መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 24
24
የኢዮአስ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 12፥1-16)
1ኢዮአስም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሰባት ዓመት ልጅ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም አርባ ዓመት ነገሠ፤ እናቱ ሳብያ የተባለች የቤርሳቤህ ሴት ነበረች። 2ኢዮአስም በካህኑ በኢዮአዳ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገርን አደረገ። 3ኢዮአዳም ሁለት ሚስቶችን አጋባው፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ወለደ።
4ከዚህም በኋላ ኢዮአስ የእግዚአብሔርን ቤት ይጠግን ዘንድ አሰበ። 5ካህናትንና ሌዋውያንንም ሰብስቦ፥ “ወደ ይሁዳ ከተሞች ውጡ፤ የአምላካችሁንም ቤት በየዓመቱ ለማደስ የሚበቃ ከእስራኤል ሁሉ ገንዘብን ሰብስቡ፤ ነገሩንም ፈጥናችሁ አድርጉ” አላቸው። ሌዋውያን ግን አላፋጠኑም። 6ንጉሡ ኢዮአስም አለቃውን ኢዮአዳን ጠርቶ፥ “የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ እስራኤልን በምስክሩ ድንኳን በሰበሰበ ጊዜ እንዲያዋጣ ያዘዘውን ግብር ከይሁዳና ከኢየሩሳሌም ያመጡ ዘንድ ስለ ምን ሌዋውያንን አልተከታተልህም?” አለው። 7ጎቶልያ ከሐዲት ነበረችና ልጆችዋም የእግዚአብሔርን ቤት አፍርሰዋልና፤ በእግዚአብሔርም ቤት ተቀድሶ የነበረውን ሁሉ ለበኣሊም ሰጥተዋልና።
8ንጉሡም ሣጥን ሠርተው በእግዚአብሔር ቤት በር አጠገብ በስተውጭ ያኖሩት ዘንድ አዘዘ። 9የእግዚአብሔርም ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ በእስራኤል ላይ ያዘዘውን ግብር ለእግዚአብሔር ያመጡ ዘንድ፥ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ያስተምሩ ዘንድ አዘዘ። 10አለቆቹና ሕዝቡም ሁሉ ሰጡ፤ እስኪሞላም ድረስ በሣጥኑ ውስጥ አስገቡት። 11ሣጥኑም በሌዋውያን እጅ ወደ ንጉሡ ሹሞች በደረሰ ጊዜ፥ ብዙ ገንዘብም እንዳለበት ባዩ ጊዜ፥ የንጉሡ ጸሓፊና የሊቀ ካህናቱ ሹም እየመጡ ብሩን ከሣጥን ያወጡ ነበር፤ ሣጥኑንም ደግሞ ወደ ስፍራው ይመልሱት ነበር። እንዲሁም በየቀኑ ያደርጉ ነበር፤ ብዙም ገንዘብ ሰበሰቡ። 12ንጉሡና ኢዮአዳም በእግዚአብሔር ቤት ሥራ ላይ ለተሾሙት ሰጡአቸው፤ እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤት የሚጠግኑትን ጠራቢዎችንና አናጢዎችን፥ የእግዚአብሔርንም ቤት የሚያድሱትን የብረትና የናስ ሠራተኞችን ይቀጥሩበት ነበር። 13ሠራተኞችም ሠሩ፤ ሥራውም ሁሉ በእጃቸው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርንም ቤት እንደ ቀድሞው ሥራ መለሱ፤ አጽንተውም አቆሙት። 14በጨረሱም ጊዜ የተረፈውን ገንዘብ ወደ ንጉሡና ወደ ካህኑ ኢዮአዳ ፊት አመጡ፤ እነርሱም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃ፥ ለአገልግሎትና ለቍርባን ዕቃ፥ ለጭልፋዎችም፥ ለወርቅና ለብርም ዕቃ አደረጉት። በኢዮአዳም ዘመን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት ሁልጊዜ ያቀርቡ ነበር።
15ኢዮአዳም ሸመገለ፤ ዕድሜም ጠግቦ ሞተ፤ በሞተም ጊዜ ዕድሜው መቶ ሠላሳ ዓመት ነበረ። 16ከእስራኤልም ጋር፥ ከእግዚአብሔርና ከቤቱም ጋር መልካም ሠርቶአልና በዳዊት ከተማ ከነገሥታቱ ጋር ቀበሩት። 17ካህኑ ኢዮአዳም ከሞተ በኋላ የይሁዳ አለቆች ገብተው ለንጉሡ ሰገዱ፤ ንጉሡም ሰማቸው። 18የአባቶቻቸውንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ትተው ባዕድ አምላክንና#ዕብ. “የማምለኪያ ዐፀዶችን” ይላል። ጣዖታትን አመለኩ፤ በዚያም ወራት#ዕብ. “በዚህ በደላቸውም ምክንያት” ይላል። በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ቍጣ ወረደ። 19ወደ እግዚአብሔርም ይመልሱአቸው ዘንድ ነቢያትን ይሰድድላቸው ነበር፤ መሰከሩባቸውም፤ እነርሱ ግን አላደመጡም።
20የእግዚአብሔርም መንፈስ በካህኑ በኢዮአዳ ልጅ በአዛርያስ#ዕብ. “ዘካርያስ” ይላል። ላይ መጣ፤ እርሱም በሕዝቡ ፊት ቆመና፥ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ለምን ትተላለፋላችሁ? መልካምም አይሆንላችሁም፤ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁ እርሱ ትቶአችኋል” አላቸው። 21ወደ እርሱም ሮጡ#ዕብ. እና ግሪክ “ተማማሉበት” ይላል። በንጉሡም ትእዛዝ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ውስጥ በድንጋይ ደበደቡት። 22እንዲሁም ንጉሡ ኢዮአስ አባቱ ኢዮአዳ ያደረገለትን ቸርነት አላሰበም፤ ልጁንም አዛርያስን አስገደለው፤ እርሱም ሲሞት፥ “እግዚአብሔር ይየው፤ ይፍረደውም” አለ።
23ዓመቱም ካለፈ በኋላ የሶርያውያን ሠራዊት መጡበት፤ ወደ ይሁዳና ወደ ኢየሩሳሌምም መጥተው ከሕዝቡ መካከል የሕዝቡን አለቆች ሁሉ አጠፉ፤ ምርኮአቸውንም ሁሉ ለደማስቆ ንጉሥ ላኩ። 24የሶርያውያንም ሠራዊት ቍጥር ጥቂት ነበር፤ እግዚአብሔር ግን ብዙውንና ጠንካራውን ሠራዊት አሳልፎ በእጃቸው ሰጣቸው፤ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ዘንግተዋልና። በኢዮአስም ላይ ፈረደበት።
25ከእርሱም ዘንድ አልፈው ከሄዱ በኋላ እጅግ ታሞ ሳለ ተዉት፤ የገዛ ባሪያዎቹም ስለ ካህኑ ስለ ኢዮአዳ ልጅ ደም ተበቅለው በአልጋው ላይ ገደሉት፤ ሞተም፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ነገር ግን በነገሥታት መቃብር አልቀበሩትም። 26የገደሉትም#ዕብ. “የተማማሉበት” ይላል። የአሞናዊቱ የሰማት ልጅ ዘቡድ፥ የሞዓባዊቱም የሰማሪት ልጅ ኢዮዛብድ ነበሩ። 27የልጆቹና በእርሱ ላይ የተደረገው ነገር፥ የእግዚአብሔርንም ቤት ማደሱ፥ እነሆ በነገሥታቱ የታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል። ልጁም አሜስያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 24: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ