ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14:1-15

ሁለተኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 14:1-15 አማ05

ንጉሥ አቢያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘውም በነገሥታት መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ አሳ ነገሠ፤ በአሳም ዘመነ መንግሥት በምድሪቱ ላይ ለዐሥር ዓመት ሰላም ሆነ፤ አሳ በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና ቅን የሆነውን ነገር አደረገ፤ ባዕዳን መሠዊያዎችንና በኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብ የማምለኪያ ስፍራዎችን አስወገደ፤ ለማምለኪያ የተሠሩ የድንጋይ ዐምዶችን ሰባበረ፤ አሼራ ተብላ የምትጠራውን የሴት አምላክ ምስሎችን አንከታክቶ ጣለ፤ አሳ የይሁዳ ሰዎች የቀድሞ አባቶቻቸውን አምላክ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲፈጽሙ፥ ሕጉንና ትእዛዞቹን እንዲጠብቁ አዘዘ፤ የኰረብታ መስገጃዎች ስፍራዎችንና ዕጣን የሚታጠንባቸውን መሠዊያዎች ከይሁዳ ከተሞች ሁሉ ስላስወገደ፥ በእርሱ ዘመነ መንግሥት ሰላም ሰፈነ፤ ለይሁዳ ከተሞች ምሽጎችን ሠራ፤ እግዚአብሔር ሰላም ስለ ሰጠውም ለብዙ ዘመን በአገሪቱ ጦርነት አልነበረም፤ አሳ የይሁዳን ሰዎች እንዲህ አላቸው፤ “ግንቦችን፥ ቅጽሮችንና በብረት መወርወሪያ የሚዘጉ የቅጽር በሮችን በመሥራት፥ ከተሞቻችንን እንመሽግ፤ የአምላካችንን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስለ ፈጸምን፥ እነሆ፥ ምድሪቱ በቊጥጥራችን ሥር ናት፤ እግዚአብሔር ጠብቆናል፤ በሁሉም አቅጣጫ የሰላም ዋስትና ሰጥቶናል፤” ሕዝቡም ከተሞችን መሸገ፤ በለጸገም፤ ንጉሥ አሳ ታላላቅ ጋሻና ጦር የታጠቁ ሦስት መቶ ሺህ ሠራዊት ከይሁዳ፥ ታናናሽ ጋሻና ቀስት የያዙ ሁለት መቶ ሰማኒያ ሺህ ሠራዊት ከብንያም ነበሩት፤ እነዚህ ሁሉ በሚገባ የሠለጠኑ ጀግኖች ወታደሮች ነበሩ። ዜራሕ ተብሎ የሚጠራ ኢትዮጵያዊ አንድ ሚሊዮን ወታደሮችና ሦስት መቶ ሠረገሎች ይዞ ይሁዳን ለመውረር እስከ ማሬሻ ገሥግሦ መጣ፤ አሳም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ፤ ሁለቱም ወገኖች ማሬሻ አጠገብ በሚገኘው በጸፋታ ሸለቆ ቦታ ቦታቸውን በመያዝ ለውጊያ ተዘጋጁ፤ በዚህ ጊዜ አሳ ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “እግዚአብሔር ሆይ፥ ኀያላኑንም ሠራዊት ሆነ ደካማውንም የመርዳት ችሎታ አለህ፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ፥ በአንተ ስለ ተማመንን እነሆ፥ ይህን ብዙ ሠራዊት ለመውጋት መጥተናልና እባክህ እርዳን፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ አንተ አምላካችን ነህ፤ አንተን ማሸነፍ የሚችል ማንም የለም።” እግዚአብሔርም ኢትዮጵያውያንን እንዲያሸንፉ ዓሣንና ሠራዊቱን ረዳቸው፤ ኢትዮጵያውያንም ሸሹ። አሳና ሠራዊቱም እስከ ገራር ድረስ አሳደዱአቸው፤ ከኢትዮጵያ ሠራዊት ብዙ ሰዎች ስላለቁ፥ ሠራዊቱ እንደገና ተንሠራርቶ ሊዋጋ አልቻለም፤ በዚህም ዐይነት ኢትዮጵያውያን በእግዚአብሔርና በሠራዊቱ ድል ሆኑ፤ የይሁዳ ሰዎችም እጅግ የበዛ ምርኮ ወሰዱ፤ በዚያ አካባቢ የነበሩ ሕዝቦች እግዚአብሔር ባደረገው ነገር እጅግ ተሸብረው ነበር፤ የአሳም ወታደሮች በገራር ዙሪያ የነበሩትን ከተሞች ሁሉ ደመሰሱ፤ ከተሞቹንም ሁሉ በመዝረፍ ብዙ ምርኮ ወሰዱ፤ እንዲሁም በአንዳንድ እረኞች ሰፈር ላይ አደጋ በመጣል ብዙ በጎችን፥ ፍየሎችንና ግመሎችን ማረኩ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ።