መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 30
30
የበዓለ ፋሲካ አከባበር በዘመነ ሕዝቅያስ
1ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ፋሲካ ያደርጉ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፤ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤዎችን ጻፈ። 2ንጉሡና አለቆቹ በኢየሩሳሌምም ያለ የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ። 3ካህናቱ በሚበቃ ቍጥር ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ በጊዜው ያደርጉት ዘንድ አልቻሉም ነበርና። 4ነገሩም ንጉሡንና ጉባኤውን ሁሉ ደስ የሚያሰኝ ሆነ። 5እንደ ተጻፈም ብዙዎቹ አላደረጉትም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ያደርጉ ዘንድ እንዲመጡ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ። 6እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልእክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የአለቆቹን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ፈጥነው ሄዱ፥ “የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአሦር ንጉሥ እጅ ወዳመለጠ ቅሬታችሁ እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ ያዕቆብም አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ። 7እናንተም እንደምታዩ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ፥ ለጥፋትም እንደ ሰጣቸው እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። 8አሁንም እንደ አባቶቻችሁ አንገታችሁን አታደንድኑ፤ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ስጡ፤ ለዘለዓለምም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱ ግቡ፤ ጽኑ ቍጣውንም ከእናንተ እንዲመልስ ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ተገዙ። 9አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብንመለስ ፊቱን ከእኛ አያዞርምና ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፤ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመልሳቸዋል።”
10መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ ሀገር እስከ ዛብሎን ሄዱ፤ እነዚያ ግን በንቀት ሳቁባቸው፤ አፌዙባቸውም። 11ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ፥ ከዛብሎንም አያሌ ሰዎች ሰውነታቸውን አዋረዱ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። 12ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የአለቆቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በእነርሱ ላይ ሆነ።
13በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ያደርጉ ዘንድ በኢየሩሳሌም ብዙ ሕዝብ ተሰበሰቡ፤ እጅግም ታላቅ ጉባኤ ነበረ። 14ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፤ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት። 15በሁለተኛውም ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተዘጋጁ#ዕብ. “ዐፈሩ” ይላል። ነጹም። ወደ እግዚአብሔርም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ። 16እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በቦታቸውና በሥርዐታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር። 17በጉባኤውም ያልነጹ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ራሳቸውን ላላነጹት ሁሉ የፋሲካውን በግ ያርዱላቸው ነበር። 18እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ፥ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ። 19ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ እንዲህ ሲል ጸለየ፥ “ምንም እንደ መቅደሱ ማንጻት ባይነጻ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን የሚያቀናውን ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው።” 20እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም አዳናቸው። 21በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች በየቀኑ እግዚአብሔርን እያመሰገኑ የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አደረጉ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር። 22ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያንን ሁሉ ያጽናና ነበር። የደኅንነትም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።
23ጉባኤው ሁሉ እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ፤ በደስታም እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል አደረጉ። 24ንጉሡ ሕዝቅያስም ስለ ቍርባን ሺህ ወይፈኖችንና ሰባት ሺህ በጎችን ለይሁዳና ለጉባኤው ሰጥቶ ነበር፤ አለቆቹም ሺህ ወይፈኖችንና ዐሥር ሺህ በጎችን ለጉባኤው ሰጥተው ነበር፤ ከካህናቱ እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና። 25የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም ሀገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው። 26በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር። 27ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምፃቸውም ተሰማ፥ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ ማደሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 30: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ