2 ዜና መዋዕል 14:1-15

2 ዜና መዋዕል 14:1-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አብ​ያም ከአ​ባ​ቶቹ ጋር አን​ቀ​ላፋ፤ በዳ​ዊ​ትም ከተማ ቀበ​ሩት፤ ልጁም አሳ በእ​ርሱ ፋንታ ነገሠ። በእ​ር​ሱም ዘመን ምድ​ሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረ​ፈች። አሳም በአ​ም​ላኩ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፊት መል​ካ​ምና ቅን ነገር አደ​ረገ፤ የእ​ን​ግ​ዶ​ቹ​ንም አማ​ል​ክት መሠ​ዊያ፥ የኮ​ረ​ብ​ታ​ው​ንም መስ​ገ​ጃ​ዎች አፈ​ረሰ፤ ሐው​ል​ቶ​ቹ​ንም ሰበረ፤ የማ​ም​ለ​ኪያ አፀ​ዶ​ቹ​ንም ቈረጠ፤ የአ​ባ​ቶ​ቻ​ቸ​ው​ንም አም​ላክ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉ​ንና ትእ​ዛ​ዙ​ንም ያደ​ርጉ ዘንድ የይ​ሁ​ዳን ሕዝብ አዘዘ። ከይ​ሁ​ዳም ከተ​ሞች ሁሉ የጣ​ዖት መሠ​ዊ​ያ​ዎ​ች​ንና ምስ​ሎ​ችን አስ​ወ​ገደ፤ መን​ግ​ሥ​ቱም በእ​ርሱ ሥር በሰ​ላም ተቀ​መ​ጠች። በይ​ሁ​ዳም ምሽ​ጎች ከተ​ሞ​ችን ሠራ፤ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ዕረ​ፍት ስለ ሰጠው ምድ​ሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፤ በዚ​ያም ዘመን ጦር​ነት አል​ነ​በ​ረም። እር​ሱም የይ​ሁ​ዳን ሰዎች፥ “እነ​ዚ​ህን ከተ​ሞች እን​ሥራ፤ ቅጥ​ርም፥ ግን​ብም፥ መዝ​ጊ​ያም፥ መወ​ር​ወ​ሪ​ያም እና​ድ​ር​ግ​ባ​ቸው፤ ምድ​ሪ​ቱ​ንም እን​ገ​ዛ​ታ​ለን፤ አም​ላ​ካ​ች​ንን እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን እንደ ፈለ​ግ​ነው እር​ሱም ይፈ​ል​ገ​ና​ልና፤ እር​ሱም በዙ​ሪ​ያ​ችን ዕረ​ፍት ሰጥ​ቶ​ናል፤ ሁሉ​ንም አከ​ና​ወ​ነ​ልን” አለ። ለአ​ሳም አላ​ባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚ​ሸ​ከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይ​ሁዳ ሠራ​ዊት፥ ወን​ጭፍ የሚ​ወ​ነ​ጭፉ፥ ቀስ​ትም የሚ​ገ​ትሩ ሁለት መቶ ሰማ​ንያ ሺህ የብ​ን​ያም ሰዎች ነበ​ሩት፤ እነ​ዚ​ህም ሁሉ ጽኑ​ዓን ኀያ​ላን ሰዎች ነበሩ። የኢ​ት​ዮ​ጵ​ያም ንጉሥ ዝሪ አንድ ሚሊ​ዮን ሰዎ​ችና ሦስት መቶ ሰረ​ገ​ሎች ይዞ ወጣ​ባ​ቸው፤ ወደ መሪ​ሳም መጣ። የይ​ሁዳ ንጉሥ አሳም ሊጋ​ጠ​መው ወጣ፤ በመ​ሪ​ሳም ደቡብ አጠ​ገብ ባለው ሸለቆ ውስጥ ተሰ​ለፉ። አሳም፥ “አቤቱ፥ በብ​ዙም ሆነ በጥ​ቂቱ ማዳን አይ​ሳ​ን​ህም፤ አቤቱ፥ አም​ላ​ካ​ችን ሆይ፥ በአ​ንተ ታም​ነ​ና​ልና፥ በስ​ም​ህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥ​ተ​ና​ልና ርዳን፤ አቤቱ፥ አም​ላ​ካ​ችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያ​ሸ​ን​ፍ​ህም” ብሎ ወደ አም​ላኩ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጮኸ። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም በአ​ሳና በይ​ሁዳ ሕዝብ ፊት ኢት​ዮ​ጵ​ያ​ው​ያ​ንን መታ፤ ኢት​ዮ​ጵ​ያ​ው​ያ​ንም ሸሹ። አሳም፥ ከእ​ር​ሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌዶር ሀገር ድረስ አሳ​ደ​ዱ​አ​ቸው፤ ኢት​ዮ​ጵ​ያ​ው​ያ​ንም ፈጽ​መው እስ​ኪ​ጠፉ ድረስ ወደቁ፤ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርና በሠ​ራ​ዊቱ ፊት ተሰ​ባ​ብ​ረ​ዋ​ልና፤ እጅ​ግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ። ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ዘንድ ታላቅ ድን​ጋጤ ስለ ወደ​ቀ​ባ​ቸው በጌ​ዶር ዙሪያ የነ​በ​ሩ​ትን ከተ​ሞች ሁሉ መቱ፤ በከ​ተ​ሞ​ቹም ውስጥ እጅግ ብዙ ምር​ኮና ብዝ​በዛ ነበ​ርና ከተ​ሞ​ቹን ሁሉ ማረኩ። የከ​ብ​ቶ​ቹ​ንም በረት አፈ​ረሱ፤ እጅግ ብዙ በጎ​ች​ንና ግመ​ሎ​ች​ንም ወሰዱ፤ ወደ ኢየ​ሩ​ሳ​ሌ​ምም ተመ​ለሱ።

2 ዜና መዋዕል 14:1-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አብያ ከአባቶቹ ጋራ አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም አሳ በርሱ ፈንታ ነገሠ፤ በዘመኑም በምድሪቱ ለዐሥር ዓመት ሰላም ሆነ። አሳ አባቱ ዳዊት እንዳደረገው ሁሉ፣ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ ባዕዳን መሠዊያዎችንና ማምለኪያ ኰረብቶችን አስወገደ፤ ማምለኪያ ዐምዶችን አፈረሰ፤ አሼራ ለተባለች ጣዖት አምላክ የቆሙ የዕንጨት ቅርጽ ምስሎችንም ቈራረጠ፤ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንዲፈልጉ፣ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲፈጽሙ የይሁዳን ሕዝብ አዘዘ። ከእያንዳንዱም የይሁዳ ከተሞች የማምለኪያ ኰረብቶችንና የዕጣን መሠዊያዎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በርሱ አገዛዝ ዘመን ሰላም አገኘች። በምድሪቱ ሰላም ስለ ሰፈነ፣ በይሁዳ የተመሸጉ ከተሞችን ሠራ። እግዚአብሔር ዕረፍት ስለ ሰጠውም፣ በዘመኑ የተዋጋው ማንም አልነበረም። እርሱም ለይሁዳ ሕዝብ እንዲህ አላቸው፤ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ማማ፣ መዝጊያና መወርወሪያ ያላቸውን ቅጥሮች በዙሪያቸው እናብጅ። አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም የኛው ናት፤ እኛ ፈለግነው፤ እርሱም በሁሉም አቅጣጫ ዕረፍት ሰጠን” እነርሱም ሠሩ፤ ተከናወነላቸውም። አሳ ታላላቅ ጋሻና ጦር የያዙ ሦስት መቶ ሺሕ የይሁዳ ሰዎች እንዲሁም ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሰማንያ ሺሕ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ ብርቱ ተዋጊዎች ነበሩ። ኢትዮጵያዊው ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰራዊትና ሦስት መቶ ሠረገላ ይዞ በመውጣት እስከ መሪሳ ድረስ መጣባቸው። አሳም ሊገጥመው ወጣ፤ መሪሳ አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆም የውጊያ ቦታ ቦታቸውን ያዙ። በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጮኸ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፤ ደካሞችን ከኀይለኞች የሚታደግ እንደ አንተ ያለ ማንም የለም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፤ በአንተ ታምነናልና፣ ይህን ታላቅ ሰራዊት በስምህ እንገጥመዋለን፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህም።” እግዚአብሔርም ኢትዮጵያውያንን በአሳና በይሁዳ ፊት መታቸው፤ ኢትዮጵያውያኑም ሸሹ፤ አሳና ሰራዊቱም እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዷቸው፤ እጅግ ብዙ ቍጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን ስለ ወደቁም፣ ሊያንሰራሩ አልቻሉም፤ በእግዚአብሔር ፊትና በሰራዊቱ ፊት ተደመሰሱ። የይሁዳም ሰዎች እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ። በጌራራ ዙሪያ ባሉት ከተሞች ሁሉ ላይ ታላቅ ድንጋጤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለ ወደቀባቸው ከተሞቹን ሁሉ አጠፏቸው፤ እጅግ ብዙ ምርኮም በዚያ ስለ ነበር፣ በዘበዟቸው። እንዲሁም በእረኞች ሰፈር ላይ አደጋ ጥለው እጅግ ብዙ በጎች፣ ፍየሎችና ግመሎች ማረኩ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።

2 ዜና መዋዕል 14:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። አሳም በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፤ ሐውልቶቹንም ሰበረ፤ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ይሹ ዘንድ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም ያደርጉ ዘንድ ይሁዳን አዘዘ። ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የፀሐይ ምስሎችን አስወገደ፤ መንግሥቱም በእርሱ ሥር በሰላም ተቀመጠች። በይሁዳም ምሽጎች ከተሞችን ሠራ፤ እግዚአብሔርም ዕረፍት ስለ ሰጠው ምድሪቱ ጸጥ ብላ ነበር፤ በዚያም ዘመን ሰልፍ አልነበረም። ይሁዳንም“እነዚህን ከተሞች እንሥራ፤ ቅጥርን፥ ግንብን፥ መዝጊያን፥ መወርወሪያንም እናደርግባቸው፤ አምላካችንን እግዚአብሔርን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ ገና በፊታችን ናት፤ እኛ ፈልገነዋል፤ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል” አለ። እነርሱም ሠሩ፤ አከናወኑም። ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት እና ጋሻ የሚሸከሙ፥ ቀስት የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። አሳም ሊጋጠመው ወጣ፤ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። አሳም “አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህምና፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ! በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና፥ እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ” ብሎ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔርም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን መታ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፤ በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ እጅግም ብዙ ምርኮ ወሰዱ። ከእግዚአብሔርም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ወደቀባቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ መቱ፤ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበርና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ። የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፤ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።

2 ዜና መዋዕል 14:1-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ንጉሥ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሳ ነገሠ፤ በአሳም ዘመነ መንግሥት በምድሪቱ ላይ ለዐሥር ዓመት ሰላም ሆነ፤ አሳ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ ባዕዳን መሠዊያዎችንና በኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን አስወገደ፤ ለማምለኪያ የተሠሩ የድንጋይ ዐምዶችን ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎችን አንከታክቶ ጣለ፤ አሳ የይሁዳ ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲፈጽሙ፥ ሕጉንና ትእዛዞቹን እንዲጠብቁ አዘዘ፤ የኰረብታ መስገጃዎች ስፍራዎችንና ዕጣን የሚታጠንባቸውን መሠዊያዎች ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ስላስወገደ፥ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ሰላም ሰፈነ፤ ለይሁዳ ከተሞች ምሽጎችን ሠራ፤ እግዚአብሔር ሰላም ስለ ሰጠውም ለብዙ ዘመን በአገሪቱ ጦርነት አልነበረም፤ አሳ የይሁዳን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ግንቦችን፥ ቅጽሮችንና በብረት መወርወሪያ የሚዘጉ የቅጽር በሮችን በመሥራት፥ ከተሞቻችንን እንመሽግ፤ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስለ ፈጸምን፥ እነሆ፥ ምድሪቱ በቊጥጥራችን ሥር ናት፤ እግዚአብሔር ጠብቆናል፤ በሁሉም አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጥቶናል፤” ሕዝቡም ከተሞችን መሸገ፤ በለጸገም፤ ንጉሥ አሳ ታላላቅ ጋሻና ጦር የታጠቁ ሦስት መቶ ሺህ ሠራዊት ከይሁዳ፥ ታናናሽ ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ ሠራዊት ከብንያም ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ በሚገባ የሠለጠኑ ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ። ዜራሕ ተብሎ የሚጠራ ኢትዮጵያዊ አንድ ሚሊዮን ወታደሮችና ሦስት መቶ ሠረገሎች ይዞ ይሁዳን ለመውረር እስከ ማሬሻ ገሥግሦ መጣ፤ አሳም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ሁለቱም ወገኖች ማሬሻ አጠገብ በሚገኘው በጸፋታ ሸለቆ ቦታ ቦታቸውን በመያዝ ለውጊያ ተዘጋጁ፤ በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፥ ኀያላኑንም ሠራዊት ሆነ ደካማውንም የመርዳት ችሎታ አለህ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ በአንተ ስለ ተማመንን እነሆ፥ ይህን ብዙ ሠራዊት ለመውጋት መጥተናልና እባክህ እርዳን፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ አምላካችን ነህ፤ አንተን ማሸነፍ የሚችል ማንም የለም።” እግዚአብሔርም ኢትዮጵያውያንን እንዲያሸንፉ ዓሣንና ሠራዊቱን ረዳቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። አሳና ሠራዊቱም እስከ ገራር ድረስ አሳደዱአቸው፤ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ብዙ ሰዎች ስላለቁ፥ ሠራዊቱ እንደገና ተንሠራርቶ ሊዋጋ አልቻለም፤ በዚህም ዐይነት ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ድል ሆኑ፤ የይሁዳ ሰዎችም እጅግ የበዛ ምርኮ ወሰዱ፤ በዚያ አካባቢ የነበሩ ሕዝቦች እግዚአብሔር ባደረገው ነገር እጅግ ተሸብረው ነበር፤ የአሳም ወታደሮች በገራር ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ ደመሰሱ፤ ከተሞቹንም ሁሉ በመዝረፍ ብዙ ምርኮ ወሰዱ፤ እንዲሁም በአንዳንድ እረኞች ሰፈር ላይ አደጋ በመጣል ብዙ በጎችን፥ ፍየሎችንና ግመሎችን ማረኩ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ።

2 ዜና መዋዕል 14:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አብያም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ልጁም አሳ በእርሱ ፋንታ ነገሠ። በእርሱም ዘመን ምድሪቱ ዐሥር ዓመት ያህል ዐረፈች። አሳም በአምላኩ በጌታ ፊት መልካምና ቅን ነገር አደረገ፤ የእንግዶቹንም አማልክት መሠዊያ የኮረብታውንም መስገጃዎች አፈረሰ፥ ሐውልቶቹንም ሰባበረ፥ የማምለኪያ ዐፀዶቹንም ቈረጠ፤ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን እንዲሹ፥ ሕጉንና ትእዛዙንም እንዲያደርጉ ይሁዳን አዘዘ። ከይሁዳም ከተሞች ሁሉ የኮረብታውን መስገጃዎችና የዕጣን መሠዊያዎቹን አስወገደ፤ መንግሥቲቱም በእርሱ ሥር ሰላም የሰፈነባት ሆነች። ምድሪቱ ሰላም ሰፍኖባት ስለ ነበር በይሁዳ የተመሸጉትን ከተሞችን ሠራ፤ እንዲሁም ጌታ ዕረፍትን ሰጠጥቶት ስለ ነበር በዚያም ዘመን ጦርነት አልነበረበትም። ይሁዳንም እንዲህ አለ፦ “እነዚህን ከተሞች እንሥራ፥ ቅጥርና ግንብ፥ መዝጊያና መቀርቀሪያ እናድርግባቸው፤ አምላካችንን ጌታን ስለ ፈለግነው ምድሪቱ አሁንም ድረስ የኛው ነች፤ እኛ ፈልገነዋል፥ እርሱም በዙሪያችን ዕረፍት ሰጥቶናል።” እነርሱም ሠሩ ተከናወነላቸውም። ለአሳም አላባሽ አግሬ ጋሻና ጦር የሚሸከሙ ሦስት መቶ ሺህ የይሁዳ ሠራዊት፥ ጋሻም የሚሸከሙ ቀስትም የሚገትሩ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ የብንያም ሰዎች ነበሩት፤ እነዚህም ሁሉ ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ነበሩ። ኢትዮጵያዊውም ዝሪ አንድ ሚሊዮን ሰዎችና ሦስት መቶ ሰረገሎች ይዞ ወጣባቸው፤ ወደ መሪሳም መጣ። አሳም ሊጋጠመው ወጣ፥ በመሪሳም አጠገብ ባለው በጽፋታ ሸለቆ ውስጥ ተሰለፉ። አሳም እንዲህ ብሎ ወደ አምላኩ ወደ ጌታ ጮኸ፦ “አቤቱ፥ በብዙም ሆነ በጥቂቱ ማዳን አይሳንህምና፤ አቤቱ አምላካችን ሆይ! በአንተ ታምነናልና፥ በስምህም በዚህ ታላቅ ወገን ላይ መጥተናልና እርዳን፤ አቤቱ፥ አምላካችን አንተ ነህ፤ ሰውም አያሸንፍህ።” ጌታም በአሳና በይሁዳ ፊት ኢትዮጵያውያንን ድል ነሣ፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። አሳም ከእርሱም ጋር ያለው ሕዝብ እስከ ጌራራ ድረስ አሳደዱአቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ፈጽመው እስኪጠፉ ድረስ ወደቁ፥ በጌታና በሠራዊቱ ፊት ተሰባብረዋልና፤ የይሁዳ ሰዎችም እጅግ ብዙ ምርኮ ወሰዱ። ከጌታም ዘንድ ታላቅ ድንጋጤ ስለ ያዛቸው በጌራራ ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ ድል በማድረግ በከተሞቹም ውስጥ እጅግ ብዝበዛ ነበርና ከተሞቹን ሁሉ በዘበዙ። የከብቶቹንም በረት አፈረሱ፤ እጅግም ብዙ በጎችንና ግመሎችንም ማረኩ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም ተመለሱ።