መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 15
15
1የእግዚአብሔርም መንፈስ በአዳድ ልጅ በአዛርያስ ላይ መላ፤ 2እርሱም ንጉሡን አሳን፥ የይሁዳንና የብንያምን ሕዝብ ሁሉ ሊገናኝ ወጣ፤ እንዲህም አለ፥ “አሳ ይሁዳና ብንያም ሁሉ ሆይ፥ ስሙኝ፤ እናንተ ከእግዚአብሔር ጋር ብትሆኑ እርሱ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ ብትፈልጉትም ይገኝላችኋል፤ ብትተዉት ግን ይተዋችኋል። 3እስራኤልም ብዙ ዘመን እውነተኛውን አምላክ ሳያመልኩ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖራሉ። 4በመከራቸውም ጊዜ ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር ተመልሰው ይፈልጉታል፤ እርሱም ይገኝላቸዋል። 5በዚያም ዘመን ለሚወጣውና ለሚገባው ሰላም አይሆንለትም፤ በሀገሮችም በሚኖሩት ሁሉ ላይ ታላቅ የእግዚአብሔር ቍጣ#ዕብ. “ድንጋጤ” ይላል። ይሆናል። 6እግዚአብሔር በመከራው ሁሉ ያስጨንቃቸዋልና ሕዝብ ከሕዝብ ጋር፥ ከተማም ከከተማ ጋር ይዋጋል። ። 7እናንተ ግን ለሥራችሁ ዋጋ ይሆንላችኋልና በርቱ፤ እጆቻችሁም አይላሉ።”
8አሳም ይህን ቃልና የነቢዩን የአዳድን ልጅ የአዛርያስን ትንቢት በሰማ ጊዜ ጸና፤ ከይሁዳና ከብንያምም ሀገር ሁሉ በተራራማው በኤፍሬም ሀገር ከያዛቸው ከተሞች ርኵሰትን ሁሉ አስወገደ፤ በእግዚአብሔርም ቤት ፊት የነበረውን የእግዚአብሔርን መሠዊያ አደሰ። 9አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር እንደ ሆነ ባዩ ጊዜ ከእስራኤል ዘንድ ብዙ ሰዎች ወደ እርሱ ተጠግተው ነበርና እርሱ ይሁዳንና ብንያምን ሁሉ፥ ከኤፍሬምና ከምናሴም፥ ከስምዖንም ፈልሰው ከእነርሱ ጋር የተቀመጡትን ሰበሰበ። 10አሳም በነገሠ በዐሥራ አምስተኛው ዓመት በሦስተኛው ወር በኢየሩሳሌም ተሰበሰቡ። 11በዚያም ቀን ካመጡት ምርኮ ሰባት መቶ በሬዎችንና ሰባት ሺህ በጎችን ለእግዚአብሔር ሠዋ። 12በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ ቃል ኪዳን አደረገ፤ 13የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን የማይፈልግ፥ ታናሽ ወይም ታላቅ፥ ወንድ ወይም ሴት ቢሆን፥ ይገደል ዘንድ ማሉ። 14ለእግዚአብሔርም በታላቅ ድምፅና በእልልታ፥ በእንቢልታና በቀንደ መለከት ማሉ። 15በፍጹምም ልባቸው ምለዋልና፥ በፍጹምም ሕሊናቸው ፈልገውታልና፥ እርሱም ተገኝቶላቸዋልና ይሁዳ ሁሉ በመሐላው ደስ አላቸው፤ እግዚአብሔርም በዙሪያቸው ዕረፍትን ሰጣቸው።
16ንጉሡም አሳ እናቱን መዓካን ለአስጣርቴስ ስለ ሰገደች ከእቴጌነቷ አወረዳት፤ አሳም ምስሉን ቈርጦ ቀጠቀጠው፤ በቄድሮንም ወንዝ አጠገብ አቃጠለው። 17በኮረብታ ላይ የነበሩትን መስገጃዎች ግን ከእስራኤል አላራቀም። ገና በእስራኤል ዘንድ እስከ አሁን ነበሩ፤ ይሁን እንጂ የአሳ ልብ በዘመኑ ሁሉ ፍጹም ነበረ። 18አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ እርሱም የቀደሰውን ወርቁንና ብሩን፥ ልዩ ልዩውንም ዕቃ ወደ እግዚአብሔር ቤትአገባ። 19አሳም በነገሠበት ዘመን እስከ ሠላሳ አምስተኛው ዓመት ድረስ ጦርነት አልነበረም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 15: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ