መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 4
4
የሰሎሞን ሹሞች
1ንጉሡም ሰሎሞን በእስራኤል ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር። 2የነበሩትም አለቆች እነዚህ ናቸው፥ የሳዶቅ ልጅ ካህኑ ዓዛርያስ፤ 3ጸሓፊዎቹም የሱባ ልጆች ኤልያብና አኪያ፥ ታሪክ ጸሓፊውም የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ነበረ። 4የዮዳሄም ልጅ በንያስ የሠራዊት አለቃ ነበረ፤ ሳዶቅና አብያታርም ካህናት ነበሩ፤ 5የናታንም ልጅ ኦርኒያ የሹሞች አለቃ ነበረ፤ የናታንም ልጅ ዘባት የንጉሡ አማካሪና ወዳጅ ነበረ፤ 6አኪያልም የቤት አዛዥ፥ ኤልያቅም የቤት አዛዦች አለቃ ነበረ፥ የሳፋን ልጅ ኤልያፍም የቤተ ሰብ ሐላፊ፥ የአዶን ልጅ አዶኒራምም ግብር አስገባሪ ነበረ።
7ሰሎሞንም ለንጉሡና ለቤተሰቡ ቀለብ የሚሰጡ በእስራኤል ሁሉ ላይ ዐሥራ ሁለት ሹሞችን ሾመ። ከዓመቱ ውስጥ እያንዳንዱን ወር እያንዳንዳቸው ይቀልቡ ነበር። 8ስማቸውም ይህ ነበረ፤ በተራራማው ሀገር በኤፍሬም የሖር ልጅ ቢዖር፥ 9በማኪስና በሰአልቢን፥ በቤት ሳሚስና በኤሎንቤትሐናን የዴቀር ልጅ፥ 10በአራቦት፥ በሶኮትና በኦፌር ሀገር ሁሉ የሔሴድ ልጅ ነበረ፤ 11በዶር ሀገር ዳርቻ ሁሉ የአሚናዳብ ልጅ ነበረ፤ ለእርሱም የሰሎሞን ልጅ ጣፈትም ሚስቱ ነበረች፤ 12ከቤትሳን ጀምሮ እስከ አቤልምሖላና እስከ ዮቅምዓም ማዶ ድረስ በታዕናክና በመጊዶ በጸርታንም አጠገብ በኢይዝራኤል በታች ባለው በቤትሳን ሁሉ የአሒሉድ ልጅ በዓና ነበረ፤ 13በሬማት ዘገለዓድ የጌቤር ልጅ ነበረ፤ ለእርሱም በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ፤#“በገለዓድ ያሉት የምናሴ ልጅ የኢያዕር መንደሮች ነበሩ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ለእርሱም ደግሞ በባሳን፥ በአርጎብ ዳርቻ ያሉት ቅጥርና የናስ መወርወሪያዎች የነበረባቸው ስድሳ ታላላቅ ከተሞች ነበሩበት፤ 14በማሃናይም የሳዶ ልጅ አሒናዳብ ነበረ፤ 15በንፍታሌምም አኪማኦስ ነበረ፤ እርሱም የሰሎሞንን ልጅ ባሴማትን አግብቶ ነበር፤ 16በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ በዓና ነበረ፤ 17በይሳኮርም የፋሩዋ ልጅ ኢዮሣፍጥ ነበረ፤ 18በብንያም የኤላ ልጅ ሳሚ ነበረ፤ 19በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎንና በባሳን ንጉሥ በዐግ ሀገር፥ በጋድ ሀገር፥ የአዴ ልጅ ጌቤር ነበረ፤ በይሁዳም ምድር ላይ እርሱ ብቻውን ሹም ነበረ።
20ይሁዳና እስራኤልም እንደ ባሕር አሸዋ ብዛት ብዙ ነበሩ፤ ይበሉና ይጠጡም፥ ደስም ይላቸው ነበር። 21ሰሎሞንም ከወንዙ ጀምሮ እስከ ግብፅ ምድር ዳርቻ እስከ ፍልስጥኤማውያን ሀገር ድረስ በመንግሥታት ሁሉ ላይ ነግሦ ነበር፤ ግብርም ያመጡለት ነበር፤ በዕድሜውም ሙሉ ለሰሎሞን ይገዙ ነበር። 22ለሰሎሞንም ለቀን ለቀኑ ቀለብ የሚሆን ሠላሳ ቆሮስ መልካም ዱቄትና ስድሳ ቆሮስ መናኛ ዱቄት፤ 23ከዋሊያና ከሚዳቋ፥ ከበረሃ ፍየልና ከሰቡ ወፎች በቀር ዐሥር ፍሪዳዎች፥ ሃያም የተሰማሩ በሬዎች፥ አንድ መቶም በጎች ነበረ። 24ከወንዙ ወዲህ ባሉት ነገሥታት ሁሉ፥ ከወንዙም ወዲህ ባለው ሀገር ሁሉ ላይ ከቲላሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ ነግሦ ነበር፤#“ከቲላሳ ጀምሮ እስከ ጋዛ ድረስ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። በዙሪያውም ባለው በሁሉ ወገን ሰላም ሆኖለት ነበር። 25በሰሎሞንም ዘመን ሁሉ ይሁዳና እስራኤል ከዳን ጀምሮ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ እያንዳንዳቸው ከወይኑና ከበለሱ በታች ተዘልለው ይቀመጡ ነበር። 26ለሰሎሞንም ሰረገላ የሚስቡ አርባ ሺህ ፈረሶች፥ ዐሥራ ሁለት ሺህ ፈረሰኞች ነበሩት። 27እነዚያም ሹሞች እያንዳንዱ በየወሩ ንጉሡን ሰሎሞንንና ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ማዕድ የሚቀርቡትን ሁሉ ይቀልቡ ነበር፤ ምንም አያጐድሉም ነበር። 28እያንዳንዱም እንደ ደንቡ የንጉሡን ሰረገላዎች ለሚስቡ ለፈረሶችና ለሰጋር በቅሎዎች ገብስና ገለባ፥ እንዲሁም ዕቃዎችን ወደ ስፍራቸው ያመጡ ነበር።
29እግዚአብሔርም ለሰሎሞን እጅግ ብዙ ጥበብንና ማስተዋልን፥ በባሕርም ዳር እንዳለ አሸዋ የልብ ስፋትን ሰጠው። 30የሰሎሞንም ጥበብ ከቀደሙ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብፅ ጥበብ ሁሉ በዛ። 31ከሰዎችም ሁሉ ይልቅ ብልህ ነበረ፤ ከኢይዝራኤላዊው ከኤታንና ከማሖል ልጆች ከአውናንና ከከልቀድ፥ ከደራልም ይልቅ ጥበበኛ ነበረ። በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ።#“በዙሪያውም ባሉ አሕዛብ ሁሉ ዝናው ወጣ” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 32ሰሎሞንም ሦስት ሺህ ምሳሌዎችን ተናገረ፤ መሐልዩም አንድ ሺህ አምስት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አምስት ሽህ” ይላል። ነበረ። 33ስለ ዛፍም ከሊባኖስ ዝግባ ጀምሮ በቅጥር ግንብ ላይ እስከሚበቅለው እስከ አሽክት ድረስ ይናገር ነበር፤ ደግሞም ስለ አውሬዎችና ስለ ወፎች ስለ ተንቀሳቃሾችና ስለ ዓሣዎች ይናገር ነበር። 34ከአሕዛብም ሁሉ፥ ጥበቡን ሰምተው ከነበሩ ከምድር ነገሥታት ሁሉ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ሰዎች ይመጡ ነበር።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 4: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ