አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። አሳም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ፥ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፤ ሐውልቶቹንም ሰበረ፤ የማምለኪያ አፀዶቹንም ቈረጠ፤ የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ያደርጉ ዘንድ የይሁዳን ሕዝብ አዘዘ። ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የጣዖት መሠዊያዎችንና ምስሎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ ሥር በሰላም ተቀመጠች። በይሁዳም ምሽጎች ከተሞችን ሠራ፤ እግዚአብሔርም ዕረፍት ስለ ሰጠው ምድሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፤ በዚያም ዘመን ጦርነት አልነበረም። እርሱም የይሁዳን ሰዎች፥ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ቅጥርም፥ ግንብም፥ መዝጊያም፥ መወርወሪያም እናድርግባቸው፤ ምድሪቱንም እንገዛታለን፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንደ ፈለግነው እርሱም ይፈልገናልና፤ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል፤ ሁሉንም አከናወነልን” አለ። ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ወንጭፍ የሚወነጭፉ፥ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ነበሩ። የኢትዮጵያም ንጉሥ ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። የይሁዳ ንጉሥ አሳም ሊጋጠመው ወጣ፤ በመሪሳም ደቡብ አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። አሳም፥ “አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም፤ አቤቱ፥ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና ርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም” ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ሕዝብ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። አሳም፥ ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌዶር ሀገር ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፤ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ወደቀባቸው በጌዶር ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዙ ምርኮና ብዝበዛ ነበርና ከተሞቹን ሁሉ ማረኩ። የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግ ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ወሰዱ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 14 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 14:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች