መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 2
2
ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው ምክር
1ዳዊትም የሚሞትበት ወራት ደረሰ፤ ልጁንም ሰሎሞንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ 2“እኔ የምድሩን መንገድ ሁሉ እሄዳለሁ፤ በርታ ሰውም ሁን፤ 3እንደማዝዝህ የምታደርገውን ሁሉ ታውቅ ዘንድ፥ በሙሴ ሕግ የተጻፈውን ሥርዐቱንና ትእዛዛቱን፥ ፍርዱንና ምስክሩንም ትጠብቅ ዘንድ በመንገዱም ትሄድ ዘንድ፥ የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። 4ይኸውም እግዚአብሔር ስለ እኔ፦ ‘ልጆችህ መንገዳቸውን ቢጠብቁ፥ በፊቴም በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በእውነት ቢሄዱ ከእስራኤል ዙፋን ሰው አይጠፋም’ ብሎ የተናገረውን ቃል ያጸና ዘንድ ነው። 5አንተም ደግሞ የሶርህያ ልጅ ኢዮአብ፥ ሁለቱን የእስራኤል ሠራዊት አለቆች የኔር ልጅ አበኔርን የኢያቴርንም ልጅ አሜሳይን ገድሎ፥ በእኔ ላይ ያደረገውን ታውቃለህ፤ የጦርነትንም ደም በሰላም አፈሰሰ፤ በወገቡም ባለው ድግና በእግሩም ባለው ጫማ ንጹሕ ደም አኖረ። 6አንተም እንደ ጥበብህ አድርግ፤ ሽበቱንም በሰላም ወደ መቃብር አታውርደው። 7ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ ቀርበውኛልና ለገለዓዳዊው ለቤርዜሊ ልጆች ቸርነትን አድርግላቸው። በማዕድህም ከሚበሉት መካከል ይሁኑ። 8የባውሬም ሀገር ሰው የብንያማዊው የጌራ ልጅ ሳሚ እነሆ! በአንተ ዘንድ ነው፤ እኔም ወደ መሃናይም በሄድሁ ጊዜ ብርቱ ርግማን ረገመኝ፤ ከዚያም በኋላ ዮርዳኖስን በተሻገርሁ ጊዜ ሊቀበለኝ ወረደ፤ እኔም፦ ‘በሰይፍ አልገድልህም’ ብዬ በእግዚአብሔር ምየለታለሁ። 9አንተ ግን ጥበበኛ ሰው ነህና ንጹሕ አታድርገው፤ የምታደርግበትንም አንተ ታውቃለህ፤ ሽበቱንም በደም ወደ መቃብር አውርደው” አለው።
የንጉሥ ዳዊት ሞት
10ዳዊትም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ። 11ዳዊትም በእስራኤል ላይ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበረ። በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌምም ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ። 12ሰሎሞንም በአባቱ በዳዊት ዙፋን ተቀመጠ፤ መንግሥቱም እጅግ ጸና።
የአዶንያስ መገደል
13የአጊት ልጅ አዶንያስም ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ መጣ፤ ሰገደላትም፤ እርስዋም፥ “ወደ እኔ መምጣትህ በሰላም ነውን?” አለችው። እርሱም፥ “በሰላም ነው” አለ። 14ደግሞም፥ “ከአንቺ ጋር ጉዳይ አለኝ” አለ፤ እርስዋም፥ “ተናገር” አለችው። 15እርሱም፥ “መንግሥቱ ለእኔ እንደ ነበረ፥ እስራኤልም ሁሉ ንጉሥ እሆን ዘንድ ፊታቸውን ወደ እኔ አድርገው እንደ ነበረ አንቺ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆኖለታልና መንግሥት ተመልሳ ለወንድሜ ሆናለች። 16አሁንም አንዲት ልመና እለምንሻለሁ ፤ ፊትሽንም አትመልሺብኝ” አላት። እርስዋም፥ “ተናገር” አለችው፤ 17እርሱም፥ “ፊቱን አይመልስብሽምና፥ ሱነማዪቱን አቢሳን ይድርልኝ ዘንድ ለንጉሡ ለሰሎሞን እንድትነግሪው እለምንሻለሁ” አለ። 18ቤርሳቤህም፥ “መልካም ነው፤ ስለ አንተ ለንጉሡ እነግረዋለሁ” አለች።
19ቤርሳቤህም የአዶንያስን ነገር ትነግረው ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን ገባች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ ሳማትም፤ በዙፋኑም ተቀመጠ፤ ለንጉሡም እናት ወንበር አስመጣላት፤ በቀኙም ተቀመጠች። 20እርስዋም፥ “አንዲት ትንሽ ልመና እለምንሃለሁ፤ ፊትህን አትመልስብኝ” አለች። ንጉሡም፥ “እናቴ ሆይ! ፊቴን አልመልስብሽምና ለምኚ” አላት። 21እርስዋም፥ “ሚስት ትሆነው ዘንድ ለወንድምህ ለአዶንያስ ሱነማዪቱ አቢሳን ይስጡት” አለች። 22ንጉሡም ሰሎሞን ለእናቱ መልሶ፥ “ሱነማዪቱን አቢሳን ለአዶንያስ ለምን ትለምኚለታለሽ? ታላቅ ወንድሜ ነውና መንግሥትን ደግሞ ለምኚለት፤ ካህኑም አብያታርና የሶርህያ ልጅ የጭፍሮች አለቃ ኢዮአብ ደግሞ ከእርሱ ጋር ናቸው” አላት። 23ንጉሡም ሰሎሞን፦ እንዲህ ሲል በእግዚአብሔር ማለ። “አዶንያስ ይህን ቃል በሕይወቱ ላይ እንደ ተናገረ እግዚአብሔር ይህን ያድርግብኝ፤ ይህንም ይጨምርብኝ። 24አሁንም ያጸናኝ፥ በአባቴም በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠኝ፥ እንደ ተናገረውም ቤትን የሠራልኝ ሕያው እግዚአብሔርን! ዛሬ አዶንያስ ፈጽሞ ይገደላል። 25ንጉሡም ሰሎሞን የዮዳሄን ልጅ በናያስን ላከ፤ እርሱም አረደው፤ ያንጊዜም አዶንያስ ሞተ።
የአብያታር መሻርና የኢዮአብ መገደል
26ንጉሡም ካህኑን አብያታርን፥ “አንተ ዛሬ የሞት ሰው ነበርህ፤ ነገር ግን የአምላክን የእግዚአብሔርን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ስለ ተሸከምህ፥ አባቴም የተቀበለውን መከራ ሁሉ አንተ ስለ ተቀበልህ አልገድልህምና በዓናቶት ወዳለው ወደ እርሻህ ፈጥነህ ሂድ” አለው። 27በሴሎም በዔሊ ቤት ላይ የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ይፈጸም ዘንድ ሰሎሞን አብያታርን ከእግዚአብሔር ክህነት አወጣው።
28ለሶርህያ ልጅ ለኢዮአብም ወሬ ደረሰለት፤ ኢዮአብ ከአዶንያስ ጋር ተባብሮ ተከተለው እንጂ ከሰሎሞን#ዕብ. “ከአቤሴሎም ጋር” ይላል። ጋር አልተባበረም፤ አልተከተለውምም ነበርና። ኢዮአብም ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ ያዘ። 29ንጉሡም ሰሎሞን ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን ሸሽቶ የመሠዊያውን ቀንድ እንደ ያዘ ሰማ፤ ንጉሥ ሰሎሞንም ወደ ኢዮአብ እንዲህ ሲል ላከ፤ “በመሠዊያው ቀንድ የተማጠንህ ምን ሆነህ ነው?” ኢዮአብም፥ “ፈርቼሃለሁና በእግዚአብሔር ተማጠንሁ” አለ። ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በንያስን ልኮ፥ “ሂድ ግደልና ቅበረው” ብሎ አዘዘው። 30የዮዳሄ ልጅ በንያስም ወደ ኢዮአብ ወደ እግዚአብሔር ድንኳን መጥቶ፥ “ንጉሡ፦ ውጣ ይልሃል” አለው፤ ኢዮአብም፥ “በዚህ እሞታለሁ እንጂ አልወጣም” አለ። የዮዳሄ ልጅ በንያስም፦ ተመልሶ “ኢዮአብ የተናገረው ቃል፥ የመለሰልኝም እንዲህ ነው” ብሎ ለንጉሡ ነገረው። 31ንጉሡም አለው፥ “ሂድና እንደ ነገረህ አድርግ፤ ገድለህም ቅበረው፤ ኢዮአብም በከንቱ ያፈሰሰውን ደም ከእኔና ከአባቴ ቤት ታርቃለህ። 32አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ከእርሱ የሚሻሉትን ሁለቱን ጻድቃን ሰዎች፥ የእስራኤልን ሠራዊት አለቃ የኔርን ልጅ አበኔርን፥ የይሁዳንም ሠራዊት አለቃ የኢያቴርን ልጅ አሜሳይን በሰይፍ ገድሎአልና እግዚአብሔር የዐመፅ ደሙን በራሱ ላይ መለሰ። 33ደማቸውም በኢዮአብ ራስና በዘሩ ራስ ላይ ለዘለዓለም ይመለስ፤ ለዳዊት ግን ለዘሩና ለቤቱ፥ ለዙፋኑም የእግዚአብሔር ሰላም ለዘለዓለም ይሁን።” 34የዮዳሄም ልጅ በንያስ ወጥቶ ያዘው፤ ገደለውም፤ በምድረ በዳም ባለው በራሱ ቤት ቀበረው። 35ንጉሡም በእርሱ ፋንታ የዮዳሄን ልጅ በንያስን የሠራዊቱ አለቃ አድርጎ ሾመ፤ መንግሥቱም በኢየሩሳሌም ጸናች። በአብያታርም ፋንታ ካህኑን ሳዶቅን ሾመ።
የሳሚ መገደል
36ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራውና እንዲህ አለው፥ “በኢየሩሳሌም ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ወዲህና ወዲያም አትውጣ። 37በምትወጣበትና የቄድሮንንም ፈፋ በምትሻገርበት ቀን ፈጽመህ እንደምትሞት ዕወቅ፤ ደምህም በራስህ ላይ ይሆናል።” ያንጊዜም ንጉሡ አማለው። 38ሳሚም ንጉሡን፥ “ጌታዬ ንጉሥ የተናገርኸው ቃል መልካም ነው፤ አገልጋይህም እንዲሁ ያደርጋል” አለው፤ ሳሚም በኢየሩሳሌም ሦስት ዓመት ተቀመጠ።
39ከሦስት ዓመትም በኋላ ከሳሚ አገልጋዮች ሁለቱ ወደ ጌት ንጉሥ ወደ መዓካ ልጅ ወደ አንኩስ ኰበለሉ፤ ለሳሚም፥ “እነሆ፥ አገልጋዮችህ በጌት ናቸው” ብለው ነገሩት። 40ሳሚም ተነሣ፤ አህያውንም ጭኖ አገልጋዮቹን ይሻ ዘንድ ወደ ጌት ወደ አንኩስ ዘንድ ሄደ፤ ሳሚም ሄዶ አገልጋዮቹን ከጌት አመጣ። 41ሰሎሞንም ሳሚ ከኢየሩሳሌም ወደ ጌት ሄዶ አገልጋዮቹን እንዳመጣ ሰማ። 42ንጉሡም ልኮ ሳሚን አስጠራና፥ “ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ለመሄድ በምትወጣበት ቀን ፈጽመህ እንድትሞት ዕወቅ ብዬ በእግዚአብሔር አላስማልሁህምን? ወይስ አላስመሰከርሁብህምን?#ዕብ. “አንተም ቃሉ መልካም ነው ሰምቻለሁ አልኸኝ” ብሎ ይጨምራል። 43የእግዚአብሔርን መሐላ፥ እኔም ያዘዝሁትን ትእዛዝ ስለምን አልጠበቅህም?” አለው። 44ንጉሡም ደግሞ ሳሚን፥ “አንተ በአባቴ በዳዊት ላይ የሠራኸውን፥ ልብህም ያሰበውን ክፋት ሁሉ ታውቃለህ፤ እግዚአብሔርም ክፋትህን በራስህ ላይ ይመልሳል። 45ንጉሡ ሰሎሞን ግን የተባረከ ይሆናል፤ የዳዊትም ዙፋን በእግዚአብሔር ፊት ለዘለዓለም ይጸናል” አለው። 46ሰሎሞንም የዮዳሄን ልጅ በንያስን አዘዘው፤ ወጥቶም ገደለው። የሰሎሞንም መንግሥት በኢየሩሳሌም ጸና።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ