መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 32
32
የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ኢየሩሳሌምን ለመውረር እንደ ተነሣ
(2ነገ. 18፥13-37፤ 19፥14-19፤35-37፤ ኢሳ. 36፥1-22፤ 37፥8-38)
1ከእነዚህም ነገሮችና ከዚህ እውነት በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም መጥቶ ወደ ይሁዳ ገባ፤ በተመሸጉትም ከተሞች ፊት ሰፈረ፤ ሊወስዳቸውም አሰበ። 2ሕዝቅያስም ሰናክሬም እንደ መጣ፥ ኢየሩሳሌምንም ሊወጋ ፊቱን እንዳቀና አየ፤ 3ከከተማዪቱ በስተውጭ ያለውን የውኃውን ምንጭ ይደፍኑ ዘንድ ከአለቆቹና ከኀያላኑ ጋር ተማከረ፤ እነርሱም ምክሩን ወደዱ። 4ብዙ ሰዎችንም ሰበሰበ፥ “የአሦርም ንጉሥ እንዳይመጣና ብዙ ውኃ አግኝቶ እንዳይጠነክር” ብሎ የውኃ ምንጮችንና በከተማዪቱ የሚፈስሱትን ወንዞች ደፈነ።#ዕብ. “ሕዝቡ ደፈኑት” ይላል። 5ሕዝቅያስም ሰውነቱን አጽናና፤ የፈረሰውንም ቅጥር ሁሉ ጠገነ፤ በላዩም ግንብ ሠራበት፤ ከእርሱም በስተውጭ ሌላ ቅጥር ሠራ፤ ወደ ዳዊትም ከተማ የሚያወጣውን በር#ዕብ. “ሚሎን” ይላል። አጠነከረ፤ ብዙም መሣሪያና ጋሻ አዘጋጀ። 6የጦር አለቆቹንም በሕዝቡ ላይ ሾመ፤ ሁሉንም በሸለቆው በኩል ባለው በከተማዪቱ በር አደባባይ ወደ እርሱ ሰበሰበ፤ እንዲህም ብሎ ልባቸውን አጸና፦ 7“ጽኑ፥ አይዞአችሁ፤ ከእኛ ጋር ያለው ከእርሱ ጋር ካለው ይበልጣልና ከአሦር ንጉሥና ከእርሱ ጋር ካለው ጭፍራ ሁሉ የተነሣ አትፍሩ፤ አትደንግጡም። 8ከእርሱ ጋር የሥጋ ክንድ ነው፤ ከእኛ ጋር ያለው ግን የሚረዳን የሚዋጋልንም አምላካችን እግዚአብሔር ነው።” ሕዝቡም በይሁዳ ንጉሥ በሕዝቅያስ ቃል ተጽናና።
9ከዚህም በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር በለኪሶ ፊት ሳለ ባሪያዎቹን ወደ ኢየሩሳሌም ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ ሕዝቅያስና በኢየሩሳሌም ወደ ነበሩ ወደ ይሁዳ ሕዝብ ሁሉ እንዲህ ሲል ላከ፦ 10“የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም እንዲህ ይላል፦ እናንተ በማን ተማምናችሁ በኢየሩሳሌም ምሽግ ትቀመጣላችሁ? 11አምላካችን እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ያድነናል እያለ ለራብ፥ ለጥምና ለሞት አሳልፎ ይሰጣችሁ ዘንድ የሚያሳስታችሁ ሕዝቅያስ አይደለምን? 12በዚህ መሠዊያ ፊት ስገዱ፤ በእርሱም ላይ ዕጠኑ፤ እያለ የይሁዳን ሕዝብና የኢየሩሳሌምን ነዋሪዎች አዝዞ፥ የኮረብታውን መስገጃዎችና መሠዊያዎቹን ያፈረሰ ይህ ሕዝቅያስ አይደለምን? 13እኔና አባቶች በምድር አሕዛብ ሁሉ ያደረግነውን አላወቃችሁምን? የምድርስ ሁሉ አሕዛብ አማልክት ሀገራቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ በውኑ ተቻላቸውን? 14አምላካችሁስ ከእጄ እናንተን ለማዳን ይችል ዘንድ አባቶች ካጠፉአቸው ከአሕዛብ አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ የቻለ ማን ነው? 15አሁንም ሕዝቅያስ አያስታችሁ፤ በእነዚህም ቃላት እንድትተማመኑ አያድርጋችሁ፤ አትመኑትም፤ ከአሕዛብና ከመንግሥታት አማልክት ሁሉ ሕዝቡን ከእጄና ከአባቶች እጅ ያድን ዘንድ ማንም አልቻለም፤ ስለዚህም አምላካችሁ ከእጄ ያድናችሁ ዘንድ አይችልም።”
16ባሪያዎቹም ደግሞ በአምላክ በእግዚአብሔርና በባሪያው በሕዝቅያስ ላይ ሌላ ብዙ ነገር ተናገሩ። 17ደግሞም የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን እየተገዳደረ በእርሱም ላይ እየተናገረ፥ “የምድር አሕዛብ አማልክት ሕዝባቸውን ከእጄ ያድኑ ዘንድ እንዳልቻሉ፥ እንዲሁ የሕዝቅያስ አምላክ ሕዝቡን ከእጄ ያድን ዘንድ አይችልም” የሚል ደብዳቤ ጻፈ። 18ቅጥሩን እንዲያፈርሱ ከተማዪቱንም እንዲወስዱ፥ በቅጥር ላይ የተቀመጡትን የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ያስፈራቸውና ያስደነግጣቸው ዘንድ በታላቅ ድምፅ በዕብራይስጥ ቋንቋ ይጮኽባቸው ነበር። 19በሰውም እጅ በተሠሩ በምድር አሕዛብ አማልክት ላይ እንደሚናገር መጠን በኢየሩሳሌም አምላክ ላይ ተናገረ።#ምዕ. 32 ከቍ. 18 እስከ 19 ያለው በዕብ. በብዙ ይናገራል።
20ንጉሡ ሕዝቅያስና የአሞጽ ልጅ ነቢዩ ኢሳይያስ ስለዚህ ተግዳሮት ጸለዩ፤ ወደ ሰማይም ጮኹ። 21እግዚአብሔርም መልአኩን ላከ፤ እርሱም ጽኑዓን ኀያላኑንና መሳፍንቱን አለቆቹንም ከአሦር ንጉሥ ሰፈር አጠፋ። የአሦርም ንጉሥ አፍሮ ወደ ሀገሩ ተመለሰ። ወደ አምላኩም ቤት በገባ ጊዜ ከወገቡ የወጡት ልጆቹ በዚያ በሰይፍ ገደሉት። 22እግዚአብሔርም ሕዝቅያስንና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ከአሦር ንጉሥ ከስናክሬም እጅና ከሁሉም እጅ አዳናቸው፤ በዙሪያቸውም ካለው ሁሉ አሳረፋቸው። 23ብዙዎቹም ለእግዚአብሔር መባ ይዘው ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር፤ ለይሁዳም ንጉሥ ለሕዝቅያስ እጅ መንሻ ይሰጡ ነበር፤ እርሱም ከዚህ ነገር በኋላ በሕዝብ ሁሉ ፊት ከፍ ከፍ አለ።
24በዚያም ወራት ሕዝቅያስ እስከ ሞት ድረስ ታመመ፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ እርሱም ሰማው፤ ምልክትም ሰጠው። 25ሕዝቅያስ ግን እግዚአብሔር እንደ ሰጠው ቸርነት መጠን አላደረገም፤ ልቡም ኮራ፤ ስለዚህም በእርሱና በይሁዳ፥ በኢየሩሳሌምም ላይ ቍጣ ሆነ። 26ሕዝቅያስም በኢየሩሳሌም ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ስለ ልቡ ኵራት ሰውነቱን አዋረደ፤ እግዚአብሔርም በሕዝቅያስ ዘመን ቍጣውን አላመጣባቸውም።
27ለሕዝቅያስም እጅግ ብዙ ሀብትና ክብር ነበረው፤ ለብርና ለወርቅም፥ ለከበረው ዕንቍና ለሽቱው፥ ለጋሻውና ውድ ለሆነው ዕቃ ሁሉ ግምጃ ቤቶችን ሠራ። 28ለእህልና ለወይን ጠጅም ለዘይትም ዕቃ ቤቶች፥ ለልዩ ልዩም እንስሳ ጋጥ፥ ለመንጎችም በረት ሠራ። 29እግዚአብሔርም እጅግ ብዙ ጥሪት ሰጥቶት ነበርና ከተሞችን ለራሱ ሠራ፤ ብዙም የበግና የላም መንጋ ሰበሰበ። 30ይህም ሕዝቅያስ የላይኛውን የግዮንን ውኃ ምንጭ ደፈነ፤ በዳዊትም ከተማ በምዕራብ በኩል አቅንቶ አወረደው። ሕዝቅያስም በሥራው ሁሉ ተከናወነ። 31ነገር ግን የባቢሎን መሳፍንት መልእክተኞች በሀገሩ ላይ ስለ ተደረገው ተአምራት ይጠይቁት ዘንድ ወደ እርሱ በተላኩ ጊዜ እግዚአብሔር ይፈትነውና በልቡ ያለውን ሁሉ ያውቅ ዘንድ ተወው።
32የሕዝቅያስም የቀሩት ነገሮች፥ ቸርነቱም፥ እነሆ፥ በአሞጽ ልጅ በነቢዩ በኢሳይያስ ራእይ በይሁዳና በእስራኤልም ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 33ሕዝቅያስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ልጆች መቃብር በላይኛው ክፍል ቀበሩት፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚኖሩትም ሁሉ በሞቱ አከበሩት። ልጁም ምናሴ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 32: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ