዮስያስ የፋሲካን በዓል እንደ አደረገ
(2ዜ.መ. 35፥1-19)
21ንጉሡም ሕዝቡን ሁሉ፥ “በዚህ በቃል ኪዳኑ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካን አድርጉ” ብሎ አዘዛቸው። 22እንደዚህም ያለ ፋሲካ በእስራኤል ላይ ይፈርዱ ከነበሩ ከመሳፍንት ዘመን ጀምሮ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ዘመን ሁሉ አልተደረገም። 23ነገር ግን በይሁዳ ንጉሥ በኢዮስያስ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህ ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለእግዚአብሔር ተደረገ።
24ደግሞም ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፈውን የሕጉን ቃል ያጸና ዘንድ፥ መናፍስት ጠሪዎቹንና ጠንቋዮቹን ተራፊምንና ጣዖታትንም በይሁዳ ሀገርና በኢየሩሳሌም የተገኘውን ርኵሰት ሁሉ ኢዮስያስ አስወገደ። 25እንደ ሙሴም ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ በፍጹምም ነፍሱ በፍጹምም ኀይሉ ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ እንደ እርሱ ያለ ንጉሥ ከእርሱ አስቀድሞ አልነበረም፤ እንደ እርሱም ያለ ንጉሥ ከእርሱ በኋላ አልተነሣም።
26ነገር ግን ምናሴ ስላስቈጣው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር በይሁዳ ላይ ከነደደው ከታላቁ ቍጣው ትኵሳት አልተመለሰም። 27እግዚአብሔርም፥ “እስራኤልን እንዳራቅሁት ይሁዳን ከፊቴ አርቀዋለሁ፤ ይህችንም የመረጥኋትን ከተማ ኢየሩሳሌምንና፦ ስሜ በዚያ ይሆናል ያልሁትንም ቤት እጥላለሁ” አለ።
28የቀረውም የኢዮስያስ ነገር፥ የሠራውም ሥራ ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29በእርሱም ዘመን የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ ከአሦር ንጉሥ ጋር ሊጋጠም ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ወጣ፤ ንጉሡም ኢዮስያስ ከእርሱ ጋር ሊጋጠም ወጣ፤ ፈርዖንም በተገናኘው ጊዜ በመጊዶ ገደለው። 30አገልጋዮቹም በድኑን በሰረገላው አድርገው ከመጊዶ ወደ ኢየሩሳሌም አመጡት፤ በመቃብሩም ቀበሩት። የሀገሩም ሰዎች የኢዮስያስን ልጅ ዮአክስን ወሰዱት። ቀብተውም በአባቱ ፋንታ አነገሡት።
የዮአክስ ዘመነ መንግሥት
(2ዜ.መ. 36፥2-4)
31ዮአክስም በነገሠ ጊዜ ሃያ ሦስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሦስት ወር ነገሠ። እናቱም አሚጣል ትባል ነበር፥ እርስዋም የሎብና ሰው የኤርምያስ ልጅ ነበረች። 32እርሱም አባቶቹ እንደ አደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ። 33በኢየሩሳሌምም እንዳይነግሥ ፈርዖን ኒካዑ በኤማት ምድር ባለችው በዴብላታ አሰረው፤ በምድሩም ላይ መቶ መክሊት ብርና አንድ መቶ መክሊት ወርቅ ፈሰሴ ጣለበት። 34ፈርዖን ኒካዑም የይሁዳ ንጉሥ የኢዮስያስን ልጅ ኤልያቄምን በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሠ፤ ስሙንም ኢዮአቄም ብሎ ለወጠው። ዮአክስንም ወስዶ ወደ ግብፅ አፈለሰው፤ በዚያም ሞተ። 35ኢዮአቄምም ብሩንና ወርቁን ለፈርዖን ሰጠው፤ እንደ ፈርዖንም ትእዛዝ ገንዘብ ይሰጥ ዘንድ ምድሩን አስገበረ፤ ለፈርዖን ኒካዑም ግብር ይሰጥ ዘንድ ከሀገሩ ሕዝብ ሁሉ እንደ ግምጋሜው ብርና ወርቅ አስከፈለ።
የኢዮአቄም ዘመነ መንግሥት
(2ዜ.መ. 36፥5-8)
36ኢዮአቄምም በነገሠ ጊዜ ሃያ አምስት ዓመት ሆኖት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ አንድ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም ሄልድፍ ትባል ነበር፤ እርስዋም የሩማ ሰው የፈዳያ ልጅ ነበረች። 37አባቶቹም እንዳደረጉ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 23: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ