መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 25
25
የይሁዳ ንጉሥ የአሜስያስ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 14፥2-6)
1አሜስያስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ አምስት ዓመት ጐልማሳ ነበረ፥ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ኢዮዓዲን የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 2በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገርን አደረገ፤ ነገር ግን በፍጹም ልብ አይደለም። 3መንግሥትም በእጁ በጸናለት ጊዜ ንጉሡን አባቱን የገደሉትን ባሪያዎች ገደለ። 4እንደ እግዚአብሔር ሕግ ቃል ኪዳን እንደ ተጻፈ፥#ዕብ. “በሙሴ ሕግ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ” ይላል። እግዚአብሔርም፥ “ሰው ሁሉ በገዛ ኀጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች በልጆቻቸው፥ ልጆችም በአባቶቻቸው ፋንታ አይሙቱ” ብሎ እንዳዘዘ ልጆቻቸውን ግን አልገደለም።
በኤዶምያስ ላይ የተደረገ ጦርነት
(2ነገ. 14፥7)
5ንጉሡ አሜስያስም የይሁዳን ሕዝብ ሰበሰበ፤ እንደ እየአባቶቻቸውም ቤቶች አቆማቸው፤ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ሁሉ#ዕብ. “ብንያም” ይላል። የሽህ አለቆችንና የመቶ አለቆችን አደረገ፤ ከሃያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ሁሉ ቈጠረ፤ ለሰልፍም የሚወጡ፥ ጋሻና ጦርም የሚይዙ ሦስት መቶ ሺህ የተመረጡ ሰዎችን አገኘ። 6ደግሞም ከእስራኤል ዘንድ መቶ ሺህ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎችን በመቶ መክሊት ብር ቀጠረ። 7አንድ የእግዚአብሔር ሰው ግን ወደ እርሱ መጥቶ፥ “ንጉሥ ሆይ፥ እግዚአብሔር ከእስራኤልና ከኤፍሬም ልጆች ሁሉ ጋር አይደለምና የእስራኤል ጭፍራ ከአንተ ጋር አይውጣ። 8ብትሄድ ግን፥ በእነርሱም ማሸነፍን ብታስብ፥ የማጽናትና የመጣል ኀይል ከእግዚአብሔር ዘንድ ነውና እግዚአብሔር በጠላቶችህ ፊት ይጥልሃል” አለው። 9አሜስያስም የእግዚአብሔርን ሰው፥ “ለእስራኤል ጭፍራ የሰጠሁት መቶ መክሊት ምን ይሁን?” አለው። የእግዚአብሔርም ሰው፥ “ከዚህ አብልጦ ይሰጥህ ዘንድ ለእግዚአብሔር አይሳነውም” ብሎ መለሰለት። 10ንጉሡ አሜስያስም ከኤፍሬም ከተሞች የመጡ ጭፍሮች ወደ ስፍራቸው ይመለሱ ዘንድ ለይቶ አሰናበታቸው፤ ስለዚህም ቍጣቸው በይሁዳ ላይ ጸና፤ ወደ ስፍራቸውም በጽኑ ቍጣ ተመለሱ። 11አሜስያስም በረታ፤ ሕዝቡንም ሰብስቦ ወደ ጨው ሸለቆ ሄደ፤ ከሴይርም ልጆች ዐሥር ሺህ ገደለ። 12የይሁዳም ልጆች ደግሞ ዐሥር ሺህ ሰዎችን ማረኩ። ወደ ዐለቱም ራስ ላይ አመጡአቸው፤ ከዐለቱም ራስ ላይ ጣሉአቸው፤ ሁሉም ተፈጠፈጡ። 13አሜስያስ ግን ከእርሱ ጋር ወደ ሰልፍ እንዳይሄዱ ያሰናበታቸው ጭፍሮችም ከሰማርያ ጀምረው እስከ ቤትሮን ድረስ በይሁዳ ከተሞች ላይ አደጋ ጣሉ፤ ከእነርሱም ሦስት ሺህ ገደሉ፤ ብዙም ምርኮ ማረኩ።
14አሜስያስም የኤዶምያስን ሰዎች ከገደለ በኋላ የሴይርን ልጆች አማልክት አመጣ፤ የእርሱም አማልክት ይሆኑ ዘንድ አቆማቸው፤ በፊታቸውም ይሰግድላቸውና ይሠዋላቸው ነበር። 15ስለዚህም የእግዚአብሔር ቍጣ በንጉሡ በአሜስያስ ላይ መጣ፤ እንዲህም ሲል ነቢይን ላከበት፥ “ሕዝባቸውን ከአንተ እጅ ያላዳኑትን የአሕዛብን አማልክት ስለምን ፈለግሃቸው?” 16እርሱም ይህን ሲናገር ንጉሡ አሜስያስ፥ “በውኑ የንጉሡ አማካሪ ልትሆን ሹሜሃለሁን? ቅጣት እንዳያገኝህ ተጠንቀቅ” አለው። ነቢዩም፥ “ይህን አድርገሃልና፥ ምክሬንም አልሰማህምና እግዚአብሔር ሊያጠፋህ እንዳሰበ አወቅሁ” ብሎ ዝም አለ።
በይሁዳና በእስርኤል መካከል የተደረገ ጦርነት
(2ነገ. 14፥8-20)
17የይሁዳም ንጉሥ አሜስያስ ምክር አደረገና፥ “ና፥ እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ኢዮአስ ላከ። 18የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ፦ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ እንዲህ ሲል ላከ፥ “የሊባኖስ ኵርንችት ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው” ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም ዱር አውሬዎች መጥተው ኵርንችቱን ረገጡት። 19አንተም፦ እነሆ፥ ኤዶምያስን መትቻለሁ ብለህ በልብህ ኰርተሃል፤ በቤትህ ተቀመጥ፤ አንተ ከይሁዳ ጋር ትወድቅ ዘንድ ስለምን መከራን በራስህ ትሻለህ?”
20የኤዶምያስንም አማልክት ስለ ፈለጉ በጠላቶቻቸው እጅ አሳልፎ ይሰጣቸው ዘንድ ይህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነበረና አሜስያስ አልሰማም። 21የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ ወጣ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤትሳሚስ ላይ እርስ በርሳቸው ተያዩ። 22ይሁዳም በእስራኤል ፊት ድል ሆኑ፥ እያንዳንዳቸውም ወደ ድንኳናቸው ሸሹ። 23የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣው፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 24ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤት በአብዲዶም እጅ የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፥ በንጉሡም ቤተ መዛግብት የተገኘውን፥ በመያዣ የተያዙትንም ልጆች ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
25የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከኢዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 26የቀሩትም የፊተኞቹና የኋለኞቹ የአሜስያስ ነገሮች፥ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 27አሜስያስም እግዚአብሔርን ከመከተል በራቀ ጊዜ በኢየሩሳሌም የዐመፅ መሐላ አደረጉበት፤ ወደ ለኪሶም ኮበለለ፤ በስተኋላውም ወደ ለኪሶ ላኩ፤ በዚያም ገደሉት። 28በፈረስም ጭነው አመጡት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 25: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ