መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 3
3
የዓለም ፍጻሜ ምልክት
1“ምልክቱም እነሆ፥ ወራት ይመጣል፤ በምድር የሚኖሩትንም ሰዎች ታላቅ ድንጋፄ ይይዛቸዋል፤ የጽድቅ መንገድም ትሰወራለች፤ ሃይማኖትም ከሀገር ትጠፋለች። 2በደልም አንተ ከአየኸውና ከሰማኸው ይልቅ ይበዛል። 3ዛሬ የጠፋና የፈረሰ ሆኖ የምታየውም ሀገር ይጠፋል፤ ምድርም ምድረ በዳ ትሆናለች። 4ልዑልም ሕይወትህን ከሰጠህ ከሦስት ወራት በኋላ ምድርን ስትታወክ ታያታለህ፤ ፀሐይም ድንገት በሌሊት ያበራል፤ ጨረቃም ድንገት በቀን ያበራል። 5ከእንጨቶችም ደም ይፈስሳል፤ ድንጋይም ትጮኻለች፤ ሕዝቡም ይታወካሉ፤ ከዋክብትም ይረግፋሉ።
6“ብዙዎች ያልጠረጠሩት ይነግሣል። 7ሁሉም ቃሉን ይሰማል። 8በብዙ ሀገሮች ሽብር ይሆናል፤ ጥቅል እሳትም ይላካል፤ የምድረ በዳ አውሬዎችም ከቦታቸው ይፈልሳሉ። ከሴቶችም ባለ ምልክት ይወለዳል። 9የሚጣፍጠውም ውኃ መራራ ይሆናል፤ ወዳጆችም እንደ ጠላት በድንገት እርስ በርሳቸው ይጋደላሉ፤ ያንጊዜም ጥበብ ትሰወራለች፤ ምክርም ወደ ማደሪያዋ ትመለሳለች። 10ብዙ ሰዎች ይፈልጓታል፤ ነገር ግን አያገኙአትም፤ በምድርም ላይ ኀጢአት፥ ዐመፅም፥ ስንፍናም ትበዛለች። 11አንዲቱ ሀገር አቅራቢያዋን ሀገር ‘በውኑ በአንቺ ዘንድ የተደረገ ጽድቅ አለን? ወይስ ጽድቅን የሚያደርግ ሰው አለን?’ ብላ ትጠይቃታለች። ያችም ‘የለም’ ትላታለች። 12በእነዚያም ወራቶች#“ሰዎች ብዙ ይመኛሉ ነገር ግን አያገኙም ...” የሚል ዘርዕ ይገኛል። ሰው ሞትን ይመኛል፤ ነገር ግን አያገኝም፤ ሚስትም ያገባል፤ ደስም አይለውም፤ ይደክማል፤ ሥራውንም ይሠራል፤ መንገዱ ግን አይከናወንለትም። 13ይኽንም ምልክት እነግርህ ዘንድ ተላክሁ፤ ዛሬ እንደ ጾምህም ዳግመኛ ሰባት ቀን ብትጸልይና ብታለቅስ ከዚህ የሚበልጥ ትሰማለህ።”
14ዳግመኛም ከእንቅልፌ ነቃሁ፤ ሰውነቴም እጅግ ስቅጥጥ አለችብኝ፤ ሰውነቴም እስክትዝል ድረስ ደከመች። 15ወደ እኔ የመጣውና የተናገረኝ መልአኩም እጄን ያዘኝ፤ በእግሬም አቁሞ አጸናኝ።
16ከዚህም በኋላ በሁለተኛዪቱ ሌሊት የሕዝቡ ያለቆቻቸው አለቃ ፍልስጥያል ወደ እኔ መጣ፤ እንዲህም አለኝ፥ “አንተ ዕዝራ! ወዴት ነበርህ? ፊትህስ ስለ ምን አዝኗል? 17በምርኮ ሀገር ያሉ እስራኤል ሁሉ ለአንተ አደራ እንደ ተሰጡህ አታውቅምን? 18እንግዲህስ እስራኤልን እንዳትጥላቸው፥ መንጋዎችንም በክፉዎች ተኵላዎች አፍ እንደ ጣለ እረኛ እንዳትሆን ተነሥተህ እህልን ቅመስ።”
19እንዲህም አልሁት፥ “ከእኔ ዘንድ ሂድ፤ ዳግመኛም እስከ ሰባት ቀን ድረስ ወደ እኔ አትምጣ፤ ከዚህም በኋላ ወደ እኔ ና፤ እኔም ነገርን እነግርሃለሁ፥”#“እኔም ነገርን እነግርሃለሁ” የሚለው ከግእዙ በቀር በሌሎች ቅጂዎች የለም። ከእኔም ዘንድ ሄደ።
ሁለተኛው ራእይ
20እኔም መልአኩ ዑርኤል እንዳዘዘኝ አዝኜ እያለቀስሁ ሰባት ቀን ጾምሁ። 21ከሰባት ቀን በኋላም የልቡናዬ አሳብ እጅግ አደከመኝ። 22የጥበብም መንፈስ ሰውነቴን አነሣሣቻት፤ ዳግመኛም በልዑል ፊት እናገር ጀመርሁ። 23እንዲህም አልሁ፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ ከምድር ዛፎችና እንጨቶች ሁሉ አንድ የወይን ሐረግን ለአንተ መረጥህ። 24ከዓለሙ ጥልቆች ሁሉ አንድ ወንዝን ለአንተ መላህ። 25ከሀገሮችም ሁሉ አንድ ሀገርን መረጥህ፤#ሌሎች ዘሮች “ከአበቦችም ሁሉ አንዲትዋን የሱሳን አበባ ለአንተ መረጥህ” የሚል ይጨምራሉ። ከተሠሩት ከተሞችም ሁሉ ጽዮንን ለአንተ ቀደስህ። 26ከተፈጠሩ ወፎችም ሁሉ አንድ ርግብን ለአንተ ለየህ፤ ከተፈጠሩት እንስሳትም ሁሉ አንድ በግን መረጥህ። 27ከምድር አሕዛብ ሁሉ አንድ ሕዝብን ለራስህ መረጥህ፤ ለዚህ ለመረጥኸው ሕዝብህም በሁሉ ዘንድ የተፈተነ ሕግህን ሰጠኸው።
28“አሁንም አቤቱ፥ ይህን አንዱን ለብዙዎች አሳልፈህ ለምን ሰጠኸው? ከሌሎችም ሥሮች ለይተህ አንዱን ሥር ለምን አጐሳቈልኸው? አንድ ሕዝብንስ በብዙዎች መካከል ለምን በተንኸው? 29የተስፋህ ባላጋራዎችዋ በሕግህ የታመኑትን ረገጧቸው። 30ወገኖችህንስ ከጠላሃቸው አንተ በእጅህ ብትቀጣቸው ይሻላል።”
31ይኽንም ቃል ከተናገርሁ በኋላ ባለፈችው በዚያች ሌሊት አስቀድሞ ወደ እኔ የመጣው መልአክ ወደ እኔ ተላከ። 32እንዲህም አለኝ፥ “ስማኝ ልንገርህ፤ አድምጠኝ ብዙም እነግርሃለሁ።” 33እኔም አልሁት፥ “አቤቱ ተናገር።” እርሱም አለኝ፥ “ይህ ለእስራኤል እጅግ ድንቅ ነውን? ወይስ ከፈጣሪው ይልቅ እስራኤልን አንተ እጅግ ትወድደዋለህን?” 34እኔም አልሁት፥ “አቤቱ፥ አይደለም፤ ነገር ግን ስለ አሳሰበኝ ተናገርሁ፤ አቤቱ፥ ሁልጊዜም የልዑልን መንገድ አገኝ ዘንድ፥ የፍርዱንም ፍለጋ አውቅ ዘንድ ስመራመር ኵላሊቴን አስጨነቀኝ።” 35እርሱም አለኝ፥ “አትችልም።” እኔም አልሁት፥ “አቤቱ፥ ስለ ምንድን ነው? ስለ ምንስ ተወለድሁ? የያዕቆብን መከራ፥ የእስራኤልንም ወገኖች ድካማቸውን እንዳላይ የእናቴ ማኅፀን ስለምን መቃብር አልሆነኝም?” 36እንዲህም አለኝ፥ “ገና ያልመጡ ቀኖችን ቍጠር፥#“የተበተኑትን የዝናም ነጠብጣቦች ሰብስብልኝ” የሚል ዘርዕ ይገኛል። የተበተኑትንም አበባዎች ሰብስብልኝ፤ የደረቀውንም ሣር አለምልምልኝ። 37የተዘጉትንም ቤቶች ክፈትልኝ፤ በውስጣቸውም የተዘጉ ነፋሳትን አምጣልኝ፤ ፈጽሞ ያላየኋቸውንም ፊታቸውን አሳየኝ፤ ቃላቸውንም አሰማኝ፤ የዚያን ጊዜም በሚገባ ያገኛቸውን መከራ እነግርሃለሁ።”
38እኔም መልሼ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ፥ አነዋወሩ ከሰው የተለየ ካልሆነ በቀር ይህን ማወቅ የሚችል ማንነው? 39እኔ ዐላዋቂና የተዋረድሁ ነኝ፤ ይህንም የምትጠይቀኝን ነገር እንዴት ልነግርህ እችላለሁ?” 40እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “እኔ ከምነግርህ ከእኒህ አንዱን መናገር እንደማትችል እንደዚሁ ፍርዴንና ስለ ወገኖች የምታገሠውን የፍቅሬን መጨረሻ ማግኘት አትችልም።” 41እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ፥ እነሆ፥ አንተ ስለ እነርሱ ታገሥህ፤ ከእኛ አስቀድሞ የነበሩ እንግዲህ ምን ያደርጋሉ? እኛና ከእኛ በኋላ የሚነሡትስ?” 42እርሱም አለኝ፥ “ወደ ኋላ ያሉት እንዳይዘገዩ፥ የቀደሙትም እንዳይፈጥኑ ፍርዴን እንደ ቀለበት አደረግኋት።” 43እኔም አልሁት፥ “ፍርድህን ፈጥነህ ታሳይ ዘንድ የቀደሙትንና ወደ ኋላ ያሉትን አሁንም ያሉትን፥ ባንድ ጊዜ አንድ አድርገህ መፍጠር አትችልም ነበርን?” ። 44እንዲህም አለኝ፥ “ሥራ ከሠሪው ፈጽሞ የሚቸኩል አይደለም፤ ዓለምም በውስጧ የተፈጠሩትን ባልቻለቻቸውም ነበር።” 45እንዲህም አልሁት፥ “አቤቱ የፈጠርሃቸውን በአንድ ጊዜ በአንድነት እንደምታስነሣቸው ለእኔ ለባሪያህ እንዴት ነገርኸኝ? የፈጠርሃቸውንም በአንድ ጊዜ ፈጥነህ የምታስነሣቸው ከሆነ ዓለም ይጨነቃል፤#በአንዳንድ ዘርዕ “ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” የሚል ይገኛል። ይህም ባይሆን ዛሬ ካሉት ጋራ አንድ ጊዜ ሊሸከማቸው በቻለ ነበር።” 46እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “እስኪ የሴት ማኅፀንን እሺ አሰኛት፤ ዐሥር ልጆችንም ስትወልጂ ለምን በየዓመቱ ትወልጃለሽ? በላት። እንግዲህ ዐሥሩን በአንድ ጊዜ ትሰጥ እንደ ሆነ ጠይቃት። 47በየዓመቱ ካልሆነ በቀር በአንድ ጊዜ የማትችል አይደለምን? 48ሕፃን ሴት መውለድ እንደማትችል፥ ያረጀችም እንደማትችል፥ እንዲሁ እኔም ለፈጠርሁት ዓለም በየጊዜው ሥርዐት ሠራሁለት።”#አንዳንድ ዘሮች “በምድር ላይ ማኅፀን በየዓመቱ ካልሆነ በቀር በአንድ ጊዜ ብዙ ልጆችን እንደማትወልድ ሥርዐት ሠርቻለሁ” የሚል ይጨምራል።
49እኔም ጠየቅሁት፤ እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ እናገር ዘንድ መንገድ ሰጥተኸኛልና እነሆ፥ በእውነት አንተ አልኸኝ፤ ወጣት የነበረች እናታችሁ ፈጽማ አረጀች፤ ኀይላችንስ እንደ ቀደሙን ሰዎች ኀይል ለምን አልሆነልንም?” 50እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “ልጅ የወለደች ሴትን ጠይቃት፤ ትነግርሃለችም። 51በጥንካሬ ያንሳሉ እንጂ ዛሬ የወለድሻቸው ቀድሞ እንደ ወለድሻቸው ለምን አልሆኑም? በላት። 52እርሷም እንዲህ ትልሃለች፥ “በወጣትነት የተወለደ ልጅ ልዩ ኀያል ነው፤ በእርጅና የተወለደውም ልዩ ደካማ ነው። 53ነገር ግን ከቀደሙት ሰዎች እናንተ በኀይል እንደምታንሱ አንተ ራስህ ታውቀዋለህ። 54ከእናንተም በኋላ የሚወለዱ ከእናንተ ያንሣሉ፤ የተፈጠረውና ያለውም የሕፃንነቱ ኀይል ዘመን ካለፈ እንዲሁ ነው።” 55እኔም አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ እሺ በለኝ፤ በዐይኖችህ ፊት ባለሟልነትን ካገኘሁ ለባሪያህ ንገረው፤ ዓለምህን በማን ትጐበኛለህ?”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 3: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ