መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 34
34
የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 22፥1-2)
1ኢዮስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የስምንት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ አንድ ዓመት ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ በአባቱም በዳዊት መንገድ ሄደ፤ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አላለም። 3በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመረ፤ በዐሥራ ሁለተኛውም ዓመት ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታውና ከዐፀዶቹ፥ ከተቀረጹትና ቀልጠው ከተሠሩት ምስሎች ያነጻ ጀመር። 4የበዓሊምንም መሠዊያዎች በፊቱ አፈረሰ፤ በላዩም የነበሩትን ኮረብታዎችን ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የተቀረጹትንና ቀልጠው የተሠሩትንም ምስሎች ሰባበረ፤ አደቀቃቸውም፤ ይሠዉላቸው በነበሩት ሰዎች መቃብርም ላይ በተናቸው። 5የካህኖቻቸውንም አጥንት በመሠዊያቸው ላይ አቃጠለ። ይሁዳንና ኢየሩሳሌምንም አነጻ። 6የምናሴንና የኤፍሬምንም፥ የስምዖንና የንፍታሌምንም ከተሞች፥ በዙሪያቸውም ያለውን ቦታ እንዲሁ አነጻ። 7መሠዊያዎቹንም አፈረሰ፤ የማምለኪያ#“የማምለኪያ” የሚለው በዕብ. ብቻ። ዐፀዶቹንና የተቀረጹትን ምስሎችም አደቀቀ፤ በእስራኤልም ሀገር ሁሉ የኮረብታዎችን መስገጃዎችአጠፋ።#ዕብ. “የፀሐይን ምስሎች ሁሉ ቈራረጠ” ይላል። ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሰ።
8በነገሠም በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ምድሪቱንና የእግዚአብሔርን ቤት ካነጻ በኋላ፥ የሴልያ ልጅ ሳፋን፥ የከተማዪቱም አለቃ መዕሴያ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የኢዮአካዝ ልጅ ኢዮአክ የእግዚአብሔርን የአምላኩን ቤት ይጠግኑ ዘንድ ሰደዳቸው። 9ወደ ታላቁም ካህን ወደ ኬልቅያስ መጡ፤ ሌዋውያኑም በረኞች ከምናሴና ከኤፍሬም፥ ከአለቆችም፥ ከቀረውም ከእስራኤል ሁሉ፥ ከይሁዳና ከብንያም ሁሉ በኢየሩሳሌምም ከሚኖሩት የሰበሰቡትን፥ ወደ እግዚአብሔር ቤት የቀረበውን ገንዘብ ሰጡት። 10የእግዚአብሔርንም ቤት በሚሠሩት ላይ ለተሾሙት ሰጡ፤ እነርሱም ይጠግኑና ያድሱ ዘንድ የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠሩ ሠራተኞች ሰጡአቸው። 11የይሁዳ ነገሥታት ላፈረሱት ቤት ሰረገሎች ያደርጉ ዘንድ፥ ለማጋጠሚያም እንጨት፥ የተጠረበውንም ድንጋይ ይገዙ ዘንድ ለአናጢዎችና ለጠራቢዎች ሰጡ።
12ሰዎቹም ሥራውን በመታመን አደረጉ፤ በእነርሱም ላይ የተሾሙት፥ ሥራውንም የሚያሠሩት ሌዋውያን ከሜራሪ ልጆች ይኤትና አብድያስ፥ ከቀዓትም ልጆች ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። ከሌዋውያንም ወገን በዜማ ዕቃ ዐዋቂዎች፥ የነበሩ ሁሉ፥ 13በተሸካሚዎችና ልዩ ልዩ ሥራ በሚሠሩ ላይ ተሾመው ነበር፤ ጸሓፊዎቹና አለቆቹም በረኞቹም ከሌዋውያን ወገን ነበሩ።
ካህኑ ኬልቅያስ የሕጉን መጽሐፍ እንደ አገኘ
(2ነገ. 22፥3-20)
14ወደ እግዚአብሔርም ቤት የቀረበውን ገንዘብ ባመጡ ጊዜ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ። 15ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፥ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤት አግኝቼአለሁ” ብሎ ነገረው። ኬልቅያስም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው። 16ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ አመጣ፤ ለንጉሡም ዳግመኛ እንዲህ አለው፥ “ወርቁንና ብሩን፥ መባውንም ሁሉ#“ወርቁንና ብሩን፥ መባውንም ሁሉ” የሚለው በዕብ. የለም “ወርቅና መባ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። የቤተ እግዚአብሔርን#“የቤተ እግዚአብሔርን” የሚለው በግእዝ ብቻ። ሥራ ለሚሠሩ ለአገልጋዮችህ በእጃቸው ሰጧቸው። 17በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን ገንዘብ አፈሰሱ፤ በሥራው ላይ ለተሾሙትና ለሠራተኞቹም በእጃቸው ሰጡ።” 18ጸሓፊውም ሳፋን ለንጉሡ፥ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጠኝ” ብሎ ነገረው። ሳፋንም በንጉሡ ፊት አነበበው። 19ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ። 20ንጉሡም ኬልቅያስን፥ የሳፋንንም ልጅ አኪቃምን፥ የሚክያስንም ልጅ አብዶንን፥ ጸሓፊውንም ሳፋንን፥ የንጉሡንም ብላቴና ዔሴኢያን፦ 21“በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ አባቶቻችን የእግዚአብሔርን ቃል ስላልጠበቁ፥ በላያችን የነደደ የእግዚአብሔር ቍጣ እጅግ ነውና ሄዳችሁ ስለ ተገኘው የመጽሐፍ ቃል ስለእኔ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ስለቀሩትም እግዚአብሔርን ጠይቁ” ብሎ አዘዛቸው።
22ኬልቅያስና እነዚያ ንጉሡ ያዘዛቸው ወደ ልብስ ጠባቂው ወደ ሐስራ ልጅ ወደ ቴቁዋ ልጅ ወደ ሴሌም ሚስት ወደ ነቢይቱ ወደ ሕልዳና ሄዱ፤ እርስዋም በኢየሩሳሌም በከተማዪቱ በሁለተኛው ክፍል ተቀምጣ ነበር፤ ይህንም ነገር ነገሩአት። 23እርስዋም አለቻቸው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ እኔ ለላካችሁ ሰው እንዲህ ብላችሁ ንገሩት፦ 24እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ እነሆ፥ በዚህ ስፍራና በሚኖሩበት ላይ በይሁዳ ንጉሥ ፊት በተነበበው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ፥ ማለት ክፉ ነገርን አመጣለሁ፥ 25በእጃቸው ሥራ ሁሉ ሊያስቈጡኝ ትተውኛልና፥ ለሌሎችም አማልክት አጥነዋልና ቍጣዬ በዚህ ስፍራ ላይ ይነድዳል፤ አይጠፋምም። 26እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ለላካችሁ ለይሁዳ ንጉሥ እንዲህ በሉት፦ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ስለ ሰማኸው ቃል ልብህ ደንግጦአልና፥ 27በፊቴም ራስህን አዋርደሃልና፥ በዚህም ስፍራ በሚኖሩበት ላይ ቃሌን በሰማህ ጊዜ ራስህን አዋርደሃልና፥ ልብስህንም ቀድደህ በፊቴ አልቅሰሃልና እኔ ደግሞ ሰምቼሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር። 28እነሆ፥ ወደ አባቶችህ እሰበስብሃለሁ፤ በሰላምም ወደ መቃብርህ ትሰበሰባለህ፤ በዚህም ስፍራና በሚኖሩበት ላይ የማመጣውን ክፉ ነገር ሁሉ ዐይኖችህ አያዩም” ያለቻቸውንም ነገር ለንጉሡ አስረዱት።
29ንጉሡም ላከ፤ የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ሽማግሌዎች ሁሉ ሰበሰበ። 30ንጉሡም፥ የይሁዳም ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ ሕዝቡም ሁሉ ከታናሹ ጀምሮ እስከ ታላቁ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወጡ፤ በእግዚአብሔርም ቤት የተገኘውን የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ በጆሮአቸው አነበበ። 31ንጉሡም በዐምዱ ቆሞ እግዚአብሔርን ተከትሎ እንዲሄድ፥ ትእዛዙንና ምስክሩን፥ ሥርዐቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ እንዲጠብቅ፥ በዚህም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል እንዲያደርግ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ። 32በኢየሩሳሌምና በብንያምም ሀገር የተገኙትን ሁሉ በዚህ ነገር አማለ። በኢየሩሳሌምም የሚኖሩ እንደ አባቶቻቸው አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቤት ቃል ኪዳን አደረጉ። 33ኢዮስያስም ከእስራኤል ልጆች ምድር ሁሉ ርኩሱን ሁሉ አስወገደ፤ በእስራኤልም የተገኙትን ሁሉ አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ አደረገ። በዘመኑ ሁሉ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል አልራቁም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 34: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ