መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 29
29
የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 18፥1-3)
1ሕዝቅያስም የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አብያ ትባል ነበር። 2አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ።
የቤተ መቅደስ መንጻት
3በመንግሥቱም በጸና ጊዜ#ዕብ. “በነገሠ በመጀመሪያ ዓመት” ይላል። በመጀመሪያው ወር የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ከፈተ፤ አደሳቸውም። 4ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፤ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፤ 5እንዲህም አላቸው፥ “ሌዋውያን ሆይ፥ ስሙኝ፤ ራሳችሁን አንጹ፤ የአባቶቻችሁንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ቀድሱ፤ ርኩስን ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። 6አባቶቻችን ከእግዚአብሔር ርቀዋል፤ በአምላካችንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ረስተዋል፤ ፊታቸውንም ከእግዚአብሔር ቤት መልሰዋል፤ ጀርባቸውንም አዙረዋል፤ 7ደግሞም የእግዚአብሔርን ቤት ደጆች ዘግተዋል፤ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፤ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም።
8“ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ሆነ፤ በዐይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ፥ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው። 9እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችሁ በሰይፍ ወደቁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም፥ ሚስቶቻችሁም የእነርሱ ሀገር ወዳልሆነ ተማረኩ፤ እስከ ዛሬም በዚያ ይኖራሉ።#“የእነርሱ ሀገር ወዳልሆነ ተማረኩ ፤ እስከ ዛሬም ድረስ በዚያ ይኖራሉ” የሚለው በዕብ. የለም። 10አሁንም የቍጣውን መቅሠፍት ከእኛ እንዲመልስ ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን አደርግ ዘንድ በልቤ አስቤአለሁ። 11አሁንም#ዕብ. “ልጆች ሆይ” ይላል። በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ፥ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ፥ ታጥኑለትም ዘንድ እግዚአብሔር መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።”
12ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአሜሳእ ልጅ መኤትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮሔል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የያሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ኢዮአድ፤ 13ከኤልሳፋንም ልጆች ሳምሪና ኢዮሔል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና ማታንያስ፤ 14ከኤማንም ልጆች ኢዮሔልና ሰሜኢ፥ ከኢዱቱንም ልጆች ሰማዕያና ኡዝሔል ተነሡ። 15ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው በእግዚአብሔር ቃል እንደ ንጉሡ ትእዛዝ የእግዚአብሔርን ቤት ያነጹ ዘንድ ራሳቸውን አነጹ። 16ካህናቱም ያነጹት ዘንድ#“ያነጹት ዘንድ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ውስጥ ገቡ፤ በእግዚአብሔርም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት። 17በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ያነጹ ጀመር፤ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ እግዚአብሔር ቤት ወለል ደረሱ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት በስምንት ቀን አነጹ፤ በመጀመሪያውም ወር በዐሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ። 18ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው፥ “የእግዚአብሔርን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የኅብስተ ገጹንም ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤ 19ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፉ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል፤ ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት ሆነዋል” አሉት።
20ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ፤ የእስራኤልንም ቤት#ዕብ. እና ግሪክ አባ. ሊ. “የከተማይቱን” ይላል። አለቆች ሰበሰበ፤ ወደ እግዚአብሔርም ቤት ወጣ። 21ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም፥ ስለ ሕዝቡም ስለ እስራኤል ለኀጢአት መሥዋዕት ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን፥ “ወደ እግዚአብሔር መሠዊያ ውጡ” አላቸው። 22ወይፈኖቹንም አረዱ፤ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት። 23የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆኑትንም አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፤ እጃቸውንም ጫኑባቸው፤ 24ካህናቱም አረዱአቸው፤ ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኀጢአት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተስረያ ያደርጉ ዘንድ ደማቸውን በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።
25ይህንም ትእዛዝ እግዚአብሔር በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና፥ መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በእግዚአብሔር ፊት አቆመ። 26ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። 27ሕዝቅያስም፥ “የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያው ላይ አሳርጉ” አለ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ማሳረግ በተጀመረ ጊዜ የእግዚአብሔር መዝሙር ደግሞ ተጀመረ፤ መለከቱም ተነፋ፤ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ ተመታ። 28የሚቃጠለውም መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ጉባኤው ሁሉ ይሰግዱ ነበር፤ መዘምራኑም ይዘምሩ ነበር፤ መለከተኞችም ይነፉ ነበር። 29ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡ፥ ከእርሱም ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ፤ ሰገዱም። 30ንጉሡ ሕዝቅያስና አለቆቹም በዳዊትና በነቢዩ በአሳፍ ቃል እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ሌዋውያንን አዘዙ። በደስታም አመሰገኑ፤ አጐነበሱም፤ ሰገዱም።
31ሕዝቅያስም፥ “አሁን እጃችሁን ለእግዚአብሔር አንጽታችሁ ቅረቡ፤ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ እግዚአብሔር ቤት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ። 32ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ ወይፈን፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 33የተቀደሱትም ቍጥር ስድስት መቶ በሬዎች፥ ሦስት ሺህም በጎች ነበረ። 34ነገር ግን ካህናቱ ጥቂቶች ነበሩና የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ አይችሉም ነበር፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር። 35የሚቃጠለውም መሥዋዕት ከደኅንነቱ መሥዋዕት ስብና ለሚቃጠለውም መሥዋዕት ከሚቀርበው የመጠጥ ቍርባን ጋር ብዙ ነበረ። እንዲሁም የእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ። 36ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላዘጋጀው ነገር ደስ አላቸው። ይህ ነገር በድንገት ተደርጎአልና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 29: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ