መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 3
3
ሰሎሞን ጥበብን እንደ ለመነ
(2ዜ.መ. 1፥3-12)
1ሰሎሞንም ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን አማች ሆነ፤ የፈርዖንንም ልጅ አገባ፤ ቤቱንና የእግዚአብሔርንም ቤት፥ በኢየሩሳሌምም ዙሪያ ያለውን ቅጥር ሠርቶ እስኪፈጽም ድረስ ወደ ዳዊት ከተማ አምጥቶ አስገባት። 2እስከዚያም ቀን ድረስ ለእግዚአብሔር ቤት አልተሠራም ነበርና ሕዝቡ በኮረብታ ላይ ይሠዉና ያጥኑ ነበር። 3ሰሎሞንም እግዚአብሔርን ይወድድ ነበር፤ በአባቱም በዳዊት ሥርዐት ይሄድ ነበር፤ ነገር ግን በኮረብታው ላይ ይሠዋና ያጥን ነበር።
4ገባዖን ፈጽማ ትሰፋ ነበርና በዚያ መሥዋዕት ይሠዋ ዘንድ ተነሥቶ ሄደ፤ ሰሎሞንም በዚያ መሠዊያ ላይ በገባዖን አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዋ። 5እግዚአብሔርም በገባዖን ለሰሎሞን በሌሊት በሕልም ተገለጠለት፤ እግዚአብሔርም ሰሎሞንን፥ “እንድሰጥህ የምትፈልገውን ለምን” አለው። 6ሰሎሞንም አለ፥ “እርሱ በፊትህ በእውነትና በጽድቅ፥ በልብም ቅንነት ከአንተ ጋር እንደ ሄደ፥ ከአባቴ ከባሪያህ ከዳዊት ጋር ታላቅ ቸርነት አድርገሃል፤ ዛሬ እንደ ሆነም በዙፋኑ ላይ የሚቀመጥ ልጅ ሰጥተህ ታላቁን ቸርነትህን አቈይተህለታል። 7አሁንም አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ እኔን ባሪያህን በአባቴ በዳዊት ፋንታ አንግሠኸኛል፤ እኔም መውጫዬንና መግቢያዬን የማላውቅ ታናሽ ብላቴና ነኝ። 8ባሪያህም ያለው አንተ በመረጥኸው ሕዝብህ፥ ስለ ብዛቱም ይቈጠር ዘንድ በማይቻል በታላቅ ሕዝብ መካከል ነው። 9ስለዚህም ሰምቶ በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ ማን ይችላል?”
10ሰሎሞንም ይህን ነገር ስለ ለመነ፥ ነገሩ እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው። 11እግዚአብሔርም አለው፥ “ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን፥ ባለጠግነትንም፥ የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና፥ 12እነሆ፥ እኔ እንደ ቃልህ አድርጌልሃለሁ፤ እነሆም፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ፥ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡና ሰጥቼሃለሁ። 13ደግሞም ከነገሥታት የሚመስልህ ማንም እንዳይኖር ያልለመንኸውን ባለጠግነትና ክብር ሰጥቼሃለሁ። 14አባትህም ዳዊት እንደ ሄደ፥ ሥርዐቴንና ትእዛዜን ትጠብቅ ዘንድ በመንገዴ የሄድህ እንደ ሆነ፥ ዘመንህን አበዛልሀለሁ።” 15ሰሎሞንም ነቃ፤ እነሆም፥ ሕልም ነበረ፤ ተነሥቶም ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ በጽዮንም በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆመ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አሳረገ፤ የደኅንነትንም መሥዋዕት አቀረበ፤ ለአገልጋዮቹም ሁሉ ታላቅ ግብዣ አደረገ።
ጥበብ የሞላበት የሰሎሞን ፍርድ
16በዚያ ጊዜም ሁለት ጋለሞታዎች ሴቶች ወደ ንጉሡ መጥተው ቆሙ። 17አንደኛዪቱም ሴት አለች፥ “ጌታዬ ሆይ! ስማኝ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን፤ በአንድ ቤትም ወለድን። 18እኔም በወለድሁ በሦስተኛው ቀን ይህች ሴት ወለደች፤ እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፤ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም። 19እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ። 20እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ አገልጋይህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከብብቴ ወሰደች፤ በብብቷም አስተኛችው፤ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አስተኛችው። 21ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ ያን የሞተውን ልጅ አገኘሁ፤ ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፤ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም።” 22ሁለተኛዪቱም ሴት፥ “አይደለም ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፤ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አለች።”#ዕብ. “ይህችም የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው” አለች የሚል ይጨምራል። እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር።
23በዚያ ጊዜም ንጉሡ፥ “አንቺ፦ ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፤ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው ትያለሽ፤ አንቺም፦ አይደለም የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትያለሽ”። አላቸው። 24ንጉሡም፥ “ሰይፍ አምጡልኝ” አለ፤ እነርሱም ወደ ንጉሡ ሰይፍ አመጡ። 25ንጉሡም፥ “ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ቈርጣችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛዪቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ” አለ። 26ደኅነኛውም ሕፃን የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ታውኳልና፥ “ጌታዬ ሆይ! አይደለም፤ ደኅነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ መግደልስ አትግደሉት” ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛዪቱ ግን፥ “አካፍሉን እንጂ ለእኔም ለእርስዋም አይሁን” አለች። 27ንጉሡም መልሶ እንዲህ አለ፥ “ለእርስዋ ስጧት እንጂ መግደልስ አትግደሉት ላለችው ሴት ስጡአት፤ እናቱ እርስዋ ናትና።” 28ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ፤ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ በእርሱ ላይ እንደ ነበረ አይተዋልና ከንጉሡ ፊት የተነሣ ፈሩ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ