መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 31
31
1ይህም ሁሉ በተፈጸመ ጊዜ በይሁዳ ከተሞች የተገኙ እስራኤል ሁሉ ወጥተው ዐምዶቹን ሰበሩ፤ ዐፀዶችንም ኮረብታዎችንም አፈረሱ፤ መሠዊያውንም አጠፉ። በይሁዳና በብንያምም ሁሉ ደግሞም በኤፍሬምና በምናሴ የነበሩትን ፈጽመው እስከ ዘለዓለሙ አጠፉአቸው። የእስራኤልም ልጆች ሁሉ ወደ ርስታቸውና ወደ ከተሞቻቸው ተመለሱ።
2ሕዝቅያስም የካህናትንና የሌዋውያንን ሰሞን በየክፍላቸውና በየአገልግሎታቸው፥ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ በሮች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነቱን መሥዋዕት ያቀርቡና ያገለግሉ ዘንድ፥ ያመሰግኑም፥ ያከብሩም ዘንድ ካህናቱንና ሌዋውያኑን መደበ። 3በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ በጥዋትና በማታ በሰንበታቱም፥ በመባቻዎቹም፥ በበዓላትም ለሚቀርበው ለሚቃጠለው መሥዋዕት ንጉሡ ከገንዘቡ የሚከፍለውን ወሰነ። 4በእግዚአብሔርም ቤት ለአገልግሎት እንዲጸኑ ለካህናቱና ለሌዋውያን ድርሻቸውን ይሰጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም የሚኖሩትን ሕዝብ አዘዘ። 5ይህንም ነገር እንዳዘዘ የእስራኤል ልጆች የእህሉንና የወይኑን፥ የዘይቱንና የማሩንም፥ የእርሻውንም ፍሬ መጀመሪያ ሁሉ ሰጡ፤ የሁሉንም ዐሥራት አብዝተው አቀረቡ። 6በይሁዳም ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤልና የይሁዳ ልጆች የበሬዉንና የበጉን፥ የፍየሉንም ዐሥራት አመጡ፤ ለአምላካቸው ለእግዚአብሔርም ቀደሱት፤ ከምረውም አኖሩት። 7በሦስተኛውም ወር መከመር ጀመሩ፤ በሰባተኛውም ወር ጨረሱ። 8ሕዝቅያስና አለቆቹም መጥተው ክምሩን ባዩ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ሕዝቡን እስራኤልንም ባረኩ። 9ሕዝቅያስም ካህናቱንና ሌዋውያኑን ስለ ክምሩ ጠየቀ። 10ከሳዶቅም ወገን የሆነ ታላቁ ካህን ዓዛርያስ፥ “ሕዝቡ መባውን ወደ እግዚአብሔር ፊት ማቅረብ ከጀመረ ወዲህ በልተናል፤ ጠጥተናልም፤ ጠግበናልም፤ እግዚአብሔርም ሕዝቡን ባርኮአልና ብዙ ተርፎአል፤ ከዚህም ገና ብዙ ተረፈ” ብሎ ተናገረ።
11ሕዝቅያስም ለእግዚአብሔር ቤት ጎተራ ያዘጋጁ ዘንድ አዘዘ፤ እነርሱም አዘጋጁ። 12መባኡንና ዐሥራቱን፥ የተቀደሱትንም በእምነት ወደዚያ አገቡ። ሌዋዊውም ኮክንያስ ተሾመባቸው፥ ወንድሙም ሰሜኢ በማዕርግ ሁለተኛ ነበረ፤ 13ንጉሡም ሕዝቅያስና የእግዚአብሔር ቤት አለቃ ዓዛርያስ እንደ አዘዙ ኢዮኤል፥ ዓዛዝያ፥ አናኤት፥ ኡሳሄል፥ ኢያሪሞት፥ ኢዮዛብድ፥ ኤልሄል፥ ሰማኪያ፥ መሐት፥ በናያስና ልጆቹ፥ ከኮክንያስና ከወንድሙ ከሰሜኢ እጅ በታች ተቈጣጣሪዎች ነበሩ። 14የሌዋዊውም የይምላእ ልጅ የምሥራቁ ደጅ በረኛ ቆሬ የእግዚአብሔርን መባና የተቀደሱትን ነገሮች እንዲያካፍል ሕዝቡ በፈቃዳቸው ለእግዚአብሔር በአቀረቡት ላይ ተሾመ። 15በካህናቱም ከተሞች#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በካህናቱ እጅ” ይላል። ለታላላቆችና ለታናናሾች ወንድሞቻቸው በየሰሞናቸው ክፍላቸውን በእምነት ይሰጡ ዘንድ ኤዶም፥ ብንያስ፥ ኢያሱ፥ ሴሚ፥ አማርያ፥ ኮክንያስ ከእጁ በታች ነበሩ። 16ከሦስትም ዓመት ወደ ላይ ላሉ በየሰሞናቸው ለሥራቸውና ለአገልግሎታቸው ዕለት ዕለት ወደ እግዚአብሔር ቤት ለሚገቡ ወንዶች ሁሉ፥ 17በየአባቶቻቸውም ቤት ለተቈጠሩ ካህናት፥ ከሃያ ዓመትም ወደ ላይ ላሉ በየሥርዐታቸውና በየሰሞናቸው ለተቈጠሩ ሌዋውያን፥ 18በማኅበራቸውም ሁሉ በየትውልዳቸው ለተቈጠሩ ለሚስቶቻቸው፥ ለወንዶችና ለሴቶች ልጆቻቸውም ይሰጡ ነበር፤ በእምነት ፈጽመው ተቀድሰዋልና። 19ክህነት ለሚገባቸው ለአሮን ልጆች ለካህናቱ፥ በከተሞቻቸውም ዙሪያ ባሉ መሰማሪያዎችና በሌሎችም ከተሞች ላሉ ለወንዶች ሁሉ፥ ከሌዋውያን ጋራ ለተቈጠሩ ሰዎችም ሁሉ ከፍለው ይሰጡ ዘንድ በስም የተጠሩ ሰዎች ነበሩ።
20ሕዝቅያስም በይሁዳ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ በአምላኩም በእግዚአብሔር ፊት መልካምንና ቅን ነገርን እውነትንም አደረገ። 21ስለ እግዚአብሔርም ቤት አገልግሎት በጀመረው ሥራ ሁሉ፥ በሕጉና በትእዛዙም አምላኩን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ፈለገው፤ ሥራውም ሁሉ ተከናወነለት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 31: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ