ኢዮስያስም ለአምላኩ ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ አረዱ። ካህናቱንም በየሥርዐታቸው አቆመ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። በእስራኤልም ሁሉ መሥራት የሚችሉትን ሌዋውያን ራሳቸውን ለእግዚአብሔር እንዲያነጹና ቅድስቲቱንም ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ እንዲያኖሩ አዘዛቸው። ንጉሡም ኢዮስያስ አለ፥ “በትከሻችሁ የምትሸከሙት አንዳች ነገር አይኑር፤ አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊት እንደ አዘዘ፥ ልጁም ሰሎሞን እንደ አዘዘ በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ፤ እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶች ቤቶች አከፋፈል በመቅደሱ ቁሙ፤ እንዲሁም ለሌዋውያን በየአባቶቻቸው ቤት አከፋፈል ይሁን፤ የፋሲካውንም በግ እረዱ፤ እናንተም ተቀደሱ፥ እግዚአብሔርም በሙሴ እጅ የተናገረውን ቃል ታደርጉ ዘንድ ለወንድሞቻችሁ አዘጋጁ።” ኢዮስያስም ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን በዚያ ለነበሩት ለሕዝቡ ልጆች ከመንጋው ሠላሳ ሺህ የበግና የፍየል ጠቦቶች፥ ሦስት ሺህም ወይፈኖች ሰጣቸው፤ እነዚህም ከንጉሡ ሀብት ነበሩ። አለቆቹም ለሕዝቡና ለካህናቱ፥ ለሌዋውያኑም በፈቃዳቸው ሰጡ፤ የእግዚአብሔርም ቤት አለቆች፥ ኬልቅያስ፥ ዘካርያስ፥ ኢዮሔል፥ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችንና ፍየሎችን፥ ሦስት መቶም በሬዎችን ለካህናቱ ሰጡ። የሌዋውያኑም አለቆች ኮኒንያስ በንያስም፥ ወንድሞቹም ሰማዕያስና ናትናኤል፥ ሰብንያስ፥ ኢዮሄል፥ ኢዮዛብድ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆን አምስት ሺህ በጎችን፥ አምስት መቶም በሬዎችን ለሌዋውያን ሰጡ። አገልግሎቱም ተዘጋጀ፤ ካህናቱም በየስፍራቸው፥ ሌዋውያኑም በየክፍላቸው እንደ ንጉሡ ትእዛዝ ቆሙ። የፋሲካውንም በግ አረዱ፤ ካህናቱም ከእጃቸው የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም ቍርበቱን ገፈፉ። በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈ ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደ ክፍላቸው ለሕዝቡ ልጆች እንዲሰጡ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ። እንዲሁም በበሬዎቹ አደረጉ። የፋሲካውንም በግ እንደ ሙሴ ሥርዐት በእሳት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸትና በሰታቴ፥ በድስትም ቀቀሉ፤ ተከናወነላቸውም፤ ለሕዝቡም ልጆች ሁሉ በፍጥነት አደረሱ። ከዚያም በኋላ ለራሳቸውና ከእነርሱ ጋር ላሉ ለካህናቱ አዘጋጁ፤ የአሮንም ልጆች ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን ለማቅረብ እስከ ሌሊት ድረስ ይሠሩ ነበርና ስለዚህ ሌዋውያን ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ለካህናቱ አዘጋጁ። የአሳፍም ልጆች መዘምራን እንደ ዳዊት፥ እንደ አሳፍም፥ እንደ ኤማንም የንጉሡም ባለ ራእይ እንደ ነበረው እንደ ኤዶትም ትእዛዝ በየስፍራቸው ነበሩ፤ በረኞቹም በሮቹን ሁሉ ይጠብቁ ነበር፤ ወንድሞቻቸውም ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና ከአገልግሎታቸው ይርቁ ዘንድ አያስፈልጋቸውም ነበር።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 35:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች