መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 14
14
1አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። 2አሳም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ 3የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ፥ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፤ ሐውልቶቹንም ሰበረ፤ የማምለኪያ አፀዶቹንም ቈረጠ፤ 4የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ያደርጉ ዘንድ የይሁዳን ሕዝብ አዘዘ። 5ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የጣዖት መሠዊያዎችንና ምስሎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ ሥር በሰላም ተቀመጠች። 6በይሁዳም ምሽጎች ከተሞችን ሠራ፤ እግዚአብሔርም ዕረፍት ስለ ሰጠው ምድሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፤ በዚያም ዘመን ጦርነት አልነበረም። 7እርሱም የይሁዳን ሰዎች፥ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ቅጥርም፥ ግንብም፥ መዝጊያም፥ መወርወሪያም እናድርግባቸው፤ ምድሪቱንም እንገዛታለን፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን እንደ ፈለግነው እርሱም ይፈልገናልና፤ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል፤ ሁሉንም አከናወነልን”#ዕብ. “እነርሱም ሠሩ፥ አከናወኑም” ይላል። አለ። 8ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ወንጭፍ የሚወነጭፉ፥ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማንያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኀያላን ሰዎች ነበሩ።
9የኢትዮጵያም ንጉሥ ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። 10የይሁዳ ንጉሥ አሳም ሊጋጠመው ወጣ፤ በመሪሳም ደቡብ አጠገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። 11አሳም፥ “አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህም፤ አቤቱ፥ አምላካችን ሆይ፥ በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና ርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም” ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። 12እግዚአብሔርም በአሳና#“በአሳና” የሚለው በዕብ. ብቻ። በይሁዳ ሕዝብ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። 13አሳም፥ ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌዶር ሀገር ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፤ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ። 14ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ወደቀባቸው በጌዶር ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዙ ምርኮና ብዝበዛ ነበርና ከተሞቹን ሁሉ ማረኩ። 15የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግ ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ወሰዱ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 14: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ