መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 23
23
የይሁዳ ንጉሥ የአካዝያስ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 11፥4-16)
1በሰባተኛውም ዓመት ኢዮአዳ በረታ፤ የመቶ አለቆቹንም፥ የኢዮራምን ልጅ አዛርያስን፥ የኢዮአናንም ልጅ እስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ አዛርያን፥ የኢዳኢንም ልጅ መዓስያን፥ የዘካርያስንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወደ እግዚአብሔር ቤት ከእርሱ ጋር ወሰደ። 2ይሁዳንም ዞሩ፤ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። የንጉሥንም ልጅ አሳያቸው፤#በግሪክ ሰባ. ሊ. እና በዕብ. “ዮዳሄም አላቸው” ይላል። አላቸውም፥ “እነሆ፥ እግዚአብሔር ስለ ዳዊት ቤት እንደ ተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4እነሆ፥ የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋውያን ከሦስት አንድ እጅ በመግቢያ በሮች በረኞች ሁኑ፤ 5ከሦስት አንድ እጅም በንጉሡ ቤት ሁኑ፤ ሌላውም ከሦስት አንድ እጅ በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ ይሁኑ። 6ወደ እግዚአብሔር ቤት ግን ከካህናትና ከሌዋውያን ከሌዋውያኑም አገልጋዮች በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ይጠብቅ። 7ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል፤ ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።” 8ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ኢዮአዳ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ኢዮአዳ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ ከሰንበት መጀመሪያ እስከ ሰንበት መጨረሻ ሰዎችን ወሰደ። 9ካህኑም ኢዮአዳ በእግዚአብሔር ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ሰይፍና ጦር፥ አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 10ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤተ መቅደሱ ቀኝ እስከ ቤተ መቅደሱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በመቅደሱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። 11የንጉሡንም ልጅ አውጥቶ ዘውዱን ጫነበት፤ ምስክሩንም ሰጠው፤ አነገሡትም፤ ኢዮአዳና ልጆቹም አነገሡት፥ “ንጉሡ በሕይወት ይኑር” እያሉም ቀቡት።
12ጎቶልያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር ቤት መጣች። 13እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ በንጉሡም ዙሪያ አለቆችና መለከተኞች፥ መኳንንትም ቆመው አየች። ሕዝቡም ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶልያም ልብስዋን ቀድዳ፥ “ዐመፅ ነው! ዐመፅ ነው!” ብላ ጮኸች። 14ካህኑም ኢዮአዳ ወጥቶ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን አለቆችና የመቶ አለቆች፥ “ከቤተ እግዚአብሔር ወደ ውጭ አውጡአት፤ የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል”#ግሪኩ “ተከትላችሁ በሰይፍ ግደሉአት” ይላል። ብሎ አዘዛቸው። ካህኑ፥ “በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ አትገደል” ብሎአልና። 15ገለልም ብለው አሳለፉአት፤ እርስዋም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፤ በዚያም ገደሉአት።
16ካህኑ ኢዮአዳም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ፥ በንጉሡም መካከል የእግዚአብሔር ሕዝብ ይሆኑ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ። 17የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ወደ በዓል ቤት ሄደው አፈረሱት፤ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፤ የበዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። 18ካህኑ ኢዮአዳም በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው እንደ ዳዊት ትእዛዝ በደስታና በመዝሙር ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ዳዊት በእግዚአብሔር ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። 19በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በእግዚአብሔር ቤት በር በረኞችን አኖረ። 20የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎችንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የሀገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፤ ንጉሡንም ከእግዚአብሔር ቤት አወረዱት፤ በእግዚአብሔርም ቤት በውስጠኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት አመጡት፤ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። 21የሀገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፤ ከተማዪቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶልያንም በሰይፍ ገደሉአት።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 23: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ