መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 5
5
ሰሎሞን የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን ለመሥራት ያደረገው ዝግጅት
(2ዜ.መ. 2፥1-18)
1የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለአባቱ ለዳዊት በዘመኑ ሁሉ ወዳጁ ስለ ነበረ፥ ሰሎሞን በአባቱ ፋንታ ንጉሥ ለመሆን እንደ ተቀባ ሰምቶ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሊቀቡት ላከ” ይላል። አገልጋዮቹን ወደ ሰሎሞን ላከ። 2ሰሎሞንም ወደ ኪራም እንዲህ ብሎ ላከ፦ 3“እግዚአብሔር ከእግሩ በታች እስኪጥልለት ድረስ በዙሪያው ስለ ነበረ ጦርነት አባቴ ዳዊት ለአምላኩ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ለአምላኬ” ይላል። ለእግዚአብሔር ስም ቤት መሥራት እንዳልቻለ አንተ ታውቃለህ። 4አሁንም አምላኬ እግዚአብሔር በዙሪያዬ ካሉት ዕረፍት ሰጥቶኛል፤ ክፉም ነገር የሚያደርግ ጠላት የለብኝም። 5እነሆም፥ እግዚአብሔር ለአባቴ ለዳዊት፦ በአንተ ፋንታ በዙፋንህ ላይ የማስቀምጠው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤት ይሠራል ብሎ እንደ ነገረው፥ ለአምላኬ ለእግዚአብሔር ስም ቤት እሠራ ዘንድ አስባለሁ። 6አሁንም ከወገኔ እንደ ሲዶናውያን እንጨት መቍረጥ የሚያውቅ እንደሌለ ታውቃለህና የዝግባ ዛፍ ከሊባኖስ ይቈርጡልኝ ዘንድ አገልጋዮችህን እዘዝ፤ አገልጋዮቼም ከአገልጋዮችህ ጋር ይሁኑ፤ የአገልጋዮችህንም ዋጋ እንደ ተናገርኸው ሁሉ እሰጥሃለሁ።”
7ኪራምም የሰሎሞንን ቃል ሰምቶ እጅግ ደስ አለውና፥ “በዚህ ታላቅ ሕዝብ ላይ ጥበበኛ ልጅ ለዳዊት የሰጠ እግዚአብሔር ዛሬ ይመስገን” አለ። 8ኪራምም እንዲህ ሲል ወደ ሰሎሞን ላከ፥ “የላክህብኝን ሁሉ ሰማሁ፤ ስለ ዝግባውና ስለ ጥዱ እንጨት ፈቃድህን ሁሉ አደርጋለሁ። 9አገልጋዮቼ ከሊባኖስ ወደ ባሕር ያወርዱልሃል፤ እኔም በመርከብ አድርጌ በባሕር ላይ እያንሳፈፍሁ አንተ እስከ ወሰንኸው ስፍራ ድረስ አደርስልሃለሁ፤ በዚያም እፈታዋለሁ፤ አንተም ከዚያ ታስወስደዋለህ፤ አንተም ፈቃዴን ታደርጋለህ፤ ለቤተ ሰቦቼም ቀለብ የሚሆነውን ትሰጠኛለህ።” 10እንዲሁም ኪራም የዝግባውንና የጥዱን እንጨት፥ የሚሻውንም ሁሉ ለሰሎሞን ሰጠው። 11ሰሎሞንም ለኪራም ስለ ቤቱ ቀለብ ሃያ ሺህ የቆሮስ መስፈሪያ ስንዴ፥ ሃያ ሺህም በቤት መስፈሪያ ጥሩ ዘይት ይሰጠው ነበር፤ ሰሎሞንም ለኪራም በየዓመቱ ይህን ይሰጥ ነበር። 12እግዚአብሔርም እንደ ነገረው ለሰሎሞን ጥበብን ሰጠው፤ በኪራምና በሰሎሞንም መካከል ሰላም ነበረ፤ በመካከላቸውም ቃል ኪዳን አደረጉ።
13ሰሎሞንም ከእስራኤል ሁሉ ገባሮቹን መርጦ አወጣ፤ የገባሮቹም ቍጥር ሠላሳ ሺህ ሰዎች ነበረ። 14በየወሩም እያፈራረቀ ወደ ሊባኖስ ዐሥር ዐሥር ሺህ ይልክ ነበር፤ አንድ ወርም በሊባኖስ፥ ሁለት ወርም በቤታቸው ይቀመጡ ነበር። አዶኒራምም የገባሪዎች አለቃ ነበረ። 15ለሰሎሞንም ሰባ ሺህ ተሸካሚዎች፥ ሰማንያ ሺህም በተራራው ላይ ድንጋይ የሚጠርቡ ጠራቢዎች ነበሩት። 16ይኸውም በሰሎሞን ሥራ ላይ ከተሾሙት ከሦስት ሺህ ስድስት መቶ#ዕብ. “ሦስት ሺህ ሦስት መቶ” ይላል። የሠራተኞች አለቆች ሌላ ነው። 17ንጉሡም የለዘቡ ታላላቅ ድንጋዮችንና ለቤቱም መሠረት ያልተጠረበውን ድንጋይ ያመጡ ዘንድ አዘዘ። 18የሰሎሞንና የኪራም አናጢዎች፥ ጌባላውያንም ወቀሩአቸው፤ ለመሠረትም አኖሩአቸው፤ ቤቱንም ለመሥራት እንጨቱንና ድንጋዮቹን ሦስት ዓመት አዘጋጁ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 5: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ